በሺዎች የሚቆጠሩ ቱኒዚያውያን ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እንዲለቁ አደባባይ ወጥተው ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, MOHAMED MESSARA/EPA-EFE/REX/Shutterstock
በሺዎች የሚቆጠሩ ቱኒዚያውያን የፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ የሥልጣን ዘመን እንዲያከትም ለመጠየቅ አደባባይ ወጡ።
ቱኒዚያውያኑ በዋና መዲናዋ ቱኒዝ የተቃውሞ ሰልፉን ያካሄዱት አገሪቷ በአስከፊ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው።
ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ላይ ከወጡበት 2021 ጀምሮ ሲደግፏቸው የነበሩ ቱኒዚያውያን ጭምር በአገሪቷ ባለው የምጣኔ ሃብት ቀውስ ስጋታቸው እየጨመረ መጥቷል።
ተቃዋሚዎቹ ከ2011ዱ ሕዝባዊ አመጽ በኋላ የተገኘውን ዲሞክራሲያዊ ጉዞ እየቀለበሱ ነው ሲሉም አውግዘዋቸዋል።
ተቃውሞው የተካሄደው የቀድሞው አምባገነን መሪ ዚነ አል-አቢዲን ቤን አሊ በግዞት እንዲወጡ ከተደረጉ ከ12 ዓመታት በኋላ ነው።
አምባገነኑን መሪ ከሥልጣን ያስወገደው የቱኒዚያ ሕዝባዊ አመጽ እንደ ስኬት ቢቆጠርም በምጣኔ ሃብትም ሆነ በፖለቲካ ረገድ መረጋጋት አላመጣም።
አገሪቷ ያለባት ብድር እየጨመረ በመምጣቱ ቡና፣ ወተት እና ስኳርን ጨምሮ መሠረታዊ ፍጆታዎችን ከውጭ ለማስገባት ተቸግራለች።
ተቃዋሚዎቹ ቱኒዚያን ወደ በአንድ ሰው የሚመራ ፍጹም አምባገነናዊነት ለመመለስ ሞክረዋል ሲሉ ፕሬዝዳቱን ይከሷቸዋል።
አንድ ተቃዋሚ መንግሥት እስካሁን ድረስ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማግኘት አልቻለም ሲሉ መፈንቅለ መንግሥቱ ረሃብና ድህነት እንዳመጣባቸው ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
በቱኒዝ ማዕከላዊ ሃቢብ ቦርጊባ አደባባይ ከተሰባሰቡት ተቃዋሚዎች መካከል አንዱ የሆነው የ34 ዓመቱ አኑዋር አሊ “ቱኒዚያ በታሪኳ አደገኛ በተባለ ጊዜ ውስጥ እያለፈች ነው። ፕሬዝዳንቱ ሁሉንም ሥልጣን ተቆጣጥሮ ዲሞክራሲ የሚባል የለም። ምጣኔ ሃብቱም እየወደቀ ነው። ይህን እያየን ዝም አንልም” ብሏል።
በዋና መዲናዋ የተካሄደው ተቃውሞ በሁለት የተለያዩ ተቃዋሚ ቡድኖች የተዘጋጀ ሲሆን ግጭቶችን ለመከላከል በውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አካባቢ በርካታ የጸጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ይታያሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ተቃዋሚዎቹ ፕሬዝዳንት ሰኢድ ሁሉንም በሚባል ደረጃ ሥልጣን መቆጣጠራቸውን ተቃውመዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2021 ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አሰናብተው ፓርላማውን ካገዱ በኋላ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ፕሬዝዳንቱ የአንድ ሰው አገዛዛቸውን የሚያፀድቀውን ሕገ-መንግስት እንዲያልፍ አድርገዋል።
አዲሱ ሕገ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2011 ከተካሄደው የአረብ አብዮት በኋላ የተረቀቀውንና የቱኒዚያ የቀድሞ አምባገነን መሪውን ዚነ አል-አቢዲን ቤን አሊን ከሥልጣን ያስወገደውን ተክቷል።
ይህም የአገሪቱ መሪ የሠራዊቱን ከፍተኛ አመራር ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩ አድርጓል።
ፕሬዝዳንት ሰኢድ ይህ እርምጃቸው የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ አዙሪትን ለመስበር አስፈላጊ ነው ብለው ይሞግታሉ።












