የትራምፕ አይገመቴነት ዓለምን ለመቀየር እያገለገለ ይሆን?

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል ኢራን ላይ እየፈፀመችው የነበረውን ጥቃት እንደሚቀላቀሉ ሲጠየቁ "ላደርገው እችላለሁ። ላላደርገውም እችላለሁ። ምን ላደርግ እንደምችል ማንም አያውቅም" ነበር ምላሻቸው።

ኢራን ወደ ድርድር እንድትመለስ የሁለት ሳምንታት እፎይታ ሰጥቻለሁ በማለት መላው ዓለም እንዲያምን አደረጉ። ከዚያም በኢራን ላይ የቦምብ ናዳ አዘነቡ።

አሁን ስለትራምፕ ጠባይ የተወሰኑ መልኮች መታየት ጀምረዋል።

የትራምፕ በጣም ተገማቹ ፀባያቸው አለመገመታቸው ነው። ሀሳባቸውን ይቀያይራሉ። ራሳቸውንም ይቃረናሉ። አቋምም የላቸውም።

በለንደን የምጣኔ ሀብት ትምሕርት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት ፒተር ቱሩቦዊትዝ "[ትራምፕ] ከፍተኛ የተማከለ የፖሊሲ ተልዕኮ መስርቷል፤ ከሪቻርድ ኒክሰን በኋላ በውጭ ፖሊሲ ረገድ ምናልባትም በጣም የተማከለ ነው"።

"እና ይህም የፖሊሲ ውሳኔ በትራምፕ ባህሪ፣ ምርጫ፣ ቁጣ ላይ በጣም የተመሠረተ ነው" ይላሉ።

ትራምፕ አይገመቴነታቸውን ለፖለቲካ ጥቅማቸው እንደ ስልት መጠቀም የያዙ ይመስላል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ አይገመቴነታቸውን ለፖለቲካ ጥቅማቸው እንደ ስልት መጠቀም የያዙ ይመስላል

ትራምፕ ይህን ለፖለቲካ ይጠቀሙበታል። ተገማች አለመሆናቸውን ለቁልፍ ስልት እና ፖለቲካዊ ጥቅም አውለውታል።

ተገማች አለመሆናቸውን ወደ ዶግማነት ከፍ አድርገውታል። እናም አሁን የግል ሰብዕናቸውን ወደ ዋይት ሐውስ ወስደው የውጭ እና ደኅንነት ፖሊሲ መሪ አድርገውታል።

ይህም የዓለምን ቅርፅ እየለወጠ ነው።

የፖለቲካ ተመራማሪዎች ይህን "የእብድ ፅንሰ ሀሳብ" ይሉታል።

ይህም ማለት የዓለም መሪ ባላንጣዎቻቸውን ለማሳመን ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ ማሳመን ይፈልጋሉ።

በትክክል ጥቅም ላይ ከዋለ ማስገደጃ መንገድ ይሆናል።

እናም ትራምፕ ክፍፍልን በመፍጠር የአሜሪካ አጋሮችን እንደሚፈልጓቸው እያደረጉ እንደሆነ ያምናሉ።

ነገር ግን ይህ ለጠላቶች የሚሰራ አካሄድ ነው? የባላንጣዎች ማጭበርበሪያ ስውር እጅ ከመሆኑ ይልቅ በግለሰብ ሰብዕና ላይ የተመሰረተ እና ባህሪውን ለመገመት ቀላል አያደርገውም?

ጥቃቶች፣ ዘለፋ እና ቅቡልነቶች

ትራምፕ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በመቀበል እና የአሜሪካ አጋሮችን በማጥቃት ነው።

ካናዳ የአሜሪካ 51ኛዋ ግዛት እንድትሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ አጋር የሆነችው ዴንማርክ ራስ ገዝ ግዛት የሆነችውን ግሪንላንድን ለመገንጠል ወታደራዊ ኃይል ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም አሜሪካ የፓናማ ካናልን ባለቤት መሆን እና መቆጣጠር አለባት ብለዋል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) መመስረቻ አንቀፅ 5 እያንዳንዱ አባል አገራት ሁሉንም አባል መከላከል እንዳለበት ይደነግጋል።

ነገር ግን ትራምፕ የአሜሪካ ቁርጠኝነት ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርገዋል።

የብሪታኒያ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋለስ "አንቀፅ 5 በሕይወት እና ሞት መካከል ላይ ያለ ይመስለኛል" ይላሉ።

ወግ አጥባቂ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ የሆኑት ዶሚኒክ ግሪቭ "ለአሁኑ የአትላንቲክ ጦር ጥምረት አክትሞለታል" ብለዋል።

