የሲሪላንካ ተቃዋሚዎች ከቤተ-መንግሥቱ ለመልቀቅ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ

ከቀናት በፊት ነበር በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በሲሪላንካ መዲና ኮሎምቦ ውስጥ ወደሚገኘውን ፕሬዝዳንት ጎታባያ ቤተ መንግስትን ጥሰው የገቡት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፕሬዝዳንታዊውን ቤተ-መንግሥት የተቆጣጠሩት የሲሪላንካ ተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ሥልጣን መልቀቃቸውን ሳያረጋግጡ ቤተ-መንግሥቱን እንደማይለቁ ይፋ አደረጉ።

ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዊክሬሜሲንጌ፤ ለወራት የዘለቀው ሕዝባዊ አመጽን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ አመጸኞች ቤተ መንግሥታቸውን ተቆጣጥረውታል።

ይህንንም ተከትሎ ከሥልጣናቸውን እንደሚለቁ እሁድ ሐምሌ 03/2014 ዓ.ም. ተግልጾ ነበር። በዚህም በመጪው ረቡዕ ሐምሌ 6 ሥልጣናቸውን እንደሚያስረክቡም ገልጸው ነበር።

ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ እስካሁን በአካል ቀርበው ወይም ይፋዊ መግለጫ ሲሰጡ አልታዩም። የአገሪቱ የመከላከያ ምንጮች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ፕሬዝዳንቱ በባሕር ኃይል መርከብ ላይ ሲሪላንካ ውስጥ ይገኛሉ።

ከእርሳቸውም በተጨማሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩት ወንድማቸው ማሂንድራ ራጃፓክሳ በተመሳሳይ በመርከብ ላይ እንደሚገኙ ምንጮች አረጋግጠዋል።

ከሦስት ቀናት በፊት ነበር በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በሲሪላንካ መዲና ኮሎምቦ ወደሚገኘውን ፕሬዝዳንት ጎታባያ ቤተ መንግሥትን ጥሰው የገቡት። በወቅቱም ፕሬዝዳንቱ በቤተ-መንግሥታቸው ውስጥ አልነበሩም።

ሲሪላንካ በአሁኑ ወቅት በባድ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት አጋጥሟታል።

በዚህም በአገሪቱ በተከሰተ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ መድኃኒት፣ ነዳጅ እና ምግብ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ተስኗታል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት ከመላው አገሪቱ በግል መኪኖች፣ አውቶቢሶች እና ባቡር ተጠቅመው ወደ መዲናዋ ሲተሙ ቆይተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ ለተከሰተው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሲወቀሱ የቆዩ ሲሆን በተለይም ኢኮኖሚውን በአግባቡ አላስተዳደሩም የሚል ወቀሳ ሲደርስባቸው ቆይቷል።

ታዲያ መሪዎቹ ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ ቢናገሩም ተቃዋሚዎች ግን ጥርጣሬያቸውን በመገልጽ ላይ ይገኛሉ።

''ትግላችን ገና አልተገባደደም'' ሲል አንድ የተቃዋሚዎች መሪ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግሯል። ''ፕሬዝደንቱ በእርግጥም ከሥልጣናቸው መልቀቃቸው ሳይረጋገጥ ትግላችንን አናቆምም'' ብሏል።

የፖለቲካ ተንታኝ እና የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃው ባሃቫኒ ፎንሴካ ለሮይተርስ እንደተናገሩት በሲሪላንካ በመጪው ቀናት ምን እንደሚፈጠር ለመተንበይ አስቸጋሪ ሆኗል። በእርግጥም ሁለቱ መሪዎች ከሥልጣናቸው የሚለቁ ከሆነም አስገራሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የፖለቲካ መሪዎች ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ ኢላማው ያደረገ ምክክር እሁድ ዕለት ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሲሪላንካ የሚመሰረት አዲስ መንግሥት ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ መረጋጋት ለማምጣት መስራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።