ፍጥጫ ከሁቲዎች ጋር፡ የየመን አማፂያን ምዕራባውያንን ለመገዳደር ምን ያህል አቅም አላቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የየመን ታጣቂ ቡድን የሆኑት ሁቲዎች የዓለማችን ኃይላን ወታደራዊ ኃይሎችን መገዳደር ይዘዋል።
ታጣቂዎቹ ከአሜሪካ (ዩኤስ)፣ ከዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) አሊያም ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው ያሰቧቸውን በቀይ ባሕር በኩል የሚያቋርጡ የንግድ መርከቦችን ማጥቃት ቀጥለዋል።
ይህ ጥቃት ደግሞ ዓለም አቀፉን ንግድ እያናጋው ነው። በርካታ መርከቦች አማፂያኑን ፍራቻ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀው ዙሪያ ጥምጥም መጓዝ ጀምረዋል።
ሁቲዎች ከአሜሪካ እየደረሰባቸው ያለው የአየር ጥቃት እና የሚሳዔል ድብደባ ግድ የሰጣቸው አይመስልም። ለዚህ ጥቃት ደግሞ በምላሹ አሜሪካ እና ዩኬን እንደሚቀጡ ዝተዋል።
የሁቲ አማፂያን እነማን ናቸው? እንዴትስ ይህን ሁሉ አቅም ሊያዳብሩ ቻሉ? የቀይ ባሕር ዕጣ ፈንታስ ምን ሊሆን ነው?
ሁቲዎች እነማን ናቸው?
ሁቲዎች የየመን አናሳ ጎሳ የሚባሉ ከሰሜናዊ-ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የመጡ ናቸው።
ስማቸውን የወሰዱት ከእንቅስቃሴው መሪ ሁሴን አል-ሁቲ ነው።
ከሃያ ዓመታት በፊት ጀምሮ ከየመን ማዕከላዊ መንግሥት ጋር በርካታ ጊዜያት በጦርነት ሲፋለሙ ቆይተዋል።
በ2014 (እአአ) የየመን ገዢው መደብ በአረብ የፀደይ አመፅ ምክንያት ከሥልጣን ሲፈነቅል ወደ የመን መዲና ሰንዓ አቅንተው ሥልጣን ያዙ።
ሁቲዎች ከሥልጣን የተወገዱትን ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳሌህን አሳደው የገቡበት በመግባት እንደሚገድሏቸው ዝተው ነበር።
ሁቲዎች ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከአረቡ ዓለም እጅግ ደሀ የምትባለው የመን ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ገባች።
በዚህ ጦርነት ምክንያት 150 ሺህ ገደማ ሰዎች እንደተገደሉ የሚገመት ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የየመን ዜጎች የምግብ እርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገደዱ።
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ኃይል ሁቲዎችን ከሥልጣን ለመጣል ለሰባት ዓመታት ያህል በአየር ጥቃት የታገዘ ጦርነት ቢያካሂድም አልተሳካለትም።
ሳዑዲ ይህን እርምጃ ለመውሰድ የወሰነችው ሁቲዎች ከጠላቷ ኢራን ጋር ቁርኝት እንዳላቸው ስትረዳ ነው።
የመካከለኛው ምሥራቅ አጥኚ የሆኑት ሞሐመድ አል-ባሻ “ሁቲዎች የአሸናፊነት መንፈስ ያላቸው ናቸው። ይህን ደግሞ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አስመስክረዋል” ይላሉ።
“ከ2015 እስከ 2022 ሳዑዲ መሩን ጥምር ኃይል እንዴት እንደተቋቋሙት አይተናል። ሳዑዲ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደገፈውን መንግሥት ወደ ሰንዓ መመለስ ትፈልጋለች።”

የፎቶው ባለመብት, Indian Navy
ካለፈው ኅዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ ነው ሁቲዎች ያሏቸወን ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን ተጠቅመው ባብ አል-ማንደብ ባሕረ ገብ መሬት በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ማጥቃት የጀመሩት።
ዋነኛው ዓላማቸው ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያለውን መርከብ ማጥቃት ነው። ይህን የሚያደርጉት ለሐማስ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ነው።
እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ወታደራዊ እርምጃ እስካላቋረጠች ድረስ ጥቃታቸውን እንደማያቆሙ ይናገራሉ።
አሜሪካ እና ዩኬ ከየመን ጋር በሚዋሰነው የቀይ ባሕር ክፍል በኩል የሚያልፉ መርከቦችን መጠበቅ ሲጀምሩ የሁቲ አማፂያን ጥቃታቸውን የአሜሪካ እና የአጋሮቿ የጦር መርከቦች ላይ አደረጉ።
በአንድ ወቅት ከአሜሪካ ባሕር ኃይል ጋር ገጥመው ሦስት ፈጣን ጀልባዎቻቸውን እና 10 አባሎቻቸውን አጥተዋል።
አብዛኞቹ የመናውያን የሱኒ እስልም እና ተከታዮች ቢሆኑም፣ ሁቲዎች ግን የሺዓ ቅርንጫፍ የሆነው የዚያድ እምነት ተከታዮች ናቸው።
ሁቲዎች ምንም እንኳን ከየመን ሕዝብ 15 በመቶውን ብቻ ቢወክሉም የአገሪቱ ትክክለኛ መሪዎች እኛ ነን ብለው ያምናሉ።
ከሌላው የየመን ሕዝብ የሚለያቸው ምንድነው?
