የትራምፕ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን የማስቀረት ውሳኔ ይጸናል? የኢትዮጵያ እና የሌሎች ሀገራት ሕጎች ምን ይላሉ?

ፕሬዝደንት ትራምፕ ያስተላለፉት ትዕዛዝ ከሕግ ወጥ ስደተኞች አሜሪካ ውስጥ የሚወለዱ ሕፃናት ዜግነት እንዳያገኙ ይከለክላል።
እርግጥ ነው ይህ ውሳኔያቸው ሕጋዊ ጋሬጣ አጋጥሞታል። ነገር ግን በርካታ ስደተኞች ሁኔታው አስግቷቸዋል።
160 ዓመት የሞላው የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት 14ኛው አንቀፅ እንደሚያትተው ማንኛውም አሜሪካ ውስጥ የተወለደ ሰው ዜግነት የማግኘት መብት አለው።
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን የመጡት ትራምፕ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ከሀገራቸው ለማባረር ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ።
ሕጋዊ ባልሆነ መንገድም ሆነ በጊዜያዊ ቪዛ ወደ አሜሪካ የመጡ ወላጆች ልጆቻቸው ዜግነት ማግኘት የለባቸውም የሚል ትዕዛዝ አውጥተዋል።
ይህ እርምጃቸው ከሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል። ኤመርሰን ኮሌጅ ያሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው አሜሪካውያን ይህን የትራምፕ ሐሳብ በአብዛኛው ይደግፉታል።
ለመሆኑ ሌሎች ሀገራት ዜግነት የሚሰጡት እንዴት ነው?

በመወለድ የሚገኝ ዜግነት
አንድ አገር ግዛት ውስጥ በመወለድ የሚገኝ ዜግነት በላቲን 'ጁስ ሶይል' እየተባለ የሚታወቅ የዜግነት አሰጣጥ በዓለማችን ብዙም የተለመደ አይደለም።
ዩናይትድ ስቴትስ በመወለድ ዜግነት ከሚሰጡ 30 ሀገራት መካከል አንዷ ናት። አብዛኞቹ በመወለድ ዜግነት የሚሰጡ ሀገራት የሚገኙት በደቡብ እና ሰሜን አሜሪካ ነው።
በተቃራኒው በእስያ፣ በአውሮፓ እና በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ዜግነት የሚሰጠው በደም ትስስር አሊያም በሥጋ ዝምድና ነው። ይህ ማለት ሕፃናት ዜግነት የሚወርሱት ከወላጆቻቸው ነው ማለት ነው።
አንዳንድ ሀገራት ደግሞ ሁለቱንም መንገዶች አጣምረው ይጠቀማሉ። ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ላላቸው ወላጆች ልጆች ዜግነት የሚሰጡም አሉ።
ጆን ስክሬትኒ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር ናቸው። እሳቸው እንደሚያብራሩት በመወለድ የሚገኝ ዜግነት በደቡብ እና ሰሜን አሜሪካ የተለመደ ቢሆንም "እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆነ አሠራር" አለው።
"ለምሳሌ አንዳንድ ሀገራት ባሪያዎችን አካተዋል። አንዳንዶች አላካተቱም። ታሪኩ በጣም ውስብስብ ነው" ይላሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ ሕገ-መንግሥት 14ኛው አንቀፅ እንዲካተት የተደረገው ከባርነት ነፃ የወጡ ሰዎችን የዜግነት መብት እንዲያገኙ ለማስቻል ነው።
አንዳንድ ሀገራት በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን ተጠቅመው "የሚፈልጉት አካተው፤ የማይፈልጉትን ትተዋል" የሚሉት ምሑሩ ይህ የዜግነት አሰጣጥ በርካቶች ከአውሮፓ ተሰደው እንደሚጡ እንዳበረታታ ይናገራሉ።
ውሳኔው "ጥንታዊ ሕዝቦች እና ከባርነት ነፃ የወጡ ሰዎች እንዲሁም ልጆቻቸው ሀገር አልባ እንዳይሆኑ የተካተተ ነው። ለጊዜው የሚመጥን ስትራቴጂ ነው። ያ ጊዜ ግን አልፏል።"
ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዴት ይገኛል?
