ከአሜሪካ 'እንባረራለን' በሚል ስጋት የተደበቁት አፍሪካዊ ስደተኞች እና የኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ የከለላ መብት

ሕገ ወጥ ስደተኞች ቀን ተሌት በፖሊስ እየታደኑ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሕገ ወጥ ስደተኞች ቀን ተሌት በፖሊስ እየታደኑ ነው

የትራምፕ ውሳኔ ያስጨነቃቸው በአሜሪካ የሚገኙ ስደተኞች ከዛሬ ነገ እንባረራለን በሚል ፍርሃት ከቤት ለመውጣት እንደፈሩ ለቢቢሲ ተናገሩ።

አንዳንዶቹ አልፎ አልፎ ካልሆነ ሥራ መሄድ አቁመናል ብለዋል።

ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት አስወጥተዋል።

ካዱሊ አሜሪካ የገባው ከ11 ዓመት በፊት ነው።

ትውልዱ ከኮንጎ ነው። አሁን አማጺያን በቁጥጥራቸው ሥር ካደረጓት ጎማ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ መንደር ነው የተወለደው።

ጠቅላላ ሐኪም ነበር። የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላን በመተቸቱ በመንግሥት ሲሳደድ ጊዜ ነው ወደ አሜሪካ ያቀናው።

ካዱሊ ትራምፕ ከመጡ ጀምሮ በፍርሃት ቆፈን ነው እየኖረ ያለው። ገበያ ለመውጣት እንኳ ይፈራል። የትራምፕ ሰዎች አፍነው ወደመጣሁበት ይመልሱኛል ብሎ ነው የሚሰጋው።

"የአሁኑ አሰሳ ፍርሃት ለቀቀብን፤ ሁሉም ስደተኛ ወንጀለኛ ነው የሚመስላቸው" ይላል።

ይበልጥ ፍርሃት ውስጥ የከተተው የትውልድ አገሩ ኮንጎ አሁንም ድረስ በጦርነት ውስጥ መሆኗ ነው። በዚህ ወቅት አንድን ሰው ወደ ኮንጎ-ጎማ እንዲመለስ ማስገደድ የሞት ፍርድ ነው ይላል።

አብያተ ክርስቲያናትና ሆስፒታሎች እየተበረበሩ ነው

አብዱል ናይጄሪያዊ ነው። ከ30 ዓመት በፊት ከአባቱ ጋር ወደ አሜሪካ መጣ።

ያን ጊዜ ገና 10 ዓመቱ ነበር።

ትራምፕ ከመጡ ወዲህ በዊስኮንሰን ግዛት በፍርሃት ይኖራል።

"ደጅ ለመውጣት ፈራሁ። አላህ እንዲጠብቀኝ እና ነገን መልካም እንዲያደርግልኝ ነው ጸሎቴ" ይላል።

አብዱል በምህጻሩ አይስ የሚባለው የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን መኰንኖች በከተሞች ስደተኛ ሲያሳድዱ በሩቅ ተመልክቷል።

የእኔም ዕጣ ፈንታ ከዚህ አይለይም ብሎ ይፈራል።

"ብታያቸው እኮ በቃ ሰው የሚያድኑ አይመስሉም። ስደተኛም እኮ ሰው ነው። ሁላችንም ሰው ነን። ደማችን ቀይ ነው።"

ለዚህ ዘገባ ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ስደተኞች ዒላማ እንዳይሆኑ በመስጋት ሙሉ ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈቀዱም።

በጭንቅ የተነሳ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩ ወላጆች አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጭንቅ የተነሳ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩ አፍሪካዊያን ወላጆች አሉ

የትራምፕ አስተዳደር ቃል በገባው መሠረት ሰነድ አልባ ስደተኞችን በእግር በፈረስ እያሳደደ ወደ ማጎርያዎች እያጋዘ ነው።

'አይስ' መኰንኖች፣ ስደተኞቹን ከትምህርት ቤት፣ ከአብያተ ክርስቲያናት እና ከሆስፒታሎች ጭምር እየያዟቸው ነው።

የወንጅል ታሪክ ያለበትም፣ የሌለበትም በሺህ የሚቆጠር ስደተኛ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

በቀን ከሺህ በላይ ስደተኛ በቁጥጥር ሥር እንደሚያውል አይስ አስታውቋል።

ካነጻጸርነው የጆ ባይደን አስተዳደር በቀን በአማካይ 311 ስደተኞችን ነበር በቁጥጥር ሥር በማዋል ወደመጡበት ይመልስ ነበረው። ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ወንጀለኞች የነበሩ ናቸው።

ይህ አሁን በትራምፕ አስተዳደር በብዙ እጥፍ ጨምሯል። በቅርቡ በምክር ቤት ሕግ ሆኖ የጸደቀው የወንጀል ታሪክ ያላቸው መጤዎችን "ጠርዞ የመላክ ሕግ" ለፖሊሶች ሰፊ ሥልጣንን ሰጥቷል።

አንዱ የሰጣቸው ሥልጣን ስደተኞቹ በተያዙበት ቅጽበት ሳይውል ሳያድር ከአገር እንዲባረሩ ማድረግ መቻሉ ነው። ይህ ቀደም ባለው ጊዜ በጦርነት ወቅት ካልሆነ እንዲያ ማድረግ የሚቻል አልነበረም።

ፒየስ አሊ የፖርትላንድ ፖሊስ አማካሪ ናቸው። በእርሳቸው አስተያየት ሕጉ ላልተፈለገ ተግባር እየዋለ ነው።

ለምሳሌ ትምህርት ቤቶች፣ አብያተ ክርስቲያናት እና ሆስፒታሎች ጭምር እየገቡ ስደተኛን ማሳደድ ተገቢ አይደለም ይላሉ።

ሁሉንም ስደተኛ እንደ ወንጀለኛ መቁጠሩም ሕጉ እየተበዘበዘ ስለመሆኑ እንደ ማስረጃ ያቀርቡታል።

ለስደተኞች ያላቸው ምክር፣ "ቤታችሁ ተንኳኩቶ ፖሊሶች ከሆኑ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወደ ውስጥ መግባት አትችሉም በሏቸው" ይላሉ።

"ለማንኛውም የሚሆነው አይታወቅምና ለቤተሰብ ምግብ እና ገንዘብ ከወዲሁ መተው መልካም ነገር ነው" ይላሉ።

የኢትዮጵያውያን "ጊዜያዊ ከለላ መብት" መቼ ያበቃል?

