ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው የታዩት ባይደን ጫና ቢበዛባቸውም ከፕሬዝዳንታዊ ፉክክሩ አልወጣም አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ባለፈው ሳምንት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በነበረ የምርጫ ክርክር ሃሳባቸውን ለመግለጽ ሲሳናቸው የታዩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከምርጫው ፉክክር ሊወጡ ነው የሚሉ ዘገባዎች መጨመራቸውን ተከትሎ ዴሞክራቶችን እና ድጋፊዎቻቸውን ለማረጋጋት ሞክረዋል።
ባይደን በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ በሚካሄደው ምርጫ ፓርቲው ዕጩ አድርጎ ይተካቸዋል ወይ የሚል ግምት እየተነሳባቸው ከሚገኙት ከምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ጋር በዋይት ሃውስ በዝግ ምሳ በልተዋል።
በኋላም ባይደን በምርጫው እንደሚቀጥሉ እና ሃሪስ ደግሞ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ለዲሞክራሲ ፓርቲ የምርጫ ዘመቻ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል።
ባይደን “እኔ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ነኝ። ማንም የሚገፋኝ የለም። ከምርጫው ፉክክር ውጭ አልሆንም” ሲሉ መናገራቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተመሳሳይ መልዕክት ከጥቂት ሰአታት በኋላ በባይደን-ሃሪስ የምርጫ ዘመቻ የገቢ ማሰባሰቢያ ኢሜይል ላይ በድጋሚ ሰፍሮ ተልኳል። ባይደን በኢሜይሉ ላይ “በፉክክሩ ውስጥ እንዳለሁ በተቻለኝ መጠን በግልፅ እና በቀላል ቋንቋ መናገር እፈልጋለሁ። እስከ መጨረሻው በዚህ ውድድር ውስጥ ነኝ” ብለዋል።
የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ከትራምፕ ጋር ባደረጉት የምርጫ ክርክር ያሳዩትን አቋም ተከትሎ በዘመቻው ይቀጥላሉ ወይ የሚሉ ጥያቄዎች ተበራክተዋል።
ለኃላፊነቱ ብቁ በመሆናቸው እና ምርጫውን በማሸነፋቸው ዙሪያ በዲሞክራቲክ ዘንድ ስጋት ቀስቅሷል።
ከክርክሩ በኋላ በኒውዮርክ ታይምስ በከተናወነ የሕዝብ አስተያየት ትራምፕ በስድስት ነጥብ ልዩነት ቀዳሚ ሆነዋል።
በቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ በተከናወነ ሌላ የህዝብ አስተያየት ደግሞ ትራምፕ ወሳኝ በሆኑ ግዛቶች በሦስት ነጥብ እየመሩ መሆናቸውን ጠቁሟል። የቀድሞው ፕሬዝዳንት በአገር አቀፍ ደረጃ እየመሩ መሆናቸውንም አመልክቷል።
አንዳንድ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ገንዘብ ለጋሾች እና የሕግ አውጭ አካላት ፕሬዝዳንቱ ከምርጫው እንዲወጡ በይፋ ጠይቀዋል። ህንዳዊ-አሜሪካዊ ራምሽ ካፑር እአአ ከ1988 ጀምሮ ለዴሞክራቶች ገንዘብ ማሰባሰብያዎችን አዘጋጅተዋል።
ካፑር ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ኃላፊነቱን ለሌላ ሰው የሚሰጥበት ጊዜው አሁን ይመስለኛል። ፍላጎት እንዳለው ባውቅም ተፈጥሮን መዋጋት አይቻልም” ብለዋል።
በኮንግረስ ውስጥ ያሉ ሁለት ዲሞክራቶች የፓርቲው መሪ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። የአሪዞና ተወካይ ራውል ግሪጃልቫ ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት ለዴሞክራቶች “ሌላ ሰው የመመልከቻ” ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።
ዋይት ሃውስ እና የባይደን የምርጫ ዘመቻ ሰዎች ጉዳዩን በንቃት እየገመገሙ ነው የሚሉ ሪፖርቶችን ውድቅ አድርገዋል። ትራምፕን በመጪው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኒውዮርክ ታይምስ እና ሲኤንኤን ረቡዕ እንደዘገቡት ከሆነ ባይደን በምርጫው ውስጥ መቆየት ስለመቻላቸው እየገመገሙ መሆናቸውን ለባልደረባቸው ተናግሯል።
ሁለቱም ዘገባዎች ፕሬዚዳንቱ በድጋሚ የመመረጥ ዕድላቸው አደጋ ላይ መሆኑን እንደሚያውቁ ለአጋራቸው እንደነገሩት እና ከኤቢሲ ኒውስ ጋር የሚያደርጉት ቃለ መጠይቅ እና በዊስኮንሲን የሚደረገው የምርጫ ዘመቻ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ የሆኑት ካሪን ዣን ፒየር ባይደን ለውድድሩ ያላቸውን ብቃት በተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች ሳይቀርብላቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሪፖርቶቹን “ፍፁም ውሸት” ሲሉ ቃል አቀባዩ ውድቅ አድርገውታል።
ከምርጫው ሊወጡ ነው የሚሉት ሪፖርቶች እውነት እንዳልሆኑ ተናግረው “ፕሬዚዳንቱን ጠየቅናቸው [እና] በቀጥታ ‘አይ፣ ፍፁም ውሸት ነው’ ብለዋል። ይህ በቀጥታ የሚመጣው ከእሱ ነው” ብለዋል።
ባይደን ረቡዕ ዕለት የካሊፎርኒያውን ጋቪን ኒውሶምን እና የሚቺጋኑን ግሬቼን ዊትመርን (ባይደን ከውድድሩ ከወጡ ሁለቱም ሊተኳቸው እንደሚችሉ ተጠቁሟል) ጨምሮ 20 ዲሞክራቲክ ገዥዎችን አገኝተዋል።
የሜሪላንድ ገዥ ዌስ ሙር ከስብሰባው በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ፕሬዝዳንቱ ሁል ጊዜ ደጋፊያችን ናቸው። እኛም እንደግፋቸዋለን” ብለዋል።
የኒውዮርክ ገዥ ካቲ ሆቹል ፕሬዝዳንቱን ያገኟቸው ገዥዎች ድጋፋቸውን እንደሰጧቸው እና ባይደን “በምርጫው ለማሸነፍ ዝግጁ ነኝ” ሲሉ ቃል ገብተዋል ብለዋል።
ካማላ ሃሪስም ፕሬዝዳንቱን ሊተኩ የሚችሉ ሰው እንደሆነ ይታሰባል። የ 59 ዓመቷ ሃሪስ አነስተኛ ድጋፍ ቢኖራቸውም፤ ከምርጫው ክርክር ወዲህ ድጋፋቸው በዴሞክራቶች ዘንድ ጨምሯል።












