ከፕሬዚደንት ትራምፕ ጋር አለመግባባት ውስጥ የገባው ኢሎን መስክ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሜያለሁ አለ

ኤለን መስክ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኢሎን መስክ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ያለው የቅርብ ወዳጅነት በአለመግባባት ከተጠናቀቀ ከሳምንታት በኋላ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሜያለሁ አለ።

ቢሊየነሩ የፖለቲካ ፓርቲን ማቋቋሙን ለሪፐብሊካን እና ዲሞክራቲክ የሁለት ፓርቲ ስርዓት ፈተና እንደሆነ በመግለጽ በማህበራዊ ሚዲያው ኤክስ ገጹ ላይ አስታውቋል።

ሆኖም ፓርቲው በይፋ በአሜሪካ የምርጫ ባለሥልጣን መመዝገቡ ግልፅ አይደለም

ከአሜሪካ ውጭ በመወለዱ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ብቁ ያልሆነው መስክ ፓርቲውን ማን እንደሚመራው አልተናገረም።

መጀመሪያ ከትራምፕ ጋር በነበረው አለመግባባት ወቅት ፓርቲ የመመስረት ሃሳብን አንስቶ የነበረው መስክ፣ አለመግባባቱ እየተካረረ መጥቶ በአስተዳደሩ ውስጥ የነበረውን ኃላፊነት ለቅቆ ከቀድሞ የቅርብ ወዳጁ ጋር የተካረረ አለመግባባት ውስጥ መግባቱ የአደባባይ ሚስጥር ነበር።

መስክ ከፕሬዚደንት ትራምፕ ጋር የተካረረ አለመግባባት ውስጥ በነበረበት ወቅት የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን በአሜሪካ ውስጥ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መኖር ይኖርበት እንደሆን የሚጠይቅ አስተያየት ለጥፏል።

መስክ በቅዳሜው ልጥፍ ላይ ያንን የሕዝብ አስተያየት በመጥቀስ "2 ለ 1 በሆነ ውጤት፣ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲኖር ፍላጎታችሁን አሳይታችኋል! አገራችንን በቆሻሻና በሌብነት ወደ ኪሳራ ስለመውሰድ ስንነጋገር የምንኖረው በአንድ ፓርቲ ስርዓት እንጂ በዲሞክራሲ አይደለም።" ሲል ጽፏል።

አክሎም "ዛሬ የአሜሪካ ፓርቲ የተመሰረተው ነፃነታችሁን ሊመልስላችሁ ነው" ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቅዳሜ ጀምሮ የፌዴራል ምርጫ ኮሚሽን ፓርቲው በይፋ መመዝገቡን የሚጠቁሙ ሠነዶችን ይፋ አላደረገም።

በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ከተለምዷዊው የሁለት ፓርቲ ስርዓት ውጪ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም ቢኖሩም፣ እውነተኛ ጫና ለመፍጠር በአገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተቀባይነት ማግኘት አዳጋች ነው።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደ ሊብሪተያን ፓርቲ፣ ግሪን ፓርቲ እና ፒፕልስ ፓርቲ ያሉ እጩዎች ትራምፕን ወይም የዴሞክራቲክ ተቀናቃኛቸውን ካማላ ሃሪስን እንዳያሸንፉ ለማድረግ ያልተሳካ ሙከራ አድርገዋል ።

መስክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የትራምፕ ዋና ደጋፊ ነበር።

ባለፈው ዓመት በተደረጉ የምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት ከፕሬዚደንቱ ጎን በአጋፋሪነት የነበረው መስክ ሥልጣን ከያዙ በኋላም የአራት ዓመት ልጁ ትራምፕን እንዲያገኝ ኦቫል ኦፊስ ድረስ ይዞት መጥቷል።

መስክ የትራምፕን የምርጫ ቅስቀሳ በገንዘብ ከደገፉ ባለሀብቶች መካከል ዋነኛው ነው። ፕሬዚደንቱ ዳግም ሥልጣናቸውን እንዲይዙ 250 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል።

ከምርጫው በኋላም በፌዴራል በጀት ውስጥ የሚታዩ ወጪዎች ላይ ቅነሳዎችን የመለየት ኃላፊነት የተሰጠውን የመንግስት ቅልጥፍና (ዶጅ) ተብሎ የሚጠራውን ተቋም እንዲመራ ተሾመ።

ከትራምፕ ጋር የነበራቸው ውዝግብ የጀመረው በግንቦት ወር አስተዳደሩን ለቅቆ በወጣበት ጊዜ እና የትራምፕን ግብር እና የወጪ ዕቅዶችን በይፋ መተቸት ሲጀምር ነው።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ትልቅ ቆንጆ" ሲሉ በይፋ የሰየሙት ረቂቅ በጀታቸው በአገሪቱ በምክር ቤት ጸድቋል።

ሕጉ ከፍተኛ ወጪን እና የግብር ቅነሳን ያካተተ ሲሆን በአሜሪካ በጀት ላይ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከሦስት ትሪሊየን ዶላር በላይ ጉድለት እንደሚያስከትል ተገምቷል።

በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ መኪኖችን የሚያመርተው ግዙፉ ቴስላ ባለቤት የሆነው መስክ የትራምፕ ሕግ በአረንጓዴ ሽግግር ላይ ወይም እንደ ቴስላ ላሉ ምርቶች ድጎማ ማድረግ ላይ አያተኩርም ሲል ይተቻል።

ትራምፕ በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ትሩዝ ሶሻል ላይ "ኤሎን በታሪክ ውስጥ ከየትኛውም የሰው ልጅ የበለጠ ድጎማ ሊያገኝ ይችላል" ሲሉ ጽፈዋል። "ያለ ድጎማ ኤለን ምናልባት ሱቁን ዘግቶ ወደ አገሩ ደቡብ አፍሪካ መመለስ ይኖርበታል።"

ትራምፕ የቢሊየነሩን ሌሎች ንግዶችን በመጥቀስ ለመስክ ኩባንያዎች የሚደረጉ ድጎማዎችን እንዲመለከት የቅልጥፍና ቢሮውን እንደሚያዙ ዝተዋል።

በተጨማሪም መስክ ለአሜሪካ መንግሥት ሮኬቶችን የሚያመጥቀውን ስፔስ ኤክስ እና ለአሜሪካ እና አውሮፓ የመከላከያ ኃይሎች የሳተላይት አገልግሎት የሚሰጠውን ስታርሊንክ ባለቤት ነው።