እስራኤል በሊባኖስና ፍልስጤም ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃት ሰነዘረች

እስራኤል በሐማስ ይዞታዎች ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃት ሰንዝራለች

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በሐማስ ይዞታዎች ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃት ሰንዝራለች

የእስራኤል መከላከያ በፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ሰነዘረ።

ጥቃቱ ከሊባኖስ ወደ እስራኤል የተተኮሱ ተከታታይ ሮኬቶችን ተከትሎ የመጣ የአጸፋ እርምጃ ነው።

የእሰራኤል መከላከያ እንዳለው በዚህ የአየር ጥቃት በደቡብ ሊባኖስ የሚገኝ የ‘አሸባሪ’ው ሐማስ የጦር ቀጠና ክፉኛ ተደቁሷል።

ከሰሞኑ የእስራኤል ፖሊስ የአል አቅሳ መስጂድ ላይ ወረራ ከፈጸመ በኋላ በአካባቢው ውጥረት ነግሶ ሰንብቷል።

አል አቅሳ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ሦስተኛው ቅዱስ ስፍራ ነው።

ይህም በመሆኑ የእስራኤል ፖሊስ መስጂድ ቅጥር በመዝለቁ በአካባቢው አገራት ጭምር ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

ሮኬቶቹ ሲተኮሱ በሊባኖስ የነበሩት የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሐኒያህ ጥቃቱን ተከትሎ “ፍልስጤማዊያን በእስራኤል ወራሪዎች ሲደፈሩ እጃችንን አጣጥፈን አንመለከትም” ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ሐማስ በሊባኖስ የመሸገበትን ስፍራና የወታደራዊ መሠረተ ልማቱን ማውደሙን አስታውቋል።

ሐማስ ከሊባኖስ የተተኮሱት ሮኬቶች ዙርያ መረጃ የለኝም ይላል።

እስራኤል በሰሜን በኩል ጎረቤት አገር ሊባኖስ በኩል የተሰነዘረውን የሮኬት ጥቃት በ17 ዓመታት ከፍተኛው ነው ብላለች።

ከ37 ሮኬቶች አብዛኛዎቹን ማክሸፏንም ተናግራለች። 6 ሮኬቶች በሕንጻዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋልም ብላለች።

ይህን ተከትሎ የእሰራኤል የጦር አውሮፕላኖች በጋዛ ሰርጥ ጥቃት ያደረሱ ሲሆን በ10 ደቂቃ ብቻ 20 ሚሳኤሎች የተለያዩ ቦታዎችን አጥቅተዋል።

የፍልስጤም ታጣቂቆችም ሮኬቶችን ወደ ደቡብ እስራኤል የተኮሱ ሲሆን በአካባቢው የማስጠንቀቂያ ደውሎች ተሰምተዋል።

የእስራኤል ጄቶች የምድር ውስጥ የጦር መሣሪያ ማምረቻ ስፍራን ማውደማቸውን ኢየሩሳሌም ፖስት መከላከያውን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በእስራኤል የድንበር ከተማ ሽሎሚ የሮኬት ጥቃቱ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት አድርሷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል የድንበር ከተማ ሽሎሚ የሮኬት ጥቃቱ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት አድርሷል

እስራኤል ከዚህ ቀደም በኢስላሚክ ጂሃድ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ካደረሰች ከነሐሴ 2022 ወዲህ ይህ ጥቃት ትልቁ ነው ተብሏል።

ይህ ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ አስቸኳይ የደኀንነት ጉዳይ ስብሰባ ከጠሩ በኋላ የተሰነዘረ ነው።

ናታያንያሁ በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ጠላቶቻችን ሁሉ እኛን በተዳፈሩ ጊዜ ከባድ ዋጋን ይከፍላሉ” ብለዋል።

የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ሚካቲ እስራኤል ሉዓላዊ ግዛት በመጣስ የሰነዘረችውን ጥቃት አውግዘዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል በሊባኖስ ‘ሁኔታዎች አስፈሪ ናቸው’ ያለ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ነገሩን ከማባባስ እንዲቆጠቡ መክሯል።