የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዝዳንት ለመሆን እየተፎካከሩ ያሉት ካማላ ሃሪስ ማን ናቸው?

ካማላ ሃሪስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ በገጠማቸው አካላዊ እና አእምሯዊ መዳከም ምክንያት በድጋሚ ለመመረጥ ከሚደረገው ፉክክር እንዲወጡ ሲደረግባቸው የነበረውን ጫና በመጨረሻ ተቀብለውታል።

ባይደን ከምርጫው ለመውጣት መወሰናቸውን ተከትሎ ምክትል ፕሬዚዳንታቸው ካማላ ሃሪስ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የ59 ዓመቷን የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላን ሃሪስ ለፕሬዝዳንትነት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በሚደረገው ፉክክር የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ እንዲሆኑ ከፓርቲው አባላት ድጋፍን አግኝተዋል።

ሆኖም ግን የምክትል ፕሬዝዳንቷ የተቀባይነት ደረጃ ዝቅተኛ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ባገለገሉበት ወቅትም የአገሪቱ መሪ ሆነው ለመመረጥ ምን ያህል ብቃት አሳይተዋል የሚለው ላይ ጥርጣሬ አለ።

ካማላ ሃሪስ ወደ ፖለቲካው እንዴት ገቡ?

ካማላ ሃሪስ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት፣ ጥቁር እና የእስያ ዝርያ ያላቸው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በአውሮፓውያኑ 2020 ታሪክ ሠሩ።

ከአንድ ዓመት በኋላ፣ በ2021 ፕሬዚዳንት ባይደን የህክምና ምርመራ ሲያደርጉ ለ75 ደቂቃ ያህልም የአሜሪካ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።

በኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ የተወለዱት ካማላ ወላጆቻቸው ስደተኞች ሲሆኑ፣ እናታቸው ሕንዳዊት፣ አባታቸው ደግሞ ጃማይካዊ ናቸው።

አባት እና እናታቸው የተፋቱት የአምስት ዓመት ሕጻን እያሉ ሲሆን፣ ያሳደጓቸውም የካንሰር ተመራማሪ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት እናቷ ሻይማላ ጎፓላን ሃሪስ ናቸው።

እናታቸው እሷን እና እህታቸውን ማያን በኦክላንድ በነበረው ጥቁር ማኅበረሰብ ውስጥ እንዲቀላቀሉ አድርገው እንዳሳደጓቸው ያስረዳሉ።

“እናቴ ሁለት ጥቁር ልጆችን እንደምታሳድግ በደንብ ተረድታው ነበር” ሲሉም ካማላ ሃሪስ የሕይወት ታሪካቸውን በሚተርከው ‘ዘ ትሩዝስ ዊ ሆልድ’ የሚል ርዕስ በተሰጠው መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።

“የምትኖርበት አገር [አሜሪካ] እኔን እና እህቴን ማያን እንደ ጥቁር ልጆች እንደሚያየን ስለምታውቅም በራሳችን መተማመን እና ኩሩ ጥቁር ሴቶች እንድንሆን ነው በጽናት ያሳደገችን” ይላሉ።

ካማላ በአሜሪካ ታሪካዊው እና ስመ ጥር በሆነው ሃዋርድ የጥቁር ዩኒቨርስቲ ነው ትምህርታቸውን የተከታተሉት።

ካማላ ሃሪስ በልጅነታቸው ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Kamala Harris

የምስሉ መግለጫ, ካማላ ሃሪስ በልጅነታቸው ወቅት

በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ወቅት የደቡብ አፍሪካን ጨቋኝ አፓርታይድ ሥርዓትን ለመገርሰስ በሚደረገው እና የአሜሪካ የጥቁሮች ጭቆና ላይ በሚደረጉ ትግል ላይ ተሳትፎ ነበራቸው።

እንዲሁም በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የጥብቅና ዲግሪያቸውን የተቀበሉ ሲሆን፣ በግዛቲቷ በተለያዩ ዐቃቤ ሕግ ቢሮዎች ውስጥ ሠርተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2010 የካሊፎርኒያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆኑ። ከስድስት ዓመታት በኋላም የአሜሪካ የምክር ቤት አባል (ሴናተር) ሆነው ተመረጡ።

ከአራት ዓመት በፊት በነበረው ምርጫ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሆነው ለመመረጥ ዘመቻ ቢጀምሩም ገና በጅማሮው ላይ ነው ውድድሩን አቋርጠው የወጡት።

ሆኖም ጆ ባይደን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሆነው ከቀረቡ በኋላ እሳቸውን ምክትላቸው እንዲሆኑ በባይደን ተመረጡ።

ካማላ “ብልህ፣ ጠንካራ፣ ልምድ ያላት እና በትግል ታሪኳ የምትታወቅ ናት” ሲሉ ፕሬዚዳንት ባይደን መስክረውላቸዋል።

ባይደን እና ካማላ ሃሪስ በአንድ ላይ ሆነውም የወቅቱን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስን በማሸነፍ ተመረጡ።

ምንም እንኳን ካማላ የመሪነቱን ስፍራ ባይይዙም የእሳቸው ጥቁር ሴት መሆን ለድላቸው ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ይነገራል። ለዚህም ዲሞክራቶችን አሸናፊ ያደረጋቸውን 90 በመቶ የጥቁር ሴቶችን ድምጽ በካማላ ምክንያት አግኝተዋል ተብሏል።

ካማላ ሃሪስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካማላ ሃሪስ በምክትል ፕሬዚዳንታቸው ምን አከናወኑ?

