ትራምፕ የተወሰኑ ስደተኞችን ወደ ጓንታናሞ ቤይ እንደሚልኩ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጓንታናሞ ቤይ እስከ 30,000 ሰዎች የሚይዝ የስደተኞች ማቆያ ማዕከል እንዲገነባ አዘዙ።
በኩባ በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ መቀመጫ ጓንታናሞ ቤይ ከሚገኘው ወታደራዊ እስር የተለየ ማቆያ እንደሚሆን ገልጸዋል።
"አስከፊ የሆኑትና አሜሪካን የሚያሰጉት ሕገ ወጥ ስደተኞችን የሚይዝ ይሆናል" ብለዋል።
በጓንታናሞ ቤይ ስደተኞችን ማቆየት ከዚህ በፊትም የሚደረግ ነበር። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድርጊቱን ይተቻሉ።
ትራምፕ በስደተኞች ጉዳይ የሾሟቸው ቶም ሆማን እንዳሉት የአገሪቱ የስደተኞችና ጉምሩክ ተቋም አይስ እየተጠቀመበት ያለው ማዕከል ማስፋፊያ ይደረግበታል።
ስደተኞች በአሜሪካ የባሕር ኃይል ተይዘው ወደማቆያው በቀጥታ እንደሚወሰዱና "ከፍተኛ" እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።
ማዕከሉ መቼ እንደሚገነባና ምን ያህል እንደሚያስወጣ አልታወቀም።
የኩባ መንግሥት የትራምፕን ዕቅድ ኮንኗል። አሜሪካ "በይዞታ" በተቆጣጠረችው መሬት በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን እያገተችና እያሰቃየች ነው ሲልም ከሷል።
'ላኪን ሪሌይ አክት' የተባለውን ሕግ ትራምፕ ከፈረሙ በኋላ ነው ውሳኔውን ያሳለፉት።
ሰነድ አልባ ስደተኞች በስርቆት ወይም ነውጥ ከታሰሩ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ሆነው ይከታተላሉ።
ሕጉ የተሰየመው አምና በቬንዝዌላዊ ስደተኛ በተገደለች የጆርጅያ የነርስ ተማሪ ስም ነው። ሕጉ በኮንግረስ ጸድቋል።
በዋይት ሀውስ ሕጉ ላይ ትራምፕ ፈርመዋል። መከላከያ ሚኒስቴርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ጉዳይ 30ሺህ ሰዎች የሚይዘውን ማቆያ ማዘጋጀት እንዲጀምሩ አዘዋል።
"አንዳንዶቹ በጣም መጥፎ ከመሆናቸው የተነሳ አገሮቻቸው ይይዟቸዋል ብለን አናስብም። እንዲመለሱ ስለማንፈልግ በጓንታናሞ ቤይ እንይዛቸዋለን። ከዚያ አምልጦ መውጣት ቀላል አይደለም" ብለዋል።
ማቆያው አሜሪካ ሰነድ አልባ ስደተኞችን የምትይዝበትን መጠን በሁለት እጥፍ ይጨምራል ተብሏል።
ጓንታናሞ ማይግራንት ኦፕሬሽንስ ሴንተር የተባለ መሥሪያ ቤት በጓንታናሞ ቤይ ይገኛል። ለአሥርታት በዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች አመራርም ስደተኞችን ማቆያም ሆኗል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች መብት ተሟጋች ኢንተርናሽናል ሬፍዩጂ አሲስታንስ ፕሮጀክት፣ ስደተኞችን ባሕር ላይ ይዞ "በኢ-ሰብአዊ" መንገድ በማቆየት አሜሪካን ይከሳል።
በአሜሪካ ለመረጃ ነጻነት የሚታገለው ተቋም ስለ ማቆያው ሁኔታ ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ ጠይቋል።
የጆ ባይደን አስተዳደር ሰዎችን ይዞ ማቆያ አይደለም ቢልም ትራምፕ እንደ ማቆያ መጠቀም ይፈልጋሉ።
የአገር ውስጥ ደኅንነት ጸሐፊ ክሪስቲ ኖአም ለማቆያው ግንባታ ገንዘብ የሚመደበው "በስምምነትና በተገቢው መንገድ" ነው ብለዋል።
ወታደራዊ እስር ቤቱ በ9/11 የሽብር ጥቃት የተያዙን ጨምሮ በርካታ እስረኞችን ከ2001 ጀምሮ የያዘ ነው።
ባራክ ኦባማን ጨምሮ ሌሎችም መሪዎች ለመዝጋት ቃል ገብተው ነበር።
15 እስር ቤቶች ያሉት ሲሆን ኩባ በቦታው የአሜሪካ ወታደራዊ መቀመጫ መኖሩን ትነቅፋለች። ፊደል ካስትሮ በ1959 ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ አሜሪካ ቦታውን "በይዞታዋ ሥር አድርጋዋለች" ስትል ኩባ ትከሳለች።
የኩባ ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካናል በኤክስ ገጻቸው "አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት በጭካኔ ሰዎችን በጓንታናሞ እንደሚይዝ ተናግሯል። ቦታው በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘ የኮባ ግዛት ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ለስቃይና ሕገ ወጥ ይዞታ ሊዳረጉ ነው" ብለዋል።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪገዝ ውሳኔው "ለሰብአዊ ይዞታና ዓለም አቀፍ ሕግ ያለውን ንቀት" የሚያሳይ ነው ሲሉ ተችተዋል።












