በአሜሪካ በጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 100 ተሻገረ

በጎርፉ የተወሰዱ መኪናዎች

አርብ ዕለት በአሜሪካ ማዕከላዊ ቴክሳስ የደረሰው የደራሽ ጎርፍ አደጋ የሟቹች ቁጥር 100 በላይ ሲደርስ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ደግሞ እስካሁን አልተገኙም።

ተጨማሪ ዝናብ እና ነጎድጓድ በአካባቢው ስጋት የሆነ ሲሆን የነፍስ አድን ሠራተኞች በጭቃ በተሞሉ የወንዝ ዳርቻዎች ሰዎችን እየፈለጉ ነው።

ይኹን እንጂ አደጋው ከደረሰ ከአራት ቀናት በኋላ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ተስፋ እየጨለመ ነው።

ሚስቲክ የተባለው የክርስቲያኒያዊ ወጣቶች ካምፕ 27 ሴቶች እና የሥራ ባልደረቦች ከሞቱት ውስጥ እንደሚገኙበት አስታውቋል።

ታዳጊ ሴቶች እና የካምፑ አማካሪ እስካሁን አልተገኙም።

አደጋውን ቀድሞ መተንበይ አለመቻሉ የብሔራዊ አየር ጠባይ አገልግሎት በጀት መቀነስ አስከትሎት ሊሆን ይችላል የሚለውን ሀሳብ ዋይት ሐውስ አጣጥሎታል።

ጓዱላፔ ወንዝ በከፍተኛ ዝናብ በተጥለቀለቀበት በኪር አካባቢ ቢያንስ 84 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

የአካባቢው የፖሊስ ቢሮ 22 አዋቂ ሰዎች እና 10 ሕፃናት እስካሁን ማንነታቸው አልተለየም ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሚስቲክ የተባለው ካምፕ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ "ሊታሰብ የማይችለው ሐዘን ከገጠማቸው ቤተሰቦች ጋር ልባችን ተሰብሯል" ብሏል።

የ70 ዓመቱ የካምፑ የጋራ ባለቤት እና ዳይሬክተር ሪቻርድ ኢስትላንድ ሕፃናቱን ለማትረፍ ሲሞክሩ ሕይወታቸው አልፏል።

የአገሪቱ ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ቀስ ብሎ የሚንቀሳቀስ ነጎድጓዳ አየር የተነበየ ሲሆን፤ ይህም በአካባቢው ደራሽ ጎርፍ ሊያስከትል ይችላል ብሏል።

ለአካባቢው አየር ትንበያ የሚያወጣው አገልግሎቱ ሐሙስ ምሽት በቴክሳስ ግዛት ነጎድጓድ ሲበረታ አምስት ሠራተኞቹ ስራ ላይ ነበሩ።

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሌቪት ለአደጋው ፕሬዝዳንቱን ለመውቀስ መሞኮሩን አጣጥለዋል።

ሰኞ ዕለት በነበረው የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ አደጋውን "የእግዚአብሔር ሥራ ነው" ብለዋል።

"ጎርፉ የተከሰተው በአስተዳደሩ ጥፋት አይደለም። ነገር ግን አስቀድሞ ተከታታይነት ያለው ማስጠንቀቂያዎች ነበሩ። ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ስራውን ሰርቷል" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት ቴክሳስን ይጎበኛሉ ተብለው የሚጠበቁት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የፌደራል መንግሥት የበጀት ቅነስ የአደጋ ምላሽ አሰጣጡን አደናቅፎ ከሆነ ሲጠየቁ ጣታቸውን በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ ቀስረዋል።

"ነገር ግን ባይደንን ለዚህ አልወቅሰውም" ካሉ በኋላ፤ "የ100 ዓመታት አደጋ እንደሆነ ነው እላለሁ" ብለዋል።

የቴክሳስ ሴናተር የሆኑት ቴድ ክሩዝ ሰኞ ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ጣት ለመቀሳሰር ጊዜው አሁን አይደለም ሲሉ ተደምጠል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመላው ዓለም የሐዘን መግለጫዎች ቀጥለዋል።

የብሪታኒያው ንጉስ ቻርለስ ሣልሳዊ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ በፃፉት ደብዳቤ በአስከፊው የጎርፍ አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል።