ቀይ ባሕርን ያወከውን የሁቲዎች ጥቃት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ይሳካ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ባለፉት ሳምንታት በቀይ ባሕር በኩል በመርከቦች ጭነት ማጓጓዝ ፈታኝ ሆኗል። በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጽያን በሰው አልባ አውሮፕላን እና በሚሳኤል መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።
ታጣቂዎቹ በተጨማሪም በጀልባ እና በሄሊኮፕተርም ጥቃት አድርሰዋል።
አብዛኛውን የመን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች “በጋዛ እና በዌስት ባንክ ላሉ ፍልስጤማውያን ወንድሞች” ድጋፍ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ወደ እስራኤል የሚጓዙ የንግድ መርከቦችን ዒላማ እንዳደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ባጣራው መረጃ መሠረት ሁቲዎች ጥቃት የሰነዘሩት በደቡባዊ ቀይ ባሕር ነው። ይህም በየመን ባሕር ዳርቻ በባብ ኤል-ማንዳብ መተላለፊያ ላይ ነው።
ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚጓዙ መርከቦች ላይም ጥቃት ተሰንዝሯል።
ነገር ግን በጥቃቱ ዒላማቸውን የመቱት የተወሰኑት ብቻ ናቸው። ከእነዚህም መካከል እአአ ጥር 17 የተፈጸመው ጥቃት ይገኝበታል።
በዚህም በአሜሪካ መርከብ ላይ ነበር ጥቃቱ የተቃጣው። ነገር ግን መርከቡ በሁቲዎች ድሮን ጎኑ ላይ ቢመታም ጉዞውን ቀጥሏል።
ጥቃቱን የሚያሳይ ምሥል ያነሳው የሕንድ የባሕር ተዋጊ መርከብ ነበር። ይህም የሁቲዎችን ጥቃት ለመመከት ያለውን ትብብር ማሳያም ነው።
የሁቲዎች ጥቃት
የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ነው ሁቲዎች የሚጠቀሙት።
በተለይ ደግሞ ሚሳኤሎች እና ድሮኖችን ይጠቀማሉ።
ቃስፍ-1 እና ቃስፍ-2 ድሮኖች አሏቸው። እነዚህም እስከ 200 ኪሎ ሜትር የሚወነጨፉ ናቸው። እስከ 1,800 ኪሎ ሜትር የሚምዘገዘጉ መሣሪያዎችም አሏቸው። በ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ መርከብን ማጥቃት ይችላሉ ማለት ነው።
ሁቲዎች ትናንሽ ጀልባዎችን በመጠቀም መርከቦች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
ሄሊኮፕተር በመጠቀም መርከብ ላይ ጥቃት የሰነዘሩበትም ወቅት ነበር።
በሄሊኮፕተር መርከብ ላይ የወረዱት ጥቃት አድራሾች አንድ መርከብን አግተዋል። ጋላክሲ ሊደር የተባለው መርከብ አሁንም በየመን ባሕር ዳርቻ እንደተያዘ ነው።
የየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከአገሪቱ መንግሥት የተወሰዱ መሣሪያዎች በሁቲዎች እጅ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፣ ከምሥራቅ እስያ በሲቪሎች አማካይነት የተገኙም መሣሪያዎች አሏቸው።
አብዛኞቹ ዘመናዊ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ግን ከኢራን እንደተገኙ በስፋት ይነገራል።
አሜሪካ እንዳለችው፣ ከየመን ወደ ኢራን በዓሣ ማስገሪያ ጀልባ ተጭኖ እየተጓዘ የነበረ የሚሳኤል እና የአየር መቃወሚያ ይዛለች።
ወታደራዊ ተንታኞች እንዳሉት ኤምቪ ቤሻድ የተባለ የኢራን መርከብ ሁቲዎች ዒላማ እንዲመቱ እያገዘ ነው።
ቀድሞ ማጓጓዣ የነበረው መርከብ አሁን የደኅንነት መቆጣጠሪያ መሆኑን ያስረዳሉ።
ቢቢሲ ከኢራን መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

