ኢሎን መስክ 'ወጪ ቅነሳ' በሚል የአሜሪካ መሥሪያ ቤቶችን "ማተረማመሱን" አስተባበለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢሊየነሩኢሎን መስክ በወጪ ቅነሳ ስም የአሜሪካ ፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን በኃይል በቁጥጥር ሥር አላዋልኩም አለ።
መስክ ይህን ያለው ትናንት በዋይት ሐውስ ከሕጻን ልጁ ጋር በድንገት ተገኝቶ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጎን በመቆም መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው።
የዓለም ቁጥር አንድ ሃብታሙ ሰው 'በኦቫል ኦፊስ' ተገኝቶ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ሲቀበል የመጀመርያው ነው።
ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ በፕሬዝዳንት ትራምፕ አዲስ መሥሪያ ቤት እንዲመራ ከተሾመ በኋላ በአሜሪካ በርካታ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ሲታመሱ ሰንብተዋል።
እሱ የሚመራው መሥሪያ ቤት በእንግሊዝኛው 'ዶጅ' በሚል ምሕጻር የሚታወቅ ሲሆን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ወጪ መቀነስና ሥራቸውን የሚያሳልጡበት መንገድ የማፈላለግ ሚና እንዲወጣ ይጠበቅበታል።
ከዚህ ባሻገር እጅግ ተለጥጠዋል ያላቸውን የፌደራል መንግሥቱን መሥሪያ ቤቶች እንዲታጠፉ ወይም ደግሞ እንዲኮስሱ ይሠራል።
ይህን ለማሳካት በበርካታ ፌዴራል መሥሪያ ቤቶች በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን እየቀነሰ ይገኛል።
በቅርቡ ዓለም አቀፉ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት፣ ዩኤስኤይድ፣ በመላው ዓለም አላስፈላጊ በሆነ መልኩ 'ገንዘብ ይረጫል' በሚል ሥራ እንዲያቆም መደረጉ አይዘነጋም።
ኢሎን መስክ ባለፉት ቀናት በኤክስ ገጹ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮን ጨምሮ የአሜሪካ የትምህርት ሚኒስቴርን አላስፈላጊነት ሲሰብክ ነበር።
ዲሞክራቶች ይህ አዲስ የተሰየመው መሥሪያ ቤት ግልጽነት ይጎድለዋል በሚል ክፉኛ ይተቹታል።
ተግባሩን እንዳያከናውንም የተለያዩ የሕግ መሰናክሎች እየገጠሙት ነው።
መስክ ለጋዜጠኞች በሰጠው ምላሽ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከበጎ ስሜት የመነጩ ናቸው እንጂ በጥላቻ የተነሳሳ ጽንፈኛ እርምጃዎች አይደሉም ብሏል።
"ሕዝቡ 'ሥር ነቀል' ለውጥ እንዲካሄድ ድምጽ ሰጠ፤ ሕዝቡ ይህን ማግኘት አለበት፤ ዲሞክራሲ ማለት ሌላ ሳይሆን ይህ ነው" ብሏል።
ቢሊየነሩ መስክ በሕዝብ የተመረጠ ባይሆንም የፌዴራል መሥሪያ ቤት ሠራተኞችን "ያልተመረጡ፣ ኢ-ሕገመንግሥታዊ የመንግሥት 4ኛ ቅርንጫፎች" ሲል ይወርፋቸዋል።
የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ከተመራጭ የሕዝብ ወኪሎች በላይ ሥልጣን ይዘዋል ሲልም ይተቻል።
የ53 ዓመቱ የቴስላ፣ የኤክስ እና የስፔስ ኤክስ ባለቤት "አሜሪካ ትቅደም" (ሜክ አሜሪካ ግሬት አጌን) የሚል ኮፍያ ለብሶ፣ ሕጻን ልጁን እሸኮኮ አድርጎ፣ ከትራምፕ ጎን በመቆም ለጋዜጠኞች ጥያቄዎች በፌዝ የታጀበ ምላሽ ሲሰጥ ነበር።