አፈትልከው የወጡ የጽሑፍ መልዕክቶች የዋይት ሐውስ ሹማምንት ለአውሮፓውያን አጋሮቻቸው ንቀት እንዳላቸው አመላክተዋል።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት "የነፃ ተጠቃሚ የሆኑ አውሮፓዊያንን መጠየፍን ሙሉ ለሙሉ እጋራለሁ" ሲሉ "አሳዛኝ" ከሚል ምፀት ጋር መልዕክት ልከዋል።

ፒት ሄግሰት (በቀኝ በኩል) ጄዲ ቫንስ ደግሞ (በስተግራ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፒት ሄግሰት (በቀኝ በኩል) ሾልኮ በወጣ መልዕክታቸው የአውሮፓ መሪዎች "ነፃ ተጠቃሚ" ሲሉ፤ ጄዲ ቫንስ ደግሞ (በስተግራ) አሜሪካ የአውሮፓ ደኅንነት ዋስትና እንደማትሆን ተናግረዋል

በዚህ ዓመት በሙኒክ የትራምፕ ምክትል ጄዲ ቫንስ አሜሪካ ከዚህ በኋላ የአውሮፓ ደኅንነት ዋስ አትሆንም ብለዋል።

ይህም በ80 ዓመት የአትላንቲክ ትብብር ታሪክ አዲስ ገፅን የገለጠ ነው።

ፕሮፌሰር ትሩቦዊትዝ "ትራምፕ ያደረጉት ነገር አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ኃላፊነት ከባድ ጥርጣሬ እና ጥያቄ እንዲነሳ ማድረግ ነው" ይላሉ።

"[የአውሮፓ] አገራት ከአሜሪካ ጋር በደኅንነት፣ በምጣኔ ሀብት ወይም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያላቸው መረዳት አሁን በቅፅበትም ቢሆን የድርድር ጉዳይ ነው።

"እኔ እንደምረዳው በትራምፕ ምህዋር ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ተገማች አለመሆንን መልካም ነገር አድርገው ያስባሉ። ምክንያቱም ትራምፕ በግርግሩ መሀል ከፍተኛ ትርፍ እንዲያገኙ ያስችላል በሚል እሳቤ ነው. . . ይህ በሪል ስቴት ዓለም ድርድር የተማሩት አንደኛው ቁልፍ ነው" ይላሉ።

የትራምፕ አካሄድ ክፍፍልን ፈጥሯል።

ከአራት ወራት በፊት ሰር ኪር ስታርመር ብሪታኒያ የመከላከያ እና ደኅንነት ወጪዋን ከጠቅላላ ምርቷ ከ2.3 በመቶ ወደ 2.5 በመቶ ከፍ እንደምታደርግ አሳውቀዋል።

ከሳምንታት በፊት በኔቶ ጉባኤ የአባል አገራት የመከላከያ በጀት ወደ አምስት በመቶ ከፍ እንዲል የተደረሰው ውሳኔ አሁን መላው የትብብሩ አገራት በጀታቸውን ከፍ እንዲያደረጉ ያስገደደ ነው።

የአይገመቴነት ተገማችነት

ትራምፕ ያለመገመትን እሳቤ የተገበሩ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት አይደሉም።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1968 ፕሬዝዳንት ኒክሰን የቬትናምን ጦርነት ለመቋጨት ሲሞክሩ የሰሜን ቬትናም ጠላቶቻቸው የማይበገሩ ሆነው አገኟቸው።

በኖረት ዳም ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር የሆኑት ሚሼል ዲሽ "አንድ ጊዜ ኒክሰን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው ሄነሪ ኪሲንጀርን 'የሰሜን ቬትናም ተደራዳሪዎችን ኒክሰን እብድ ነው በላቸው፤ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አላውቅም። ስለዚህ ነገሮች ከመበላሸታቸው በፊት ወደ ስምምነት ብትመጡ የተሻለ ነው [እንዲሉ አደረጋቸው]'" ይላሉ።

"ይህም የእብድ ሰው ፅንሰ ሀሳብ ይባላል።"

ፕሬዚደንት ኒክሰን ከሄንሪ ኪሲንጀር ጋር ሲነጋገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእብድ ሰው ፅንሰ ሀሳብ ከሪቻርድ ኒክሰን የውጭ ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ነው።

በለንደን ኮሌጅ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ጁሊ ኖርመን ተገማች ያለመሆን ዶግማ አሁን እንደተፈጠረ ይስማማሉ።

"በየቀኑ ምን እየተከሰተ እንደሆነ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው" ሲሉ የሚሞግቱት ፕሮፌሰሯ፤ "ይህ ሁሌም ቢሆን የትራምፕ አካሄድ ነው" ይላሉ።

ትራምፕ በአትላንቲክ የመከላከያ ግንኙነት ላይ አቋማቸውን ለመለወጥ ዝናቸውን በሚገባ ተጠቅመዋል። እናም አንዳንድ የአውሮፓ መሪዎች ትራምፕን ከጎናቸው ለማድረግ ሽንገላ እና ልምምጥ አሳይተዋል።

