የቱኒዝያው ፕሬዝዳንት ከሰሃራ በታች በመጡ አፍሪካውያን ስደተኞች ላይ ለምን አነጣጠሩ?

አፍሪካዊ ስደተኛ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በአንድ አገር ቀውስ ሲያጋጥም ስደተኞችን ወይም የሕዝብ ቁጥራቸው አናሳ የሆኑ ማኅበረሰቦችን ተጠያቂ ማድረግ የተለመደ ነው።

ይሄ በተለይም በልወደድ ባይ ፖለቲከኞች ወይም በምርጫ ለማሸነፍ በሚሞክሩ አምባገነን መንግሥታትም ተግባራዊ ሲደረግም ይታያል።

የቱኒዝያው ፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት የመጡ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ንግግር ማድረጋቸውም ከዚህ ጋር የተያያዘ ይመስላል።

ፕሬዝዳንቱ በዋነኝነት አረብ እና ሙስሊም የሆነችውን የሰሜን አፍሪካዋን አገራቸውን የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ለመለወጥ ሴራ ተጎንጉኗል ሲሉም ተናገሩ።

ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካውያን ወደ ቱኒዝያ የሚሰደዱት የዚህ ሴራ አካል ነው ይላሉ።

የታሪክ መዛግብት በግልጽ እንደሚያሳዩት እንደነዚህ አይነት ንግግሮች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ብጥብጥ እና ሁከት የሚመሩ ናቸው። በቱኒዝያም የሆነው ይኽው ነው።

የፕሬዝዳንቱን ንግግር ተከትሎም ጥቁር አፍሪካውያን ላይ ያነጣጠረ ጥቃትም ደርሷል። አንዳንዶቹም ይህንን ጥቃት በመፍራት ከቤታቸውም አልወጡም።

ላለፉት አምስት ዓመታት በቱኒዝያ ትምህርቷን ስትከታተል የቆየችው እና ከደቡብብ አፍሪካ የመጣችው ተማሪ፣ የፕሬዝዳንቱ ንግግር በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ጥቁር አፍሪካውያን ላይ በአሳዛኝ ሁኔታ ተጽእኖ እንዳደረሰባቸው ተናግራለች።

ግለሰቧ ለቢቢሲ አፍሪካ ዴይሊ ፖድካስት እንደተናገረችው የአንዳንዶች ቤት በእሳት የተቃጠለ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ እንደተደበደቡ እንዲሁም በርካቶች በአገሪቱ ውስጥ ደኅንነት እንደማይሰማቸው ገልጻለች።

ይህንንም ተከትሎ በርካታ ጥቁር አፍሪካውያን ወደ የኤምባሲያቸው በማምራት ወደ የአገራቸው መልሱን እያሉ ይገኛሉ።

የቱኒዝያው ፕሬዚዳንት ካይስ ሰኢድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቱኒዚያ መንግሥት የፕሬዝዳንቱ ንግግር በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ በሚገቡ ላይ እንጂ፣ በሕጋዊነት በአገሪቱ የሚገኙትን አይመለከትም በማለት ተከራክሯል።

12 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ቱኒዝያ ወደ 20 ሺህ የሚገመቱ ከሰሃራ በታች የመጡ ስደተኞች እንዳሉ ይገመታል።

የቱኒዝያ የሰብዓዊ መብቶች ተመራማሪ ኬንዛ ቤን አዙዝ “ይህ የሕጋዊነት ወይም የሕገወጥነት ጉዳይ ሳይሆን፣ በዚህች አገር ጥቁር ሆኖ የመገኘት ጉዳይ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከአገሪቱ ሕዝብ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሆኑት ጥቁር ቱኒዝያውያን በቆዳቸው ቀለም ምክንያት መድልዎ ይደርስባቸዋል ሲሉም አክለዋል።

ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት የሚመጡ ስደተኞች የሜዲትራንያን ባሕርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት በሚል የሰሜን አፍሪካ አገራትን መሸጋገሪያ አድርገዋቸዋል። የስደተኞቹም ጉዳይ በሰሜን አፍሪካ እና በአውሮፓ መንግሥታት መካከል መወዛገቢያ ሆኖም ቆይቷል።

