በቱኒዚያ የባሕር ዳርቻ ጀልባዎች ሰጥመው ቢያንስ 29 ስደተኞች ሞቱ

ስደተኞችን የጫነች ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቱኒዚያ የባሕር ዳርቻ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ጀልባዎች ሰጥመው ቢያንስ 29 ስደተኞች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት የመጡ ናቸው የተባሉት ስደተኞቹ አውሮፓዊቷ አገር ጣሊያን ለመግባት የሜዴትራኒያን ባሕርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ነው አደጋው የደረሰው።

በቅርቡ በቱኒዚያ የባሕር ዳርቻ እንዲህ ዓይነት አደጋ ሲያጋጥም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ባለፉት አራት ቀናትም ሌሎች አምስት ጀልባዎች ሰጥመዋል።

ይህ የተሰማው ቱኒዚያ በቂ መረጃ የሌላቸው የአፍሪካ ስደተኞችን ለማስቆም ዘመቻ ከጀመረች በኋላ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በላምፔዱሳ ደሴት ያሉ የጣሊያን ባለሥልጣናት ባለፉት 24 ሰዓታት ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው ከፍተኛ ነው የተባለ 2 ሺህ 500 ስደተኞች በሥፍራው ከደረሱ በኋላ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆዮርጂያ ሜሎኒም አውሮፓ በባሕር ዳርቻዋ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የስደተኞች ማዕበል ልትጥለቀለቅ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።

ቱኒዚያ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ለሚፈልጉ ስደተኞች መናኻሪያ ናት።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ከሆነ በዚህ ዓመት በጣሊያን የባህር ዳርቻ የደረሱ ቢያንስ 12 ሺህ ስደተኞች ከቱኒዚያ የተነሱ ናቸው። ይህ ቁጥር በባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት 1 ሺህ 300 ነበር።

ሆኖም የቱኒዚያ የባሕር ዳርቻ ጠባቂዎች እንደሚሉት ስደተኞች ባሕር እንዳያቋርጡ ለማስቆም እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑንና በዚህም ባለፉት አራት ቀናት ወደ አውሮፓ ሲያመሩ የነበሩ 80 አነስተኛ ጀልባዎችን ማገዳቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ባለፈው ወር ባደረጉት አነጋጋሪ ንግግራቸው፣ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ስደተኞችን፣ በአገሪቷ ውስጥ ወንጀል በመፈፀም እና የሕዝብ ስጋት በመሆን ከሰዋል።

የፕሬዝዳንት ካይስ ሳኢድ አስተያየት በአፍሪካ ኅብረት የተተቸ ሲሆን በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችም “ዘረኛ የጥላቻ ንግግር” ሲሉ አውግዘውታል።

የፕሬዝዳንቱ አስተያየትም በቱኒዚያ የሚኖሩ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ስደተኞች ስጋት እንዲያድርባቸው አድርጓል። አንዳንዶችም ዘረኛ የሆኑ ድርጊቶች መበራከታቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

በዚህም እንደ አይቮሪይ ኮስት እና ጊኒ ያሉ አገራት በአገሪቷ ባለው ችግር ዜጎቻቸውን ከቱኒዚያ እየመለሱ ነው።

ቱኒዚያ በድህነት ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር ስትሆን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር ያለው ድርድር በመቋረጡ ምጣኔ ሃብቷ ቀውስ ገጥሞታል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ቱኒዚያ ከአይኤምኤፍ ጋር በአስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባትም አስጠንቅቀዋል።