ከሳምንታት በፊት በሄግ በተካሄደው የኔቶ ጉባኤ የልምምጥ መድረክ ነበር። የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩት ከጉባኤው አስቀድመው "ለውድ ዶናልድ" የላኩት አጭር የጽሑፍ መልዕክት በትራምፕ ይፋ ወጥቷል።

"በኢራን ለወሰዱት ቁርጠኛ እርምጃ እንኳን ደስ አለዎት፤ እናመሰግናለን። ይህ እውነትም ታይቶ የማይታወቅ ነው" ሲሉ በመልዕክታቸው አስፍረዋል።

ሁሉም የኔቶ አባል አገራት ከጠቅላላ ምርታቸው ለመከላከያ ወጪያቸው 5 በመቶውን እንዲመድቡ መስማማታቸው ሲገለፅ፤ "በአስርት ዓመታት ማንም ፕሬዝዳንት ሊያደርገው የማይችለውን እርስዎ አሳክተዋል" ሲሉም አሞካሽተዋል።

በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት አንተኒ ሳክራሙቺ "ሩት [ትራምፕ] ሊያስፍርህ እየሞከረ ነው፤ አሁን በኤርፎርስ ዋን ተቀምጦ እየሳቀብህ ነው" ብለዋል።

የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩት እና ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩት ከጉባኤው አስቀድመው ለትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ልከዋል

ይህም ታዲያ በትራምፕ ያለመገመት እሳቤ ውስጥ ድክመት ለመሆኑ ማስረጃ ሊሆን ይችላል።

እርምጃቸው ትራምፕ ሙገሳ ይወዳል በሚል ላይ የተመሰረተ ነው። ወይም ደግሞ ትራምፕ ከረዥም እና ውስብስብ ሂደት ይልቅ የአጭር ጊዜ አሸናፊነትን ይሻሉ ብለው ያምናሉ።

ጉዳዩ ይህ ከሆነ እና ግምገማቸው ትክክል ከሆነ ትራምፕ ባላንጣዎቻቸውን ለማጭበርበር የሚጠቀሙበት ስውር እጃቸውን ይገድባል።

ወይም ያወቁት የተረጋገጠ እና ግልፅ ተገማች ሰብዕና አላቸው ማለት ነው።

ተቃዋሚዎች ለመማረክ እና ለማስፈራራት አለመበገር

የአለመገመት እሳቤ ወይም ደግሞ የእብድ ሰው ፅንሰ ሀሳብ ባላንጣዎች ላይ መስራት እና አለመስራቱ ላይ ጥያቄዎች አሉ።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የዋሽንግተን አጋር የነበሩ፤ ነገር ግን በትራምፕ እና በጄዲ ቫንስ በኦቫል ኦፊስ ውርደት ገጥሟቸዋል።

ከዚህ ክስተት በኋላ አሜሪካ የዩክሬንን የማዕድን ሀብት እንድትጠቀም ፈቃድ አግኝታለች።

በሌላ ወገን ቭላድሚር ፑቲን ከትራምፕ ማራኪነት እና ስጋት ነፃ ናቸው።

ባለፈው ሐሙስ በስልክ ከተወያዩ በኋላ ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ለመቋጨት ዝግጁ ባለመሆናቸው ትራምፕ "ተበሳጭቻለሁ" ብለዋል።

ዜሌንስኪ ከትራምፕ ጋር በኦቫል ኦፊስ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ዜሌንስኪ በኦቫል ኦፊስ ውስጥ በአለባበሳቸው ነቀፋ ከገጠማቸው በኋላ የዩክሬን የማዕድን ሀብቶችን ለአሜሪካ ጥቅም እንዲውሉ ተስማምተዋል

ኢራንስ?

ትራምፕ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ "የዘላለም ጦርነቶች" ያላትን ተሳትፎ ለማብቃት ለደጋፊዎቻቸው ቃል ገብተው ነበር።

የኢራንን የኒውክሌር ጣቢያዎች ለመደብደብ የወሰኑት ውሳኔ ምናልባትም በሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው በእጅጉ ያልተገመተው የፖሊሲ ውሳኔ ነው።

ጥያቄው ግን የተፈለፈገውን ውጤት ያመጣል ወይ የሚለው ነው።

የቀድሞው የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊሊያም ሄግ እርምጃው በትክክል ተቃራኒ ውጤት ያመጣል ሲሉ ይሞግታሉ። ኢራንን የበለጠ የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን ያደርጋል ባይ ናቸው።

ፕሮፌሰር ዲሽ በዚህ ይስማማሉ። "አሁን ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለመታጠቅ የመወሰን እድሏ ከፍተኛ ነው ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

"ስለዚህ ድምፃቸውን አጥፍተው ማጠናቀቅ እና [የኒክሌር] ሙከራን ቢያካሂዱ አይደንቀኝም።

"እኔ እንደማስበው የሳዳም ሁሴን እና የሙአመር ጋዳፊ ትምህርት ለሌሎች አሜሪካን ለሚጋፈጡ አምባገነኖች እና የአገዛዝ ለውጥ ላለማምጣት ለሚሹ [ትምሕርት ነው]. . .