በዚህ ወቅት አዲስ የሆነው ጉዳይ ፕሬዝዳንቱ ችግሩን ለማሳየት የተጠቀሙበት ቋንቋ ነው። በፕሬዝዳንቱ ላይ የተነሱ ትችቶች በጠነከሩበት በአሁኑ ወቅት ፍርሃትን እንዲሁም ብሔራዊ ስሜትን ለመቀስቀስ የታቀደ ይመስላል። በዚህም የሕዝቡን ስሜት ወደ ሌላ አቅጣጫ በማስቀየር የማስተባበር ሁኔታም ታይቶበታል።

ቱኒዝያ በአሁኑ ወቅት በምጣኔ ሃብት ቀውስ ላይ ትገኛለች። ፕሬዝዳንት ዜን ኤል ኤቤዲን ቤን አሊ በአውሮፓውያኑ 2011 ከሥልጣናቸው መገርሰሳቸውን ተከትሎ የመጣው ፖለቲካዊ ቀውስ ምጣኔ ሃብቱንም በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል።

ለምሳሌ የቱሪዝሙን ዘርፍ ብናይ በሽብር ጥቃቶች፣ ከዚያም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ክፉኛ ተሽመድምዷል።

ፖለቲካውም ፕሬዝዳንቱ በሚፈልጉበት መንገድ እየሄደ አይደለም።

አፍሪካውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ፕሬዝዳንቱ በአውሮፓውያኑ 2021 ምክር ቤቱን ከበተኑ በኋላ አገሪቱን ወደ መረጋጋት እና ብልጽግና ለመምራት ፍኖተ ካርታ ቢያውጁም ቱኒዝያ ከፍተኛ ውድቀት ገጥሟታል።

አዲስ ሕገ መንግሥት እንዲያረቁ ያወቀሩት ኮሚቴ ባቀረበው ረቂቅ ላይ ስር ነቀል ለውጥ በመደረጉ ኮሚቴው ለፕሬዝዳንቱ ያለውን ድጋፍ አንስቷል።

ለሕግ አውጪው እና ለፍትህ አካላት የተሰጡ ኃላፊነቶችን በመጠቅለል ሥልጣኑን በሙሉ በፕሬዝዳንቱ እጅ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።

እንዲሁም በረቂቁ ላይ ሕዝባዊ ምክክር በኢንተርኔት ቢደረግም አገሪቷ ካሏት ዘጠኝ ሚሊዮን መራጮች መካከል ጥቂት መቶ ሺዎች ብቻ የተሳተፉበት ሆኗል።

የሕዝብ አስተያየት መስጫውንም 70 በመቶ የሚሆኑ ብቁ መራጮች አንሳተፍም ብለዋል።

ዕቅዳቸው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በተካሄደው የፓርላማ ምርጫም የተሻለ ውጤት አላመጣም።

ለምርጫ የወጣው ሕዝብ በጣም ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ 11 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ ፕሬዝዳንቱ ሕዝቡ ፓርላማ አይፈልግም እንዲሉ መነሻ ሆኗቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሚዲያው ላይ፣ በፖለቲከኞች ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ሙሰኛ ናቸው እንዲሁም በሥልጣን ባልገዋል ይሏቸዋል። ራሳቸውንም ሥልጣን የማይሹ እና የአገሪቱም አዳኝ አድርገው ነው የሚያዩት።

ቱኒዝያ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ከሚመጡ ስደተኞች የህልውና ስጋት ተጋርጦባታል ማለታቸው በሌሎች ችግሮች ላይ ያለውን ትኩረት ለጊዜው ቀልብሶታል።

እንዲህ አይነት ፀረ ስደተኛ ንግግር የሚቀነቀነው በፕሬዝዳንቱ ብቻ አይደለም፣ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊ የሆነው የቱኒዝያ ናሺናሊስት ፓርቲም ተመሳሳይ ትርክትን ይከተላል።

በአውሮፓ ውስጥ እንዳሉት ቀኝ አክራሪዎች እና ፀረ ስደተኞች ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ጥቁር ስደተኞች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡም ዘመቻ ሲያደርግ ቆይቷል።

ፓርቲው ከሰሃራ በታች የሚመጡ አፍሪካውያን ሰፋሪዎች እንደሆኑ እና የቱኒዝያውያንንም መሬት መንጠቃቸው እንደማይቀርም ሲቀሰቅስ ይሰማል።