ሶማሊያዊያን ከሚባረሩ የአፍሪካ ስደተኞች በቁጥር ላቅ ያሉ ናቸው
የምስሉ መግለጫ, ሶማሊያዊያን ከሚባረሩ የአፍሪካ ስደተኞች በቁጥር ላቅ ያሉ ናቸው

ብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች በእንጥልጥል-በጭንቅ ነው የሚኖሩት። ይህም የሆነው በ"ጊዜያዊ ከለላ መብት" (Temporary Protected Status) ምክንያት ነው።

ይህ መብት ለተወሰኑ አገር ስደተኞች የተሰጠ ልዩ መብት ነው። እነዚህ አገሮች የእርስ በርስ ጦርነት እና ሌሎች አስከፊ ሁኔታዎች ያሉባቸው ናቸው።

ይህ ልዩ መብት ከእነዚህ አገራት የመጡ ዜጎች በጊዜያዊነት አሜሪካ መቆየት እና ሥራ ማመልከትን ያጎናጽፋል።

እስከ ዛሬ በዚህ ልዩ መብት ተጠቃሚ የሆኑ ስደተኞች ይህ መብት እስከመቼ ይዘልቃል በሚል ፍርሃት ላይ ናቸው።

አንዳንቹ ባይደንን ይወቅሳሉ።

ለምሳሌ ጆ ባይደን አንጎላ እና ኮንጎን ሲጎበኙ ይህን መብት ከዚያ ለመጡ ስደተኞች ያራዝማሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎ ነበር።

ባይደን ግን ይህንን ሳያደርጉት ነጩን ቤተ መንግሥት ተሰናበቱ።

ይህ ጊዜያዊ መብት ሲያበቃ አፍሪካውያኑ ሊባረሩ ይችላሉ ማለት ነው።

ከ17 አገራት የመጡ አንድ ሚሊዮን ስደተኞች በዚህ ጊዜያዊ የከለላ መብት በአሜሪካ እየኖሩ ነው። ከ17ቱ አገሮች አምስቱ የሚገኙት በአፍሪካ ነው።

አሜሪካ ለካሜሮን፣ ለደቡብ ሱዳን እና ለኢትዮጵያ ዜጎች የሰጠችው ልዩ የከለላ መብት በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ያበቃል። የሶማሊያ እና የሱዳን ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት ይጠናቀቃል።

ጊዜው ሲያበቃ የትራምፕ አስተዳደር የእነዚህን አገራት ዜጎች ሊያባርሯቸው ይችላል የሚል ስጋት ረብቧል።

የስጋት እንቅልፍ

በቅርብ ዓመታት አፍሪካውያን በሜክሲኮ ድንበር በኩል ወደ አሜሪካ በብዙ ቁጥር ገብተዋል። ይህ የሆነው በሜዲትራኒያን አድርጎ ወደ አውሮፓ መግባት አደገኛ እየሆነ በመምጣቱ ነው።

አይስ በ2024 ባወጣው ዘገባ በተጠቀሰው ዓመት 1818 አፍሪካውያን ከአሜሪካ ተባረዋል። ሴኔጋል፣ ሞሪታኒያ እና ናይጄሪያ ይመራሉ።

ሆኖም በ2024 አንዲባረሩ በአይስ ዕቅድ ከተያዘላቸው 1.4 ሚሊዮን ስደተኞች የአፍሪካውያን ድርሻ 3 በመቶ ብቻ ነው።

ከእነዚህም መካከል ሶማሊያውያን በቁጥር የሚስተካከላቸው የለም። 4090 ናቸው። የሞሪታኒያ፣ ናይጄሪያ እና የጋና ዜጎች ደግሞ ይከተላሉ።

አንድ ባለሙያ እንደሚሉት ይህ አጋጣሚ ለአፍሪካ መሪዎች ትልቅ ዕድል ሊሆን ይችላል።

"ለስደት የሚጋብዙ በሮችን መዝጋት፣ ዜጎች የሚለውጡበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል" ይላሉ።

ምናልባት አሜሪካ ለስደተኞች ጨርሶውኑ በሯን ከዘጋች ቻይና፣ ሩሲያ እና ተገዳዳሪ አገራት ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብለው ያስባሉ።

"እነዚህ አገራት ከአፍሪካ ጋር በጋራ በመሥራት፣ ሕጋዊ የስደት መስመርን በመዘርጋት፣ የኢኮኖሚ ትብብር በመፍጠር፣ ንግድን በማሳለጥ አዲስ ግንኙነት ከጀመሩ፣ የአፍሪካ እና የአሜሪካ ግንኙነት ከዚህ ቀድሞ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሊቀየር ይችላል።"

ከአስራ አንድ ዓመታት በፊት ከኮንጎ የተሰደደው ሐኪም ካዱሊ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ መልዕክት አለው።

"ትራምፕ ሰብአዊነትን ከፖለቲካ ሊያስቀድሙ ይገባል፤ አሜሪካ ታላቅነቷን መልሳ የምትጎናጸፈው ያኔ ነው።"