የባይደን ከምርጫ ፉክክር መውጣት ለትራምፕ፣ ለዴሞክራቶች እና ለካማላ ሃሪስ ምን ማለት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በስተመጨረሻም ባይደን እጅ ሰጥተዋል።
ምንም እንኳ እርጅናው ቢጫጫናቸውም፤ ብዙ የቅርብ አጋሮቻቸው ይቅርብዎ ቢሏቸውም ባይደን እኔን ከምርጫው የሚያስወጣኝ ‘አንድ ፈጣሪ’ ብቻ ነው ሲሉ ነበር።
ይሁን እንጂ በመጨረሻ እጅ ሰጥተው፤ “ለፓርቲዬ እና ለአገሬ ስል” እራሴን ከምርጫው አግልያለሁ ብለዋል።
ለመሆኑ የባይደን ከምርጫ መውጣት ለካማላ ሃሪስ፣ ለዴሞክራቶች እና ለዶናልድ ትራምፕ ምን ማለት ነው?
ሃሪስ
ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ የጆ ባይደንን ድጋፍ ማግኘታቸው የዴሞክራቶች ዕጩ ሆነው የመቅረባቸውን ዕድል በከፈተኛ ሁኔታ ከፍ የሚያደርግ ነው።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከአራት ዓመት በፊት ካማላ ሃሪስን ምክትላቸው አድርገው መምረጣቸው ትክክለኛ ውሳኔዬ ነበር ሲሉ አሞካሽተዋል።
ካማላም የፕሬዝዳንቱን ድጋፍ ማግኘታቸውን በጸጋ እንደሚቀበሉት ተናግረው የፓርቲውን ዕጩነት ለማግኘት የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ አንተኒ ዙከር ግን ሃሪስ የማሸነፋቸው ነገር አጠራጣሪ ቢሆንም ዴሞክራቶች ዕጩ አድርገው ከመቀበል ወጪ አማራጭ ያላቸው አይመስለኝም ይላል።
በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ከባይደን ቀጥሎ የአገሪቱ መሪ ካማላ ናቸው። ዴሞክራቶችም ቢሆኑ በአሜሪካ ታሪክ ጥቁር ሴት ፕሬዝዳንት መሪ የምትሆንበትን አማራጭ የሚነጥቁ ከሆነ ለስማቸው ጥሩ አይሆንም። ስለዚህ ካማላ በምርጫው ሊቀርቡ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ ካማላ ለዴሞክራቶቸ አደጋ ናቸው። ትራምፕን ሊገዳደሩ ይችሉ እንደሆን በበርካቶች ላይ ጥያቄ አለ።
የሕዝብ አስተያየቶች ሃሪስ ከትራምፕ አንጻር ያላቸው ተቀባይነት ዝቅ ያለ መሆኑን ያሳያሉ።
ከዚህ ተጨማሪ ሃሪስ አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ተፈትነው ትችት የደረሰባቸው ምክትል መሪ ናቸው።
በጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት በአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር ላይ ላለው የስደተኞች ቀውስ መፍትሄ እንዲያበጁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ የወሰዷቸው እርምጃዎች ውጤታማ አልነበሩም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዴሞክራቶች
በቀጣይ ወር ዴሞክራቶች በቺካጎ አጠቃላይ ጉባኤ ያደርጋሉ። በዚህ ጉባኤ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን በትክክል መገመት ባይቻልም ፓርቲው ከካማላ ጎን እንደሚሆን ይጠበቃል።
አንተኒ፤ ዴሞክራቶች ካማላን ዕጩ አድርገው ማቅረባቸው አደጋ ቢሆንም አሁን ላይ ያላቸው የተሻለ አማራጭ ካማላ ናቸው ይላል።
ይሁን እንጂ ካማላ ፓርቲውን አንድ ማድረግ የሚሳናቸው ከሆነ፤ በቀጣይ ሳምንታት ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች የፓርቲው ዕጩ ለመሆን በአደባባይ እና ከመድረክ ጀርባ ቅስቀሳዎቸን የሚያደርጉ ይሆናል።
ስለዚህ በዴሞክራቶች ጉባኤ ዕለት ያልተጠበቀ ዕጩ ወደፊት ሊወጣ ይችላል።
ሪፐብሊካኖች
አንተኒ እንደሚለው ሪፐብሊካኖች ዒላማ አድርገው ሲተቹ የቆዩት የዴሞክራቶች ዕጩ የነበሩትን ጆ ባይደንን ነው።
ይህ ማለት ትራምፕ ባለፉት ወራት ሲተቹ እና ሲያጣጥሉ የቆዩት በምርጫው ፉክክር ላይ የማይቅርብ ዕጩን ነበር። ዶናልድ ትራምፕ እና የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው ለወራት ባይደንን በተለይ ከዕድሜያቸው ጋር ተያይዞ የመጣባቸውን ድክመት ትኩረት አድርገው ሲተቹ ቆይተዋል።
አሁን ዴሞክራቶች ወጣት እና አዲስ በሆነ ዕጩ ይመለሳሉ። ሪፓብሊካኖች አዲስ የሚመጣውን ዕጩ ድክመት ለይተው መተቸት የሚጠብቃቸው ኃላፊነት ነው።
አንተኒ እንደሚለው ካማላ ሃሪስ የዴሞክራት ዕጩ ሆነው የሚመጡ ከሆነ፤ ሪፐብሊካኖች ምክትል ፕሬዝዳንቷን የወቅቱ የወደቀ መንግሥት አስተዳደር አካል አድርገው አጥብቀው ሊተቹ ይችላሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕዝብ አስተያየቶች ዶናልድ ትራምፕ ከባይደንም ሆነ ከካማላ ሃሪስ የተሻለ ተቀባይነት አላቸው።












