በአርባ ምንጭ ጫሞ ሐይቅ ላይ ከሰጠሙት ሰዎች መካከል የሰባቱ አስከሬን ተገኘ

ቱሪስቶች በጫሞ ሐይቅ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቱሪስቶች በጫሞ ሐይቅ ላይ

ቅዳሜ መጋቢት 16/2015 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን በምትገኘው አርባ ምንጭ ውስጥ ጫሞ ሐይቅ ላይ በጀልባ ሲጓዙ ሰጥመው የደረሱበት ካልታወቀ ሰዎች መካከል የሰባቱ ሰዎች አስክሬን መገኘቱ ፖሊስ አስታውቋል።

በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ሐይቁ ውስጥ ሰጥመው ከሁለት ቀናት በላይ ሳይገኙ ከቆዩት ሰዎች መካከል የሰባቱ አስከሬን መገኘቱን የዞኑ ፖሊስ አስታውቋል።

የጋሞ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደገፌ ደበላን ጠቅሶ የዞኑ ኮምዩኒኬሽን እንደገለጸው ሰኞ ረፋድ ላይ ከተገኘው አስከሬን በተጨማሪ የስድስቱ ሰዎች አስከሬን ሰኞ መጋቢት 18/2015 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ተገኝቷል።

የፖሊስ ምክትል አዛዡ እንደገለጹት የፀጥታ ኃይሎች እና የጀልባ አሽከርካሪዎች ለሦስት ቀናት ባደረጉት የተጠናከረ ፍለጋ የአምስት ወንዶች እና የሁለት ሴቶች አስከሬን መገኘቱን ተናግረው፣ የቀረውን የአንድ ሰው አስከሬን ለማግኘት ፍለጋው መቀጠሉን ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር አብረሃም ቡሄ ስምንት ሰዎችን ጭና ስትጓዝ የነበረችው ጀልባ የሰጠመችው በድንገተኛ በተከሰተ ማዕበል ምንክያት መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“አልፎ አልፎ ክረምት ላይ ማዕበል ያጋጥማል። ከዚህ ውጪ ለጀልባዋ መስጠም ሌላ ምንስዔ ካለ እየተጣራ ነው” ብለዋል አዛዡ።

ምክትል ኢንስፔክተር አብረሃም ጀልባዋ ካሳፈረቻቸው ሰዎች በተጨማሪ የተለያዩ ጭነቶች ይዛ እንደነበረ መረጃው እንዳላቸው ገልጸው፤ ለጀልባዋ መስጠም ምክንያቱ ይህ ስለመሆኑ እየተጣራ ነው ብለዋል።

ከፖሊስ አዛዡ በተጨማሪ የአርባ ምንጭ ከተማ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን እንዳለው፣ ጀልባዋ ከአቅም በላይ ሰው፣ እንስሳ እና ዕቃ ጭና የነበረችው ጀልባ በማዕበል ምክንያት ጫሞ ሐይቅ ላይ ሰጥማለች ብሏል።

ጀልባዋ የሰጠመችበትን ስፍራ የሚያሳይ ካርታ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጋሞ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ አልጎ እንዳሉት ጀልባዋ ከስምንቱ ሰዎች በተጨማሪ በሬ፣ ቡላ እና ሽንኩርት ጭና ነበር ስለማለታቸው የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ገልጿል።

በጀልባዋ ላይ ስድስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶችን ሲጓዙ እንደነበሩ የገለጹት ምክትል ኢንስፔክተር አብረሃም ከስምንቱ ሰዎች መካከል እስከ ሰኞ መጋቢት 19/2015 ዓ.ም. እኩለ ቀን ድረስ የአንድ ሰው አስክሬን መገኘቱን ገልፈው ነበር።

በአደጋው የሰመጡ ሰዎችን ፈልጎ ለማግኘት የሚደረገው ፍለጋ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፣ አደጋው ከደረሰ ሁለት ቀናት ያለፉ በመሆናቸው በሕይወት የሚተርፍ ሰው የማግኘቱ ነገር አጠጣሪ ሆኖ ቆይቷል።

“ከዚህ በኋላ ሰዎችን በሕይወት የማግኘት ዕደሉ ጠባብ ነው” ያሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ፤ “ጊዜ ይወስድ ይሆናል እንጂ የሰዎችን አስክሬን ማግኘታችን አይርም” ብለዋል።

በጫሞ ሐይቅ ላይ አደገኛ አዞ መኖሩን ያስታወሱት የፖሊስ አዛዡ፤ ነገር ግን የሰዎቹ አስክሬን በአዞ የመበላቱ ዕድል ጠባብ መሆኑን ይገልጻሉ።

“ምንም አንኳ በሳይንስ ባይረጋገጥም በአካባቢው ማኅብረሰብ ዘንድ አዞ በሕይወት የሌላ ነገር አይበል የሚል እምነት አለ። ከዚህ በተጨማሪም አደጋው የደረሰው በሐይቁ መካከለኛ ክፍል ላይ ነው። አዞዎች ያሉት ደግሞ የሐይቁ ዳርቻ ላይ ነው። ስለዚህ አስከሬኖቹ ይገኛሉ፣ የትም አይሄድም” በማለት ተናግረዋል።

በጀልባዋ ተሳፍረው የነበሩት ሰዎች ነጋዴዎች መሆናቸውን እና ከአማሮ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ እየተጓዙ እንደነበረም ተናግረዋል።

“ባለን መረጃ መሠረት አንደኛው የጅልባ ባለቤት ልጅ ነው። ሌላኛው የጀልባ ኦፕሬተር ሲሆን የተቀሩት ስድስቱ ነጋዴዎች ናቸው” ብለዋል።

ምክትል ኢንስፔክተሩ “ትኩረታችን አስክሬን መፈለግ ነው። ፖሊሶች እና አሳ አስጋሪዎች በጀልባዎች አሰማርተን አሰሳ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

በአካባቢው በመሰል አደጋ የሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ይህ የመጀመሪያው አለመሆኑን የተናገሩት ምክትል ኢንስፔክተር አብረሃም “የሟቾች ቁጥር አንደዚህ ባይበዛም አደጋ ያጋጥማል” ብለዋል።