ጆ ባይደን ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ፉክክር እራሳቸውን አገለሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት ለመመረጥ ሲያካሂዱ የነበረውን የምርጫ ዘመቻ ማቋረጣቸውን ይፋ አደረጉ።
በበርካታ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና በቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝዳንቶች ከምርጫው ፉክክር እንዲወጡ ሲወተወቱ የነበሩት ባይደን አሁን ከምርጫው ለመውጣት ወስነዋል።
ጆ ባይደን በድጋሚ ለመመረጥ ሲያደርጉ የነበረውን የምርጫ ዘመቻ እንዲያበቃ የወሰኑት “ለፓርቲዬ እና ለአገሬ የተሻለ ጥቅም ነው” በማለት ገልጸዋል።
ምርጫው ሊካሄድ አራት ወራት ብቻ ሲቀሩት ነው ባይደን ለተጨማሪ አራት ዓመታት በዋይት ሐውስ ለመቆየት ከሚያደረገው የምርጫ ፉክክር እራሳቸውን ያገለሉት።
ባይደን በሶሻል ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰራጩት ደብዳቤ ላይ የአሜሪካ ፐሬዝዳንት ሆነው ማገልገላቸው የሕይወት ዘመናቸው ትልቁ ክብር መሆኑን ገልጸዋል።
ባይደን ምክትላቸውን ካማላ ሃሪስን “ድንቅ አጋር” በማለት የወደሷቸው ሲሆን፣ ሃሪስ በእርሳቸው ቦታ ለፕሬዝዳንትነት እንዲቀርቡ ድጋፋቸውን አሳውቀዋል።
ባይደን በመግለጫቸው ላይ “እምነቱን ለጣለብኝ ለአሜሪካ ሕዝብ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” በማለት፤ “ዛሬም ሆነ ሁልጊዜ አሜሪካውያን ከተባበሩ ምንም ነገር ማድረግ አያቅታቸውም ብዬ አምናለሁ። እኛ የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች [ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ] መሆናችንን ብቻ ማስታወስ ነው ያለብን” ሲሉ አስበዋል።
አሁን ከምርጫው ለመውጣት መወሰናቸውን በተመለከተ በሚቀጥለው ሳምንት ለአሜሪካ ሕዝብ ንግግር እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።
ባይደን ከቀናት በፊት በኮቪድ መያዛቸው ከተረጋጋጠ በኋላ መኖሪያቸው ወደሚገኝበት ዴላዌር ግዛት ሄደው የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን አርብ ዕለት ደግሞ “በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ምርጫ ዘመቻው” ለመመለስ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።
ከተለያዩ ወገኖች ከምርጫው እንዲወጡ ጫና ሲደረግባቸው የሰነበቱት ባይደን ከአንድ ሳምንት በፊት ከምርጫው የሚያስወጣቸው “ሁሉን ማድረግ የሚችለው ጌታ” ብቻ ነው ብለው ነበር። ኋላ ላይ ግን የጤና ዕክል ከገጠማቸው ከውድድሩ መውጣትን ሊያስቡበት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እርጅና የተጫጫናቸው የ81 ዓመቱ አዛወንት ፕሬዝዳንት ባይደን በቀጣይ ምርጫ ዴሞክራቶችን ወክለው እንዳይቀርቡ ከፓርቲ አባሎቻቸው ተደጋጋሚ ጥሪዎች ሲቀርብላቸው መቆየታቸው ይታወቃል።
ቃላቶችን በአግባቡ ሰካክተው ሃሳባቸውን ለመግለጽ ሲቸገሩ የሚታዩት ጆ ባይደን ምንም እንኳ ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብላቸው ኅዳር 2017 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ የፓርቲያቸው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ሆነው ከመሳተፍ ወደኋላ እንደማይሉ ሲገልጹ ነበር።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፣ የቬርሞንት ግዛት ዴሞክራት ሴናተር ፒተር ዌልች፣ ለዴሞክራቶች ከፍተኛ ገንዘብ ከሚለግሱት መካከል አንዱ የሆነው ዕውቁ የሆሊዉድ ተዋናይ ጆርጅ ክሎኒ እንዲሁ ባይደንን “ምርጫው ይቅርብዎት” ሲሉ ነበር።
አሁን ባይደን ከተለያየ አቅጣጫ ሲደረግባቸው የነበረውን ጫና ተቀብለው የምርጫ ዘመቻቸውን ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።
ዴሞክራቶች በቀጣይ ነሐሴ ወር አጠቃላይ ስብሰባ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ባይደንን የሚተካ ዕጩ በዚሁ ወቅት በማሳወቅ ፓርቲያቸውን በመወከል ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የሚፎካከር ዕጩ ያቀርባሉ።












