አትላንቲክ ውቅያኖስን ለማቋረጥ የሞከሩ ጥንዶች ሞተው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, sarahjustinepackwood.com
አትላንቲክ ውቅያኖስን በጀልባ ለማቋረጥ ጉዞ ጀምረው የነበሩት ጥንዶች ሕይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው ተገኘ።
ጥንዶቹ ለመጨረሻ ጊዜ ከታዩ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ከባሕር ዳርቻ በሕይወት አድን አነስተኛ ጀልባ ውስጥ አስክሬናቸው መገኘቱ ተገልጿል።
ብሪታኒያዊቷ ሳራ ፓክዉድ እና ካናዳዊው ባለቤቷ ብሬት ክሊበሪ አድራሻቸው መጥፋቱ ሪፖርት የተደገው ሰኔ 11/2016 ዓ.ም. ነበር።
ጥንዶቹ የ21 ቀናት የባሕር ላይ ጉዞ በማድረግ ከ3 ሺህ 228 ኪሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው አዞሬስ ለማቅናት አቅደው ነበር።
ይሁን እንጂ ጥንዶቹ ሕይወታቸው አልፎ በካናዳዋ ኖቫ ስኮሺያ ግዛት አቅራቢያ በሚገኝ ደሴት ላይ አስክሬናቸው ተገኝቷል።
ጥንዶቹ ጉዟቸውን የጀመሩት 13 ሜትር ርዝመት ባላበት ጀልባ ቢሆንም አስክሬናቸው የተገኘው በአደጋ ጊዜ ጥቅም ላይ በሚውል አነስተኛ ጀልባ ላይ ነው።
የጥንዶቹ አትላንቲክ ወቅያኖስን በጀልባ የማቋረጥ ህልም ተጨናግፎ ሕይወታቸውን እንዴት እንዳሳጣቸው እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የካናዳ ፖሊስ ትናንት እሑድ ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም. ምርመራው መቀጠሉን ገልጿል።
መርማሪዎች ለጥንዶቹ ሞት ትክክለኛ ምንክያት እያጣሩ ቢሆንም ጀልባቸው ከዕቃ ጫኝ መርከብ ጋር ሳይጋጭ አይቀርም የሚል መላምት አለ።

የፎቶው ባለመብት, YouTube/TherosAdventures
ሳልትዋየር የተባለ ካናዳ የዜና ድረ-ገጽ መርማሪዎች ዕቃ ጫኝ ግዙፍ መርከብ የጥንዶቹን መርከብ ሳያውቅ ሳይገጭ አይቀርም የሚል መላምት አላቸው ብሏል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ጠንዶቹም ግጭቱ ሲፈጠር በታችኛው የጀልባቸው ክፍል ውስጥ ሆነው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ ብሏል።
የካናዳ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች እና ወታደራዊ አውሮፕላኖች ግጭት ደርሶባት ሊሆን ይችላል የተባለችውን ጀልባ እስካሁን አላገኙም።

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Theros Sailing Adventure
ቴሮስ አድቬንቸርስ በተባለው የዩቲዩብ ቻናላቸው ላይ በተለጠፈው ቪዲዮ ላይ ጥንዶቹ ግሪን ኦዲሴይ ተብሎ የተሰየመው ጉዟቸው በፀሀይ ኃይል፣ በባትሪዎች እና ከመኪና ተወስዶ በተሠራ የኤሌክትሪክ ሞተር ኃይል ጀልባቸው እንደሚንቀሳቀስ አብራርተዋል።
"ነዳጅ ሳታቃጥሉ መጓዝ እንደሚቻል ለማሳየት የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው" ሲሉ ክሊበሪ ተናግረው ነበር።
ፓክዉድ ደግሞ “እስካሁን በሕይወታችን ትልቁ ጉዞ ሳይሆን አይቀርም” ብለው ነበር ።
ጥንዶቹ እአአ በ2015 ለንደን ውስጥ በአጋጣሚ ነበር የተገናኙት። ክሊበሪ ጡረታ የወጡ መሐንዲስ ሲሆኑ ለእህታቸው ኩላሊት ለመለገስ በዝግጅት ላይ ነበሩ።
ጥንዶቹ እአአ 2016 ነበር በጀልባቸው ላይ ካናዳ ውስጥ ጋብቻቸውን የፈጸሙት።