የፎቶው ባለመብት, INDIAN NAVY
ዓለም አቀፍ ምላሽ
በቀጠናው የደኅንነት ቡድን የመሩት ክሪስ ፋረል እንደሚሉት፣ የተለያየ ቁሳቁስ የጫኑ መርከቦች ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢሆንም ከአየር የሚደረግ ጥቃትን መከላከል የሚያስችል መሣሪያ ግን የላቸውም።
ይህ በቀይ ባሕር በኩል የሚያቋርጡ “የንግድ መርከቦች ከረዥም ጊዜ በኋላ የገጠማቸው ከባድ ችግር ነው” ይላሉ።
ዓለም አቀፍ ምላሽ ከመጠናከሩ ጋር በተያያዘ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በጋራ በየመን የሁቲ አማጽያን ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽመዋል።
በዚህም ሁለቱ አገራት የአማጽያኑን ወታደራዊ አቅም ለማዳከም ያለመ ጥቃት ነበር የሰነዘሩት።
ሆኖም ግን የየመንን ሰፊ ተራራማ አካባቢዎች ሁቲዎች ይቆጣጠራሉ።
መደበቅ የሚችሉትም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ወታደራዊ ተንታኞች ይናገራሉ።
ባለፈው ታኅሣሥ በአሜሪካ የሚመራ ወታደራዊ ጥምረት የንግድ መርከቦችን ለመጠበቅ እንደሚሠራ ተገልጿል።
በዚህም ቀይ ባሕርን የመቆጣጠር ሥራ የሚሠሩ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም ለዚህ ተግባር መርከብ እንደምታቀርብ አስታውቃለች።
ከአሜሪካ ጥምረት ውጪ እንደ ፈረንሳይ ያሉ አገራትም በቀጠናው መቆጣጠሪያ ጣቢያ አላቸው።
የአሜሪካ የባሕር ኃይል ካፕቴን ብራድሊ ማርቲን እንደሚሉት የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮችን ማስተባበር ፈታኝ ነው።
ባሕሩ ላይ የሚከናወነውን ጥበቃ የሚያካሂዱትን መርከቦቹ ነዳጅ ሞልቶ መሣሪያ ማስታጠቅም ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል።
ከሁቲዎች የሚተኮሱትን እንደ ሲ ቫይፐር ያሉ ሚሳኤሎችን መከላከል በሚሊዮን ዶላር የሚያስወጣ ነው።
በተቃራኒው ሁቲዎች የድሮን ጥቃት ለመፈጸም የሚያወጡት በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ነው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የመርከቦች ጉዞ መስተጓጎል
በርካታ ተቋማት መርከባቸው በቀይ ባሕር እንዳይጓዝ እያደረጉ ነው።
ይህ ማለት ደግሞ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በተባለው የአፍሪካ ዳርቻ መንገድ ለመጓዝ ከፍተኛ ወጪን ያወጣሉ ማለት ነው።
ለጅሙን የውቅያኖስ ላይ ዙሪያ ጥምጥም መንገድ በማስቀረት በቀይ ባሕር ለመጓዝ የመረጡ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ አማራጮች እየተጠቀሙ ነው።
አንደኛው መንገድ የመርከቦችን አቅጣጫ የሚጠቁም መከታተያ ሥርዓት መዘርጋት ነው። ይህም ኤአይኤስ ትራኪንግ ይባላለል።
የመከታተያ ሥርዓቱ የሁቲ አማጽያን መርከቦቹን እንዳያገኙ የሚያግዝ ነው።
አንዳንድ መርከቦች ደግሞ “ከእስራኤል ጋር ግንኙነት የለንም” ብለው መርከባቸው ላይ ይጽፋሉ።
መርከቡ ላይ “ታጣቂዎች አሉ” ወይም “ሠራተኞቹ ቻይናውያን ብቻ ናቸው” ብለው የሚጽፉም አሉ።
አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም በቅርቡ ጥቃት ቢፈጽሙም ሁቲዎች ጉዳት የማድረስ አቅማቸው እንዳለ መሆኑን ወታደራዊ ተንታኙ ያስረዳሉ።
“ጥቃቱን መቀነስ ይቻላል። ነገር ግን ችግሩ የሚፈታው ለጋዛ ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ ሲሰጥ ነው። መርከቦችን በመከላከል ብቻ ጥቃቱን ማቆም አይቻልም” ይላሉ።













