በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ 30 ሺህ ቤተሰብ አፈናቀለ

የፎቶው ባለመብት, Aar Mohamed/Save the Children
ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ወደ 30 ሺህ ቤተሰብ መፈናቀሉን የሕጻናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ቺልድረን) አስታወቀ።
ድርጅቱ እንዳለው በሁለቱ አገሮች ከተፈናቀሉ በሺህ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ሌላ 50 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ጎርፉ 10ሺህ የቁም እንሰሳትን የወሰደ ሲሆን 24ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብልንም እንዳልነበረ አድርጎ አውድሟል።
ድንገተኛ እና ከፍተኛ ዝናብ በእነዚህ የኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ገጠር አካባቢዎች የጣለው ለሦስት ዓመታት ዝናብ ሳይዘንብ ድርቅ ሆኖ ከቆየ በኋላ ነው።
ይህም በመሆኑ ዝናብ መጣሉ ያመጣውን ተስፋ እንዲመክን አድርጎታል ብሏል ድርጅቱ።
የሕጻናት አድን ድርጅቱ እንደሚለው ይህ ምስቅልቅ ያለ የአየር ሁኔታ የሚያሳየው አፍሪካ ምን ያህል በየአር ንብረት ለውጥ እየተናጠች እንደሆነ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥ በአካባቢው የሚያደርሰው ጉዳትም ከፍተኛ እንደሆነ ማሳያ ነው ብሏል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ በእነዚህ አካባቢዎች በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ በድምሩ 25 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ለረሀብ ተጋልጧል።
2 ሚሊዮን 500ሺህ ሕጻናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል።
በዚህ ዓመት በመላው ዓለም 345 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እጥረት ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተባበሩት መንግሥታት መረጃ ይህ አሐዝ ከ2020 ከነበረው ቁጥር ከእጥፍ በላይ ነው።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች አፈሩ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፣ ዝናብ ወደ ውስጥ ሰርጎ እንዳይገባም አድርጎታል። ይህ ደግሞ ሰብል እንዳይበቅል ምክንያት ሆኗል።
በዚህ የተነሳ ብዙ ሕዝብ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ፈተና ሆኖበታል።
በአካባቢዎቹ በሕይወት ለመቆየት የሚረዱ የተመጣጠኑ ምግቦችን ማግኘት አዳጋች በመሆኑ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በቀላሉ ለበሽታ እየተዳረጉና እየሞቱ እንደሆነም ድርጅቱ አብራርቷል።
ሕጻናቱ ለዕድገት አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ባለማግኘታቸው የመቀንጨር እና በአእምሮ ጤና እና በአካል ብቁና ንቁ አለመሆንንም አስከትሏል።
የሕጻናት አድን ድርጅት የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቃል አቀባይ ማላማ ምዊላ ጉዳዩ ልብ የሚሰብር ነው ብለዋል።
“በሐዘን ላይ ሐዘን ነው የሆነው፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ልጆች እና ቤተሰቦቻቸው ዝናቡን ለሦስት ዓመት ሲጠብቁት ነበር። ዝናቡ ሲዘንብ የዘሯትን ሰብል ይዞባቸው ሄደ። ጎርፉ የቀሩትን ቀንድ ከብቶች ጠራርጎ ወሰዳቸው” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ40 ዓመታት ውስጥ በሶማሊያ ያልታየ ከፍተኛ ረሀብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር።
ይህም የሆነው ለአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ድርቅ ሆኖ በመቆየቱ ነበር።
ከዚያ ቀደም ብሎ በ2011 በአካባቢው በነበረ ግጭት፣ ድርቅ እና የዋጋ ንረት 260ሺህ ሰዎች መሞታቸው አይዘነጋም።