የኢትዮጵያዊ ዜግነት በሁለት መንገዶች የሚገኝ ሲሆን እነዚህም ከኢትዮጵያዊ ወላጆች በመወለድ እና ጥያቄ ቀርቦ በሕግ አማካኝነት የሚገኙ ናቸው።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 7(1) እንደሰፈው እናት እና አባት ወይም ከሁለቱ አንዳቸው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ካላቸው የሚወለዱት ልጆች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያገኛል፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ዜግነት የሚገኘው በአገሪቱ ግዛት ውስጥ በመወለድ ሳይሆን፣ ከወላጆች መካከል ቢያንስ አንዳቸው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ሲኖራቸው ነው።
ሌላው ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሚገኝበት መንገድ የሀገሪቱን ዜግነት ከሚፈልጉ ሰዎች በሚቀርብ ሕጋዊ ጥያቄ መሠረት መንግሥት በሚሰጠው ውሳኔ ጠያቂዎች ቃለ መሐላ ፈጽመው በሕግ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፖሊሲ ለውጥ
በቅርብ ዓመታት በርካታ ሀገራት የዜግነት ሕጋቸውን መከለስ ጀምረዋል። አንዳንዶች ደግሞ በስደተኞች ምክንያት በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን አንስተዋል።
በመወለድ የሚገኝ ዜግነት መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች "የውልደት ቱሪዝም" እንዲስፋፋ አድርገዋል። ይህ ማለት አንድን ሀገር የሚጎበኙት ወላጆች ዜግነት ለማግኘት ብቻ ነው ማለት ነው።
ሕንድ በአንድ ወቅት በምድሯ ለሚወለዱ ሕፃናት ዜግነት ትሰጥ ነበር። ነገር ግን በተለይ ከባንግላዴሽ የሚመጡ ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ ይህ ሕግ እንዲቀር ተደርጓል።
ከአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2004 ጀምሮ ሕንድ የሚወለዱ ሕፃናት ዜግነት የሚያገኙት ሁለቱም ወላጆች ሕንዳውያን ከሆኑ ነው። አሊያም ከወላጆች መካከል አንዳቸው ሕንዳዊ ሆነው አንዳቸው ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኛ ቢሆኑ እንኳን ዜግነት ለማግኘት በቂ ነው።
በቅኝ ግዛት ዘመን በመወለድ የሚገኘው ዜግነት ይሰጡ የነበሩት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ይህን ሕግ ከሥራ ውጪ አድርገውታል። በአሁኑ ወቅት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ዜግነት ለመስጠት ቢያንስ ከወላጆች መካከል አንዳቸው ዜጋ አሊያም ቋሚ ነዋሪ መሆን አለባቸው ይላሉ።
በእስያ ሀገራት የዜግነት ጉዳይ እጅግ ጥብቅ ሲሆን፣ የሚወሰነው ወላጆች የአገሪቱ ዜጋ በመሆናቸው ላይ ነው። ቻይና፣ ማሌዥያ እና ሲንጋፖር ይህን መንገድ ነው የሚከተሉት።
በአውሮፓም የዜግነት ሕግ እየተቀየረ መጥቷል። አየርላንድ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን በመተው ከአውሮፓ ሀገራት የመጨረሻዋ ናት።
ሰኔ 2004 (እአአ) በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ 79 በመቶ የአገሪቱ ዜጎች ሕገ-መንግሥቱ ይቀየር የሚል ድምፅ ሰጥተዋል። ይህን ተከትሎ የአየርላንድ ዜግነት ለማግኘት ከወላጆች መካከል ቢያንስ አንዳቸው ዜግነት ያላቸው አሊያም ቋሚ ነዋሪ እንዲሁም ሕጋዊ ጊዜያዊ ነዋሪ መሆን አለባቸው።
መንግሥትን ይህን ሕግ የቀየረው የውጭ ሀገራት ሴቶች ወደ አየርላንድ በመምጣት ልጅ በመውለድ የአውሮፓ ሕብረት ፓስፖርት እያገኙ በመሆኑ ነው ብሏል።
በአውሮፓውያኑ 2010 ዶሚኒካን ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥቷን በማሻሻል ሕጋዊ ካልሆኑ ስደተኞች የተገኙ ልጆች ዜግነት እንዳያገኙ ከልክላለች።
ከሦስት ዓመታት በኋላ ደግሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አብዛኞቹ ከሄይቲ የመጡ ስደተኞች ዜግነታቸው እንዲነጠቅ ወስኗል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በወቅቱ ይህን ውሳኔ አጥብቀው ተቃውመውት ነበር።
ይህን ተከትሎ በ2014 ዶሚኒካን ሪፐብሊክ ከሕገ-ወጥ ስደተኞች ለተወለዱ ሕፃናት ዜግነት ሰጥታለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሕጋዊ ፈተና
ይህንን በአሜሪካ ግዛት ውስጥ በመወለድ የሚገኘውን የዜግንት መብት የሚያስቀረውን ውሳኔ ፕሬዝደንት ትራምፕ ያስተላለፉት ሥልጣን በያዙ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ነው። የእሳቸውን ውሳኔ ተከትሎ በዲሞክራቶች የሚመሩ ግዛቶች እና ከተሞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ግለሰቦች ክስ መሥርተዋል።
ሁለት የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች የፕሬዝዳንቱን ውሳኔ በመቃወም አቤቱታ ያቀረቡ ከሳሾች ሐሳብ ደግፈዋል። የሜሪላንድ ግዛት ዳኛ የሆኑት ዴብራ ቦርድማን አንዷ ናቸው።
ዳኛዋ አምስት ነፍሰጡር ሴቶች የፕሬዝደንቱ ውሳኔ ሕገ-መንግሥቱን የጣሰ ነው ብለው ያቀረቡት ክስ ተቀባይነት አለው ብለዋል ድጋፍ ሰጥተዋል።
በርካታ የሕግ አዋቂዎች ፕሬዝደንት ትራምፕ ሕገ-መንግሥቱ የሰጠውን በመወለድ የሚገኝ ዜግነት በእሳቸው ትዕዛዝ ውድቅ ማድረግ አይችሉም ሲሉ የውሳኔውን የመጽናት ዕድል ጥያቄ ውስጥ አስገብተውታል።
የትራምፕ ትዕዛዝ በፍርድ ቤት ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ ለጊዜው ተግባራዊ አይደረግም።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን ጉዳይ ተመልክቶ የሚሰጠው ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ እየተጠበቀ ነው። ነገር ግን ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች መካከል አብዛኞቹ ወግ-አጥባቂ በመሆናቸው ትራምፕ ያሳለፉትን ትዕዛዝ ሊደግፉ ይችላሉ እየተባለ ነው።