"ስለዚህ ኢራናውያን ለመጨረሻ ጊዜ ራሳቸውን ለመከልከል እንደሚፈልጉ በጣም ይሰማቸዋል፤ እናም ሳዳምን እና ጋዳፊን እንደ አሉታዊ ምሳሌዎች፤ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡን ደግሞ እንደ አዎንታዊ ምሳሌ ይመለከቷቸዋል" ይላሉ።

የኢራኑን ጠቅላይ መሪ ፎቶ ያዙ ሠልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከአሜሪካ ጥቃት በኋላ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደምትሞክር ብዙዎች ይስማማሉ

በደቡብ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር ሞህሰን ሚላኒ እንደሚሉት ከቢሆንታ እይታዎች መካከል አንዱ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መጠናከር ነው።

እአአ በ1980 ሳዳም ሁሴን ኢራንን ሲያጠቁ ዓላማቸው "ኢስላማዊ ሪፐብሊክን ማፈራረስ ነበር" ይላሉ። "ነገር ግን ተቃራኒው ነው የሆነው።"

"የእስራኤል እና የአሜሪካዊያኑ ስሌትም ይህ ነበር። . . . ቁንጮ ላይ ያሉትን ሰዎች ብናስወግድ ኢራን በፍጥነት እጅ ትሰጣለች ወይም አጠቃላይ ስርዓቱ ይፈርሳል የሚል ነው" ይላሉ።

በድርድር እምነት ማጣት?

ወደ ፊት ራቅ አድርገን ስናስብ፤ ተገማች አለመሆን በጠላቶች ላይ ላይሰራ ይችላል።

ነገር ግን በቅርብ ጊዜ በአጋሮች መካከል ወዲያው የሚከሰት የለውጥ ግንኙነትን ማስቀጠል ይችል እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ይህ ሂደት በአብዛኛው ስሜት ላይ የተወሰነ ነው። እናም አሜሪካ አስተማማኝ ያልሆነች አጋር ሆና እንድትቆጠር ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት ሊኖር ይችላል።

ፕሮፌሰር ኖርማን "ሰዎች አሜሪካን በድርድር ካላመኑ፤አሜሪካ በመከላከያ እና በፀጥታ ጉዳዮች ከጎናቸው እንደምትቆም እርግጠኛ ካልሆኑ አብረዋት መስራት አይፈልጉም" ሲሉ ይከራከራሉ።

"ስለዚህ ብዙዎች 'አሜሪካን ዳግም ታላቅ ማድረግ' የሚፈልጉ ሰዎች እንደሚያስቡት አይሳካም" ይላሉ።

የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ በበኩላቸው አውሮፓ አሁን ከአሜሪካ ነፃ መሆን አለባት ብለዋል።

ፕሮፌሰር ትሩቦዊትዝ "የቻንስለሩ አስተያየት አስፈላጊነት አሜሪካ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ስልታዊ ጉዳዮች እየተለወጡ መሆናቸውን እውቅና መስጠት ነው" ብለዋል።

"ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ወደነበሩበት ሁኔታ መመለስ አይችሉም። ስለዚህ አዎ፤ አውሮፓ የበለጠ ነፃ ወደመሆን ይሄዳል" ይላሉ።

የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ እና ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ አውሮፓ አሁን ከአሜሪካ ነፃ መሆን አለባት ይላሉ

ይህ የአውሮፓ መንግሥታት በጣም ትልቅ የመከላከያ ኢንዱስትሪ እንዲገነቡ፣ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ ብቻ ያላትን ቁሳቁስ እና አቅሞችን እንዲይዙ ይገፋል ሲሉ ፕሮፌሰር ዲሽ ይናገራሉ።

ለምሳሌ አንዳንድ አውሮፓዊያን በዓለም የተራቀቀ የስለላ ችሎታ አላቸው። ነገር ግን አብዛኛው የስለላ መረጃ የሚቀርበው ከአሜሪካ ነው።

"አውሮፓ ብቻውን መሄድ ካለባት ትጥቅ የማምረት አቅሙ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ያስፈልገዋል" ሲሉ ያክላሉ። የሰው ኃይል እንዲሁ አንገብጋቢ ይሆናል።

ታዲያ ይህን ሁሉ ለመገንባት ዓመታት ይወስዳል።