"የፌዴራል ወጪን መቀነስ ለኛ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው" ያለው መስክ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
ኢሎን መስክ በጋዜጠኞች ከቀረቡለት ጥያቄዎች አንዱ " ለኮንዶም መግዣ ወደ ጋዛ 50 ሚሊዮን ዶላር የአሜሪካ መንግሥት ልኳል" በሚል በሐሰት ያሰራጨውን ንግግር እንዲያስተባብል የሚጠይቅ ነበር።
መስክ በሰጠው ምላሽ "አንዳንዴ የምናገራቸው ነገሮች ልክ ላይሆኑ ይችላሉ። መስተካከል ይኖርባቸዋል።" ብሏል።
ትራምፕ በተሾሙበት የመጀመርያ ሳምንት መስክ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን የሠራተኛና ወጪ ቁጥር በአያሌው ለማሳነስ ሞክሯል። እሱ የሚመራው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ዘልቀው በመግባት ምን ያህል ለብክነትና ላልተፈለገ ወጪ እንደተዳረጉ ለመፈተሽ ሙከራ ተደርጓል።
"ብዙ ማጭበርበርና ብዙ ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን ነው ያገኘነው" ብለዋል ትራምፕ ከመስክ ጎን ሆነው። ነገር ግን በማስረጃ አስደግፈው የተናገሩት ነገር አንድም የለም።
ትራምፕና መስክ በዚህ እርምጃቸው ቢያንስ አንድ ትሪሊየን ዶላር የሚሆን፣ የሚባክን ገንዘብ ይገኛል ብለው ያምናሉ።
መስክና እሱ የሚመራው መሥሪያ ቤት የሚወስዳቸው 'ጭፍን" እርምጃዎች በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሜሪካንን ብዙ ዋጋ ያስከፍላታል ብለው ያምናሉ፣ ዲሞክራቶች።
በምክር ቤት የዲሞክራት ፓርቲ ወኪል ቸክ ሹመር፣ "አንድ በሕዝብ ያልተመረጠ ግለሰብ የፌዴራል መንግሥቱን በቁጥጥር ሥር አውሎታል" ሲሉ ወቅሰዋል። ስለሆነም ፓርቲያቸው የዚህን ሰው ተግባር ለማቆም በርትቶ ይሠራል ብለዋል።
ሁለቱም ምክር ቤቶች በሪፐብሊካን መያዛቸው ዲሞክራቶች በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት እንዳይሄዱ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
ኢሎን መስክ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ራሱንና ኩባንያዎቹን እያበለጸገ ነው።
የጥቅም ግጭት አለ በሚል ለተነሳው ጥያቄ ዶናልድ ትራምፕ "የጥቅም ግጭት በሚኖርበት ጊዜ እሱን ከዚያ ጉዳይ እናነሳዋለን" ብለዋል።
የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ በሠራው የዳሰሳ ጥናት በርካታ አሜሪካዊያን የኤለን መስክን እርምጃ የሚደግፉ ቢሆንም በተሰጠው ሥልጣን ገደብ አልባነት ግን ደስተኞች አይደሉም።
ትራምፕን በተመለከተ ደግሞ ብዙ አሜሪካዊያን በጠቅላላው በመንግሥታቸው እየተወሰደ ያለው እርምጃ ደጋፊ ቢሆኑም 66 በመቶ የሚሆኑት ግን የሸቀጦችን ዋጋ በማስተካከል ላይ ቅድሚያ ትኩረት እንዲያደርጉ ይሻሉ።
ኢሎን መስክ እስከአሁን እየወሰደ በሚገኘው እርምጃ ከፍተኛ ተጎጂ ሆኗል የተባለው ዩኤስአይድ ነው።
ማክሰኞ የዚህ መሥሪያ ቤት ተቆጣጣሪ ጄኔራል የሆነ ግለሰብ የኤለን መስክን ተግባር መተቸቱን ተከትሎ ወዲያውኑ ከሥራው ተባሯል።
ግለሰቡ የዚህ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የግዳጅ ፈቃድ እንዲወጡ መደረጉና አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታደርጋቸው የድጋፍ ሥራዎች በድንገት መቋረጣቸው ትክክል እንዳልሆነ የሚያትት ሪፖርት ማሰራጨቱን ተከትሎ ነው እርምጃው የተወሰደበት።












