በቱኒዚያ ጠረፍ የስደተኞች ጀልባ የመስመጥ አደጋን ተከትሎ 34 ሰዎች ደብዛቸው ጠፍቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሐራ በታች ካሉ አገራት እንደሆኑ የተገመቱ ስደተኞች የተሳፈሩባት ጀልባ ሰምጣ የ34 ሰዎች ደብዛ ጠፍቷል። ከስደተኞቹ መሀል ልጆችና ጨቅላ ሕጻናት ይገኙበታል።
የስደተኞች ጀልባ ሲሰጥም ይህ በሁለት ቀናት ውስጥ አምስተኛው ጀልባ መሆኑ ነው።
ለጊዜው ሰባት ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን በሁለት ቀናት 67 ሰዎች በድምሩ ደብዛቸው ጠፍቷል።
የቱኒዚያ ባለሥልጣናት እንደሚገምቱት ጀልባዎቹ ይጓዙ የነበረው ወደ ጣሊያን ነበር።
ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ የቱኒዚያ የጠረፍ ጠባቂዎች 56 ጀልባዎች ወደ ጣሊያን ሊያመሩ ሲሉ በቁጥጥር ሥር አውለናቸዋል ብለዋል።
የድንበር ጠባቂዎቹ ኃላፊ ሆሳም ጀባብሊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰሞኑን ብቻ ሦስት ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ወደ ጣሊያን ሊሳፈሩ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቱኒዚያ ወደ አውሮፓ ለሚያቀኑ ስደተኞች ዋነኛ መነሻ ወደብ ሆናለች።
የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ በዚህ ዓመት ወደ ጣሊያን ከተጓዙ ስደተኞች 12ሺህ የሚሆኑት መነሻቸው ቱኒዚያ ነበር።
ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ12 እጥፍ ብልጫ አለው።
ባለፈው ወር የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ ከሰሐራ በታች የሚመጡ ጥቁር አፍሪካዊያን በአገራቸው ወንጀል እያለማመዱ እንደሆነና ለአረብ ለቱኒዝያ ጥቁሮች አደጋ እንደሆኑ የሚያመላክት ዘረኛ ንግግር መናገራቸው ይታወሳል።
ይህ ዘረኝነት የተጫነው ንግግራቸው አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ በርካታ የመብት ተሟጋቾችን አስቆጥቶ ነበር።
ባለፈው አርብ በብራስልስ ንግግር ያደረጉት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በቱኒዚያ መረጋጋት ካልመጣ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር።
ቱኒዚያ ከአይኤም ኤፍ ጋር ብድር ለማግኘት ያደረገችው ድርድር ውጤት ባለማስገኘቱ አሁን በአገሪቱ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ምስቅልቅል ተፈጥሯል።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ቱኒዚያ በአስቸኳይ ከአይ ኤም ኤፍ ጋር ስምምነት ገብታ ኢኮኖሚዋን እንድታቃና መክረዋል።
በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ቱኒዚያ የአረቡን የጸደይ አብዮት ተከትሎ ፖለቲካዋ ሊረጋጋ አልቻለም። የአሁኑ ፕሬዝዳንትም ፓርላማቸውን በትነው በአዋጅ ነው አገሪቱን እየመሩ ያሉት።












