ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ በጠና መታመማቸውን ባለቤታቸው ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, @MOHAMMED_MEAZA
የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በጠና መታመማቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኃይሌ ለቢቢሲ ገለጹ።
ብ/ጄኔራል ተፈራ በአሁኑ ወቅት መንቀሳቀስ እንደማይችሉ እና ከወራት በፊትም ለህክምና ወደ ውጭ አገር እንዳይወጡ መከለልከላቸውንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ መነን እንደሚሉት በኅዳር ወር ላይ ጄኔራሉ ወደ እስራኤል ሄደው ለመታከም ቢሞክሩም አየር ማረፊያ ሲደርሱ መውጣት እንደማይችሉ ተነግሯቸው ተመልሰዋል።
ለህመማቸው መንስዔ የሆነው ከዚህ ቀደም በጥይት የተመታ እግራቸው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ጥይቱ አቅጣጫውን ለውጦ ነርቫቸው ላይ እንዳረፈ መረዳታቸውን ገልጸዋል።
ህመሙ ያለው በቀኝ እግራቸው ላይ ቢሆንም ለመነሳትም ሆነ ለመቆም በጣም እንደሚከብዳቸው እና ጭንቅላታቸውም ላይ ከፍተኛ ህመም እንደለባቸው እንደሚናገሩ ወ/ሮ መነን ተናግረዋል።
ብ/ጄኔራል ተፈራ በአገር ውስጥ ባሉ የህክምና ተቋማት ከማስታገሻ መድኃኒቶች ውጭ ሌላ ህክምና ያላደረጉ ሲሆን፣ የሐኪሞች ቦርድም ወደ ውጭ አገር በመሄድ እንዲታከሙ ደብዳቤ መጻፉንም ባለቤታቸው ያስረዳሉ።
ከወራት በፊት ጥቅምት አካባቢ በጠና ታመው በነበረበት ወቅት ያለባቸው የጤና ችግር መገጣጠሚያቸውም ላይ ችግር እያመጣ እንደሆነ ተነግሯቸው በውጭ አገር እንዲታከሙ ደብዳቤ ተጽፎላቸው ነበር ብለዋል።
ጄኔራሉ ለህክምና ወደ ውጭ አገር ለመጓዝ አዲስ አበባ አየር ማረፊያ ባቀኑበትም ወቅት አይቻልም ተብለው እንደተመለሱ የሚናገሩት ወ/ሮ መነን፣ በዚህም ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገናል ብለዋል።
ወደ ውጭ አገር እንዳይጓዙ ለምን እንደተከለሉ ምክንያቱን የትኛውም አካል እንዳላስረዷቸውም ገልጸዋል።
“ኢሚግሬሽን እኔ አላገድኩም ይላል። እኛ ጋር እግድ የለባቸውም ስለዚህ ከእኛ ጋር የሚገናኝ ነገር የለም ይላሉ። አየር ማረፊያ ስንጠይቅ ደግሞ ወደዚያኛው ይልኩናል” ብለዋል ወ/ሮ መነን።
እስካሁን የአገሪቱ የሕግም ሆነ የፀጥታ አካል ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከአገር እንዳይወጡ ተከልክለዋል ስለመባሉ ያለው ነገር የለም።
ቢቢሲ ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞን ለማናገር ባለቤታቸውን የጠየቀ ቢሆንም፣ በገጠማቸው ህመም የተነሳ ማስታገሻ እየወሰዱ ስለሆነ ማናገር እንደማይችሉ ወ/ሮ መነን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ እና ሰብዓዊነት የተሰማቸው የሚያውቋቸው ዶክተሮች ማስታገሻ በየቀኑ እየሰጧቸው ከህመማቸው ጋር እየታገሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከአገር እንዳይወጣ እግድ እንዴት ይጣላል?