ሁቲዎች ጦርነት ይወዳሉ፤ አመፀኛ እና ጨካኝ ናቸው
“. . . ጦርነት ይወዳሉ፤ አመፀኛ እና ጨካኝ ናቸው” የሚሉት ከ2015 -17 (እአአ) በየመን የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር የነበሩት ኤድመንድ ፊተን-ብራውን ናቸው።
“በኤደን እና ታይዝ በጣም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ተመልክቻለሁ። ሁቲዎች ራሳቸውን የምርጦች ምርጥ አድርገው ነው የሚቆጥሩት። በሱኒዎች ላይ በተለይ በማዕከላዊ የመን እና በደቡባዊው ክፍል የሚያደርሱት ጭቆና የተለየ ነው። አንዳንድ ጊዜ ያልተጣቁ ሰዎችን በአልሞ ተኳሽ እየመቱ ይዝናናሉ።”
የተባበሩት መንግሥታት የየመን የእርስ በርስ ጦርነትን ለመቋጨት የራሱን ጥረት አድርጓል። በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና ያለውን የየመን መንግሥት ያስጠለለችው ሳዑዲም ግጭቱን በድርድር ለመፍታት ሞክራለች።
አምባሳደር ኤድመንድ በድርድር ወቅት ከሁቲዎች ጋር ቁጭ ብሎ የማውራት ዕድል ገጥሟቸው ነበር።
“በጣም ከባድ ነበር” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
“ብስጩ ናቸው። ወዲያው ይናደዳሉ። አርፈው አይቀመጡም፤ በዚያ ላይ አርፍደው ነው የሚመጡት። ድርድሩን አቋርጠው መውጣት ይቀናቸዋል። እሹሩሩ በሉን ይላሉ። በዚያ ላይ ጫት ካልቀረበላቸው አይቀመጡም። ድርድሩን ያስተናገዱት ኩዌቶች በጣም ተናደው ነበር።”
ሁቲዎች መርከቦችን ማጥቃት ከጀመሩ በኋላ አሜሪካ እና ዩኬ የአየር ጥቃት ጀምረዋል። በዋና መዲናዋ ደግሞ ፀረ-ምዕራባውያን የተቃውሞ ሰልፎች እየተደረጉ ነው።
“አሜሪካ፣ ዩኬ እና የሳዑዲ መራሹን ኃይል በመቃወም፤ እስራኤልን በመሞገት እና ጋዛን በመደገፍ ሁቲዎች ዕውቅና እያተረፉ ነው” የሚሉት አል-ባሻ ናቸው።
ነገር ግን ይላሉ ምሑሩ የዛሬይቱ የመን እጅግ የተከፋፈለች ናት። በሰሜን ምሥራቅ የመን ማሪብ እና ታይዝ አካባቢዎች የፀረ-ሁቲ እንቅስቃሴ አለ። ሁቲዎች በነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ ቢካሄድ የሚያሸንፉ አይመስልም ይላሉ።
አምባሳደሩ እንደሚሉት ደግሞ ሁቲዎች ሕዝቡን እያስፈራሩ አውራ ጎዳና እያስወጡ ነው።
“ተቃውሞ ይጠራሉ፤ ሥራ መግባት አይፈቀድም ይላሉ፤ ሰዎች መቅረት እንደማይችሉ ይናገራሉ። ከቁጥጥራቸው ውጭ የሆኑ ቦታዎች ዘንድ እጅግ ይጠላሉ።”
ሁቲዎች ከበቂ በላይ የሆነ የድሮን እና ሌሎች አቅርቦቶች አሏቸው። አብዛኛውን አቅርቦት የሚያገኙት ከኢራን ነው። የጦር መሣሪያዎቹ ከኦማን ጋር ባለው ድንበር በኩል በትናንሽ ጀልባዎች ተጭነው ነው የመን የሚገቡት።
መጨረሻው ምን ይሆን?
ሁቲዎች የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ከመመከት ወደኋላ የሚሉ አይደሉም።
አምባሳደሩ “በፍፁም ሊሸነፉ አይሹም” ይላሉ።
“በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ ድል አድርገናል ብለው ሊያውጁ ይችላሉ። ዓላማችንን አሳክተናል ይላሉ። ኢራን የሁቲ አማፂያን ድርጊት የእስላማዊ ሪፐብሊኳን አደጋ ላይ እየጣለ ነው ብላ የምታስብ ከሆነ ሁቲዎች ቀስ ብለው እንዲሸሹ ሊያደርጉ ትቸላለች።”
ለጊዜው የቀይ ባሕር ነገር ግን ቁርጡ አልታወቀም።
ምንም እንኳ አሜሪካ ሁቲዎች አለን የሚሉትን የሚሳዔል ማስወንጨፊያዎች ብትመታም፣ የሚመጣባቸውን ጥቃት እየተቋቋሙ ቀጥለዋል።
በርካታ የጦር መሣሪያዎች አሏቸው። ቀጥሎ ደግሞ ከመሬት በሚወነጨፍ ሚሳዔል የምዕራባውያን አውሮፕላኖችን ሊመቱ ይችላሉ።
በዚህም ወደፊት በባሕር ብቻ ሳይሆን በአየርም ቀይ ባሕር እና ኤደን ባሕረ ሰላጤን አቋርጦ መሄድ በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል።