የተቃወሞ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዶ ነበር

የብሔርተኝነት ካርድ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የፖለቲካ እስልምና ተጽእኖ ለመመከት አመቺ ዘዴ ሆኖም ብቅ ብሏል። ዓለም አቀፍ ርዕዮተ ዓለም የሆነው የፖለቲካ እስልምና የቱኒዝያ ደጋፊዎች ፕሬዚዳንቱን የሚቃወሙ ፓርቲዎችን ይወክላል።

ፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎቻቸውን “ከሃዲ” በማለት በተደጋጋሚ ሲያወግዟቸው ይሰማል።

ጽንፈኝነት በቱኒዝያ ብቻ የተወሰነ አይደለም በሌሎች አገራትም ያለ እንጂ።

ፕሬዝዳንት ሰኢድ የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እስላማዊ ርዕዮተ ዓለም በሕብረተሰቡ እና በፖለቲካው ላይ ያለውን ተፅእኖ ለማዳከም እየወሰዱት ያለውን ስትራቴጂ የተከተሉ ይመስላሉ።

ከአገር በፊት እምነትን የሚያስቀድመውን የእስልምና እምነት ተሻጋሪ ርዕዮተ ዓለምንም ለመመከት ብሔራዊ ማንነትን የማጎልበት ስሜትን እንደገና ለማነቃቃት ጥረት አድርገዋል።

እንደ ቱኒዝያ በግብፅም ጥቁር አፍሪካውያን ስደተኞች መኖራቸውን እንደ ስጋት የሚቆጥሩ ጽንፈኛ ብሔርተኞች የሚያሰሟቸው ትርክቶች እየተበራከቱ መጥተዋል።

በቱኒዝያ በጥቁሮች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በተመለከተ ምላሽ የሰጠው የግብፁ ናሺናሊስት ሪቫይቫል እንቅስቃሴ ለፕሬዝዳንቱ ያለውን ድጋፍም ገልጿል።

ቡድኑ ግብፅ በሱዳናውያን እና ከሰሃራ በታች በሚመጡ ስደተኞች ተጨናንቃለች ሲልም ባለሥልጣናቱ ፍልሰቱን እንዲያስቆሙ እና ስደተኞቹንም እንዲያባርሩ ጠይቋል።

በተጨማሪም በቅርቡ ጥቁር አሜሪካዊው ኮሜዲያን ኬቨን ሃርት በግብፅ ሊያደርግ ያቀደውን ትርኢት በመቃወም ዘመቻ አካሂደዋል።

ለዚህም የሰጡት ምክንያት አርቲስቱ ጥንታዊ ግብፅ የጥቁር ሥልጣኔ ናት ለሚለው የ‘አፍሮ ሴንትሪዝም’ ድጋፍ ሰጥቷል በሚል ነው። ይህም ሁኔታ እንደ ሌሎች ቱኒዝያውያን ራሳቸውን ከሰሃራ በታች ካሉ አፍሪካውያን ማንነት ጋር ለመለየት የሚሞክሩ በርካታ ግብፃውያንን አስቆጥቷል።

የኮሜዲያኑ ፕሮግራም ግብፃውያንን ከባህላቸው እና ከመሬታቸው ለማፈናቀል የተጠነሰሰ የሴራ አካል ተደርጎ ታይቷል። ትርዒቱ የተሰረዘ ሲሆን አዘጋጆቹም ምክንያቱን አልገለጹም። ይህም ሁኔታ ለግብፅ አክራሪ ብሔርተኞች እንደ ድል ተቆጥሯል።

ዓለም አቀፉን ቁጣ ተከትሎ የቱኒዝያው ፕሬዚዳንት ንግግራቸውን ለማለሳለስ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። በዚህም ቱኒዝያ አፍሪካዊት አገር መሆኗን፣ እንዲሁም ከጥቁር አፍሪካውያን ጋር የተጋቡ ዘመዶች አሉኝም ብለዋል።

በተጨማሪም መንግሥት በቱኒዝያው ውስጥ ያሉ ጥቁር አፍሪካውያንን ደኅንነት ለማስጠበቅ አንዳንድ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል። ለምሳሌም ያህል የቅሬታ ስልኮች መቀበል እንዲሁም የቪዛ ቆይታቸው ጊዜ ያለፈበትን ቅጣት መሰረዝ ይገኝበታል።

ሆኖም ይህ የመንግሥት እርምጃ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ነው ተብሏል። የአገሪቱ ገጽታ ላይመለስ ጠልሽቷል።