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ለህክምና ወደ ውጭ አገር እንዳይጓዙ ተከልክለዋል ከሚለው የቤተሰባቸው ቅሬታ ጋር ተያይዞ ቢቢሲ አንድ ሰው ከአገር እንዳይወጣ እገዳ የሚጣልበት እንዴት እንደሆነ የሕግ ባለሙያን ጠይቋል።
የአንድ ሰው የመንቀሳቀስ ነጻነቱ ሊታገድ የሚችለው ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት ቀርቦ፣ በነጻነቱ ላይ ክልከላ በሚቀመጥበት ጊዜ እንደሆነም የሕግ ባለሙያው አቶ ሔኖክ አክሊሉ ያስረዳሉ ነው።
ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ፍርድ ቤቱ ተገቢ ነው የሚለውን ክልከላ ይጥላል ብለዋል አቶ ሔኖክ። ከእነዚህም ውስጥ ከአገር አለመውጣት፣ በአንድ ቤት መወሰን እና ሌሎች የነጻነት ክልከላዎች ተግባራዊ ይሆናሉ።
ይህንንም ሕግ አስፈጻሚ አካላት የሚያስፈጽሙ ሲሆን ከዚህ ውጭ ግን የአስተዳደር አካላት በዘፈቀደ የዜጎችን መሠረታዊ የመንቀሳቀስ ነጻነት ሊነፍግ በሚችል መንገድ መከልከል የሚችሉበት ሕጋዊ አሰራር እንደሌለ ጠበቃ ሔኖክ ያስረዳሉ።
ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እየተተገበረ ነው የሚለውን በሚያዩበት ወቅት፣ በአገሪቱ የመውጫ በሮች ላይ ያሉ የፀጥታ ተቋማት አንድ ሰው የፍርድ ቤት ክልከላ ባይኖርበትም የደኅንንት ችግር ይሆናል በሚሉበት ወቅት ከበረራ የሚመልሱበት አጋጣሚዎች እንዳሉም ያስረዳሉ።
ለዚህም ምክንያቱ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ሕግ አስፈጻሚዎች “እዚህ ቦታ ላይ የተቀመጣችሁት እንደእነዚህ ዓይነት ሰዎች ሲወጡ ክትትል እንድታደርጉ ነው፤ ለምን ዝም አላችሁ ተብለው ስለሚገመገሙ ነው” ይላሉ።
ይህ አስፈጻሚው አካል በዘፈቀደ የሚያደርገው ተግባር እንደሆነ የሚናገሩት ጠበቃ ሔኖክ ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ተቀባይነት የሌለው ነው ይላሉ።
በዚህ ዓይነት መንገድ ከዚህ ቀደም ዜጎች ከበረራ ሲታገዱ እና ያላቸው ፕሮግራሞች ሲስተጓጎሉ መመልከታቸውምን ያስረዳሉ።
“አስፈጻሚው አካል እነዚህ ሰዎች የደኅንነት ስጋት ከሆኑ ፍርድ ቤት አቅርቦ ሕጋዊ ክልከላ ለምን እንዲደረግባቸው አያደርግም” ሲሉም ይጠይቃሉ።
ከሕጋዊው አሰራር ውጭ ጉዳት ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች መክሰስም ሆነ መጠየቅ የሚችሉበት አማራጮችን የኢትዮጵያ ሕግ አስቀምጧል ይላሉ ጠበቃው።
ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነት በረራዎች የሚከለከሉት ፖለቲከኞች ወይም ታዋቂ ሰዎች ቢሆኑም ያለውን ሕጋዊውን አማራጭ ሲከተሉ እንደማይታይም ያስረዳሉ።
“ምንም ዓይነት ሕጋዊ ክልከላ በሌለበት አንድ ሰው በርካታ ገንዘብ አውጥቶ ያቀደው ጉዞ የሚደነቃቀፍበት ሁኔታ ቀላል አይደለም። በማስረጃ አጠናክሮ በሕግ መጠየቅ ይቻላል” ብለዋል።
ጥቂት ስለ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ተሰውረው በደኅንነት ኃይሎች በሄሊኮፕተር ወደ ባሕር ዳር ከተማ ተወስደው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀልም በ30 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰኔ 3/2014 ዓ.ም. ውሳኔ አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ለዓመታት በከፍተኛ መኮንንነት ያገለገሉት ብርጋዲዬር ጄነራል ተፈራ ማሞ፣ ከአስር ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከሌሎች ጋር ተከሰው ለዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎም ከእስር ተለቀው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ብ/ጄኔራል ተፈራ ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉ ሲሆን እንዲሁም በቅርቡ የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ሆነው ሰርተዋል።
ከልዩ ኃይል አዛዥነታቸው ተነስተው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አማካሪነት ሹመት ቢሰጣቸው ሳይቀበሉት መቅረታቸው ይታወሳል።
ብ/ጄኔራል ተፈራ ሞሞ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥነት ከተነሱ በኋላ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ የአማራ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ ላይ ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።












