ትራምፕ አሜሪካ ጋዛን እንደምትወስድ በድጋሚ አረጋገጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ ጋዛ በአሜሪካ እጅ ትሆናለች አሉ።
ትራምፕ ይህን ያሉት ትናንት በቤተ መንግሥታቸው የዮርዳኖስን ንጉሥ ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።
ትራምፕ ሁለት ሚሊዮን የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ግብጽና ዮርዳኖስ እንሰዳቸዋለን ብለው አወዛጋቢ ሐሳብ ካቀረቡ በኋላ አንድ የአረብ አገር መሪ በአካል አግኝተው ሲያነጋግሩ ንጉሥ አብደላህ የመጀመርያው ናቸው።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም በሰጡት ሌላ መግለጫ 'ጋዛን እንገዛታለን" ብለው ነበር።
በዚህ በትናንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ደግሞ 'ጋዛን በገንዘብ አንገዛትም፤ ግን የኛ እናደርጋታለን" ሲሉ የራሳቸውን የቀድሞ ሐሳብ ተቃርነዋል።
ግብጽና ዮርዳኖስ የጋዛን ነዋሪ አንቀበልም ብለው መግለጫ ካወጡ በኋላ ትራምፕ ይህን የማያደርጉ ከሆነ ለሁለቱ አገሮች የምንሰጠውን በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ እናስቀራለን ብለው መዛታቸው ይታወሳል።
ግብጽና ዮርዳኖስ ከእስራኤል ቀጥሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛውን የአሜሪካ የቀጥታ ወታደራዊ እርዳታ የሚያገኙ አገራት ናቸው።
በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ቁልፍ አጋር የሆነችው ዮርዳኖስ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን ስደተኞች መኖርያ ናት።
ንጉሥ አብደላህ አገራቸው የፍልስጤማዊያንን መፈናቀል በማንኛውም መልኩ አትደግፈውም ብለው ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ ከንጉሥ አብደላህ ጎን ሆነው ትናንት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ጋዛን የመጠቅለሉን ጉዳይ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
"ጋዛን እንወስዳታለን፣ እንቆጣጠራታለን፣ ውብ እናደርጋታለን" ብለዋል።
በርካታ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ሆቴሎችን፣ መኖርያ ቤቶችና ቢሮዎችን በጋዛ እንደሚገነቡም ፍንጭ ሰጥተዋል።
በዚህም ለዮርዳኖስ ዜጎችና ለሌሎች ብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።
የሪልስቴት ባለሃብት ስለሆኑ በግላቸው ጋዛን የማልማት ሐሳብ እንደሌላቸው ግን ጠቁመዋል።
ትራምፕ ይህን ሲናገሩ ከጎናቸው የነበሩት ንጉሥ አብደላህ ቃል ትንፍሽ ሳይሉ የማይዋጥላቸውን ነገር ለመስማት ተገደው ታይተዋል።
የትራምፕ ንግግር አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ የምትከተለውን ፖሊሲ የሚቃረንና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ሁሉ የጣሰ ነው።
የዮርዳኖሱ ንጉሥ በጋዜጠኞች ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢሰነዘርባቸውም "ለሁሉም መልካም የሆነ አማራጭ እናፈላልጋለን" የሚል ድፍን ያለ ሐሳብ ከመስጠት ባሻገር የትራምፕን ቃል በቀጥታ ለመቃረን አልደፈሩም።
ከዚያ ይልቅ ሁለት ሺህ የታመሙ ፍልስጤማዊያን ሕጻናትን አገራቸው ወስዳ ታሳክማለች ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ዮርዳኖስና ግብጽ ከጋዛ የምናስወጣቸውን ነዋሪዎች ወስደው ያኖራሉ ሲሉ በድጋሚ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል።
አንዲት ጋዜጠኛ ትራምፕን 'የፍልስጤምን ሕዝብ የት ቦታ ለማስፈር ነው የሚፈልጉት?' በሚል ጥያቄ ያነሳች ሲሆን ትራምፕ በሰጡት ምላሽ "ቁራሽ መሬት ከግብጽ፣ ቁራሽ መሬት ደግሞ ከዮርዳኖስ አድርገን...ሌላም ቦታ ቢሆን እዚያና እዚህ እናኖራቸዋለን" ብለዋል።
በዚህ ወቅት ንጉሥ አብደላህ በማቀርቀር ዝምታን መርጠዋል።
ከዚህ መግለጫ በኋላ ግን ንጉሥ አብደላህ በኤክስ ገጻቸው፣ ከትራምፕ ጋር የነበራቸው ቆይታ 'ገንቢ' እንደነበር ከጠቀሱ በኋላ ፍልስጤማዊያንን የማፈናቀሉ ሐሳብ ግን ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመዋል።
"ይህ የዮርዳኖስ ብቻ ሳይሆን የአረቡ ዓለም በጠቅላላ አቋም ነው" ብለዋል።
ጨምረውም፣ "ጋዛን መልሶ መገንባት መተግበር ያለበት ፍልስጤማዊያንን በማያፈናቅል መልኩ ነው" ብለዋል።
እስራኤል አገር ሆና በፈረንጆቹ 1948 ዓ/ም ስትመሠረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን ከገዛ መሬታቸው ተፈናቅለዋል።
መሬታቸውን በእስራኤል ካጡ በኋላ እነዚህ ፍልስጤማዊያን የተሰደዱት ወደ ዮርዳኖስ ነው። አሁንም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃይ ፍልስጤማዊያን በዮርዳኖስ በስደት ይኖራሉ።
ዮርዳኖስ ፍልስጤማዊያን ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ሶሪያዊያን ስደተኞችም ይኖሩባታል።
አገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ የአሜሪካ የኢኮኖሚና ወታደራዊ ድጋፍ ጥገኛ ናት።
ትራምፕ በትናንቱ መግለጫቸው "ፍልስጤማዊያንን ወደ'ሚያምር ቦታ እንወስዳቸዋለን፣ ሐኪም ወዳለበት፣ ሕክምና ወደሚያገኙበት፣ በሐሴት ወደሚኖሩበት ስፍራ..." ብለዋል።
ንጉሥ አብደላህ የትራምፕን ሐሳብ ይቀበሉታል ወይ? ተብለው በትናንቱ የዋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት መግለጫ ላይ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ "ነገሩን እየመከርንበት ነው፤ ግብጽም ሐሳቧን ታቅርብና የምናየው ይሆናል" ሲሉ ጥያቄውን አልፈውታል።
ምናልባት ግብጽ የምታቀርበው ሐሳብ ጋዛን ከነዋሪዎቿ ጋር ሆኖ ማስተዳደር ሊሆን ይችላል የሚሉ መረጃዎች አሉ።
ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤሉ ቤኒያሚን ናታንያሁ ጋር ከመከሩ በኋላ ነበር ለመጀመርያ ጊዜ ጋዛን አሜሪካ እንደምትወስዳት የተናገሩት።
ከዚያ በኋላ ይህንኑ ሐሳባቸውን በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን "ጋዛን በገንዘብ ገዝተን መልሰን እንገነባታለን " ብለው ነበር።
ከሰሞኑ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት የጋዛ ነዋሪዎች ሌላ ቦታ እንደሚወሰዱና ዳግም ወደ ጋዛ መመለስም እንደማይፈቀድላቸው በማያሻማ ሁኔታ አስረድተዋል።
"ሌላ ቦታ ቋሚ መኖርያ እናዘጋጅላቸዋለን" ብለዋል።