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ሥልጣናቸው የሴኔቱ ፕሬዚዳንት ያደረጋቸው ካማላ፣ ይህም ረቂቅ ሕጎች እኩል ድምጽ በሚያገኙበት ወቅት የመለያ ድምጽ በመስጠት ወሳኝ ሚና ነበራቸው።

ያንን ሥልጣናቸውን 32 ጊዜ የተጠቀሙት ካማላ፣ በአሜሪካ ታሪክም ይህንን ያደረጉ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆንም ክብረ ወሰን ጨብጠዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደንም ምክትል ፕሬዚዳንቷ ስለነበራቸው ሚና ሲናገሩ “ካማላ የመጨረሻውን ድምጽ የምትሰጠው እሷ ናት። ግምቶችን አትቀበልም፤ ከባባድ ጥያቄዎችን ትጠይቃለች” ብለው ነበር።

አሜሪካ ጽንስ ማቋረጥን በአገር አቀፍ ደረጃ መብት ያረጋገጠችበት 'ሮ ቨርሰስ ዌድ' የተሰኘው ሕግ መቀልበስን ተከትሎ የሥነ ተዋልዶ ጤናን መብት ለማረጋገጥ ከሁለት ዓመት በፊት በተለያዩ ግዛቶች ያደረጉት ጉብኝት ለካማላ የበለጠ ዕውቅናን አስገኝቶላቸዋል።

ሆኖም ካማላ ሃሪስ በምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው ያገኙት ተቀባይነት ዝቅተኛ እንደሆነ የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች ያመለክታሉ።

'ፋይቭ ሰርቲ ኤይት' የተሰኘው ተቋም ባሰባሰው የሕዝብ አስተያየት 51 በመቶ አሜሪካውያን ካማላ በሥልጣን ዘመናቸው ያሳዩት ብቃት ዝቅተኛ እንደሆነ ያምናሉ። ጥሩ ብቃት አሳይተዋል ያሏቸው 37 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የዚሁ ተቋም መረጃ ያሳያል።

ይህም የሆነው ፕሬዚዳንት ባይደን ለካማላ የሰጧቸው ዋና ተግባር በአሜሪካ ደቡባዊ ድንበር ላይ ያለውን የፍልሰት መጠን መቀነስ ሲሆን፣ ይህንንም ማድረግ ባለመቻላቸው ሊሆን እንደሚችል የቢቢሲ የአሜሪካ ልዩ ዘጋቢ ካቲ ኬይ ታስረዳለች።

ካማላ ሃሪስ ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ካማላ ጆ ባይደንን በዕጩነት ስለመተካት ምን ይላሉ?

አምስት ዲሞክራት የምክር ቤት አባላት የ81 ዓመቱ ጆ ባይደን በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ከሚካሄደው የፓርቲው ፕሬዚዳንታዊ ዕጩነት ራሳቸውን እንዲያገሉ በግልጽ ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሃዮ ግዛት ተወካይ የሆኑት ቲም ራያን፣ ካማላ ሃሪስ በዕጩነት እንዲተኩ ሃሳብ አቅርበዋል።

“የእኛ የተሻሉት ዕጩ ካማላ ሃሪስ ናቸው ብዬ አምናለሁ። የሃሪስ ዕጩነት ባለፈው ካየነው ጆ ባይደን የበለጠ አደጋ ነው ለሚሉ በእውነታ ላይ እየኖሩ አይደሉም” ሲሉ ኒውስዊክ በተባለው መጽሄት አስፍረዋል።

የካሊፎርኒያ ተወካይ የሆኑት አዳም ሺፍ በበኩላቸው ካማላ “ገራሚ ፕሬዚዳንት ትሆናለች። ትራምፕንም ታሸንፋለች” ብለዋል።

የቅርብ ጊዜ የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች እንደሚጠቁሙት ካማላ ከሪፐብሊካኑ ዕጩ ትራምፕ በኩል ከፍተኛ ፉክክር ቢገጥማቸውም ከባይደን የተሻሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው።

በቅርቡ ሲኤንኤን በሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት 43 በመቶ መራጮች ባይደን ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የሚፈልጉ ሲሆን፣ 49 በመቶው ትራምፕን ይደግፋሉ። ሆኖም ካማላ ሐሪስ ዕጩ ቢሆኑ 45 በመቶ ድጋፍ የሚያገኙ ሲሆን፣ 47 በመቶ ደግሞ ለትራምፕ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ጆ ባይደንን እንዲተኩ ሌሎች የቀረቡ ባለሥልጣናት የካሊፎርኒያው አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሰም፣ የሚቺጋን አስተዳዳሪ ግሬቸን ዊትመር እና የትራንስፖርት መሥሪያ ቤት ኃላፊው ፒት በትጊየግ ናቸው።

ሆኖም ካማላ ለፕሬዚዳንት ባይደን ያላቸውን ድጋፍ እየገለጹ ሲሆን “ጆ ባይደን ዕጯችን ነው። ከዚህ ቀደም ትራምፕን አሸንፈነዋል፤ እንደገናም እናሸንፈዋለን። በቃ!” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።