በሶሪያ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ በተሰነዘረ የድሮን ጥቃት ስድስት ተዋጊዎች ተገደሉ

በአሜሪካ የሚደገፉ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሶሪያ በሚገኘው የአሜሪካ ትልቁ የጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት በኩርዲሽ የሚመሩ እና በአሜሪካ የሚደገፉ ቢያንስ ስድስት ታጣቂዎች ተገድለዋል።

የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይል በምስራቅ ሶሪያ ዴር ኣል ዙር በሚገኘው የኮማንዶ ማሰልጠኛ ላይ ትናንት ሰኞ ማለዳ ጥቃት እንደተፈጸመበት አሳውቋል።

ኃይሉ ይህ ጥቃት የተሰነዘረው በሶሪያ መንግስት ቁጥጥር ስር ባለ እና ለጦር ሰፈሩ ቅርብ ከሆነ አከባቢ በኢራን በሚደገፉ ታጣቂዎች ተፈጽሟል ሲል ከሷል።

በኢራን የሚደገፍ አንድ የታጣቂ ቡድን ጥቃቱን እንደፈጸመ ገልጿል።

በሶሪያ 800 ወታደሮች ያሰማራችው አሜሪካ በሰራዊቷ ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የተሰጠ አስተያየት ወይም ሪፖርት የለም።

አሜሪካ በጆርዳን የጦር ሰፈር በኢራን በሚደገፍ ታጣቂ በተፈጸመ ጥቃት ወታደሮች ከተገደሉባት በኋላ ባለፉት የእረፍት ቀናት የአጸፋ ምላሽ መውሰድ ከጀመረች በኋላ ተመሳሳይ ጥቃት ሲያግጥም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ፔንታገን በሌላ የሶሪያ ክፍል በሚገኝ የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ባለፈው ቅዳሜ ጥቃት መፈጸሙን ለቢቢሲ አረጋግጧል። ሆኖም የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2019 ኢስላሚክ ስቴትን ወይም አይ ኤስ በማሸነፍ የሶሪያ ሰሜን ምስራቃዊ ክፍል በአብዛኛው የተቆጣጠረው የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይል በአሜሪካ በሚመራው ጥምረት ድጋፍ ይደረግለታል። ይህ ኃይል በሰጠው መግለጫ በድሮን ጥቃቱ ስድስት የኮማንዶ ተዋጊዎቹ እንደተገደሉ አሳውቋል።

ቀጥሎም ይህ ጥቃት በኢራን በሚደገፍ ታጣቂ በሶሪያ መንግሥት ቁጥጥር ስር ካለ ስፍራ እንደተፈጸመ ጠቅሷል።

የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይል ጥቃቱን ያወገዘ ሲሆን ለጥቃቱ ምንጭ ተገቢ ምላሽ የመስጠት መብት አለኝ ብሏል።

ከባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ 7 የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይል አባላት እንደተገደሉ እና 18 ደግሞ እንደቆሰሉ መቀመጫውን ዩኬ ያደረገ እና የሶሪያን ጉዳይ የሚከታተል የሰብአዊ መበት ተሟጋች ድርጅት ገልጿል።

በኢራቅ የሚገኘው እና በኢራን እንደሚደገፉ የሚታመኑ ታጣቂ ቡድኖች ዋነኛ አካል የሆነው የኢስላሚክ ኃይል “በአሜሪካ በተወረረው” አካባቢ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

ታጣቂው የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት ከጀመረ ወዲህ በኢራቅ፣ ሶሪያ እና ዮርዳኖስ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች የአሜሪካ ወታደሮችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን እንደፈጸመ ሲገልጽ ቆይቷል።

ይህንን የሚያደርጉት ለፍልስጤም ህዝብ ያላቸው አጋርነት ለመግለጽ እንደሆነም ይናገራሉ።

ከቀናት በፊት በዮርዳኖስ እና ሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ የጦር ሰፈር በተፈጸመ ጥቃት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች ተገድለው ነበር።

ኢራን በነዚህ ጥቃት ውስጥ እጇ እንደሌለበት ብትገልጽም አሜሪካ ጥቃቶቹ የሚፈጸሙበት ድሮን ኢራን ሰራሽ እንደሆኑ ትከሳለች።

ባለፈው አርብ አሜሪካ በኢራቅ እና ሶሪያ ከ85 በላይ ኢላማዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረች ሲሆን እነዚህ ጥቃቶች በዮርዳኖስ ለተገደሉት የአሜሪካ ወታደሮች ምላሽ መሆኑን ትገልጻለች። ቀጥላም ይህ “ገና ጅማሮ” እንደሆነ ኣሳውቃለች።

በሶሪያ በተፈጸመው የአሜሪካ ጥቃት 29 የኢራን ደጋፊ ታጣቂዎች እንደተገደሉ ተገልጿል። በኢራቅ ደግሞ 16 ሰዎች እንደተገደሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ቀጠናው ይህ አይነት ውጥረት ባለበት ሰዓት በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ላይ ያሉት የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ሳዑዲ አረቢያ ይገኛሉ። ኃላፊው የቅርቡ የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት ከጀመረ በኋላ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲጓዙ ይህ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

ብሊንከን ባለፈው ሳምንት ግብጽ፣ ኳታር፣ እስራኤል እና ዌስት ባንክ የተጓዙ ሲሆን የእስራኤል ታጋቾች ተለቀው ሁኔታው የሚረጋጋበት ጉዳይ ላይ መምከራቸው ተዘግቧል።