የመቀለ ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያን ለመቆጣጠር የተደረገው ሙከራ እና የተፈጠረው ውዝግብ

የፎቶው ባለመብት, mekele fm/fb
በትግራይ ክልል በህወሓት አመራሮች መካከል ያለውን የሥልጣን አለመግባባትን ተከትሎ አንድ የፓርቲው አባል በአምስት ታጣቂዎች በመታገዝ በዋና ከተማዋ መቀለ የሚገኝ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራን ተከትሎ ለሰዓታት የዘለቀ ውዝግብ ተከስቶ እንደነበር የጣቢያው ሠራተኞች እና ፖሊስ ለቢቢሲ አረጋገጡ።
ረቡዕ ጥር 21/2017 ዓ.ም. ረፋድ ላይ አንድ የፀጥታ ኃላፊ እና አምስት ታጣቂዎችን ይዞ ወደ መቀለ 104.4 ኤፍ ኤም ጣቢያ የደረሰው ግለሰብ ጣቢያውን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት መክሸፉን የጣቢያው ሠራተኞች ቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአምስት ታጣቂዎች ጋር ወደ ጣቢያው ያመራው ግለሰብ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ የሚባል የህወሓት አባል ሲሆን፣ ጣቢያውን ለማስተዳደር በመቀለ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ረዳኢ "ተሹሚያለሁ" እንዳለ ተገልጿል።
ዶክተር ረዳኢ በዶክተር ደብረጽዮን በሚመራው የህወሓት ክንፍ ለመቀለ ከንቲባነት የተሾሙ ሲሆን፣ በክልሉ ጊዜያዊው አስተዳደር ግን ሕገወጥ ከንቲባ ተደርገው ይወሰዳሉ።
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የሬዲዮ ጣቢያው ሠራተኛ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ የተባለው ግለሰብ በታጣቂዎች ታግዞ ወደ ጣቢያው ከዘለቀ በኋላ የተቋሙን ማህተም ከፀሐፊዋ በመንጠቅ ለሠራተኞች ማስታወቂያ መለጠፉን ተናግረዋል።
ስለ ክስተቱ ለቢቢሲ የተናገረ ሌላ የጣቢያው ሠራተኛ ደግሞ በዶክተር ደብረጽዮን በሚመራው የህወሓት ክንፍ ደጋፊ የሆነ ግለሰብ ደብዳቤ እንኳ ሳይዝ ጣቢያውን በኃይል ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጉን አረጋግጧል።
ይህ ግለሰብ እንደሚለው ይህ ክስተት በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ኃይል የትግራይ ቴሌቪዥን እና ድምጸ ወያኔ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ከእጁ ስለወጣ ኤፍ ኤም መቀለን በመሣሪያ ኃይል በመንጠቅ መጠቀሚያ ለማድረግ ያደረገው ሙከራ ነው።
አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ የተባለው ግለሰብ በአምስት ታጣቂዎች በመታገዝ ወደ ጣቢያው ከዘለቀ በኋላ ማህተም በመንጠቅ ለሠራተኞች የስብሰባ ጥሪ ማስታወቂያ መለጠፉን ይህ የጣቢያው ምንጭ ለቢቢሲ ገልጿል።
ሌላ የድርጅቱ ሠራተኛ በበኩሉ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍሰሃ "በዶክተር ረዳኢ የተሾምኩት ትክክለኛው [የጣቢያው] ሥራ አስኪያጅ እኔ ነኝ፣ ሥልጣን አስረክበኝ" በሚል ነባር የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሀለፎም ንርአ እንደጠየቀ ተናግሯል።
"ሥልጣን አስረክበኝ አለው፣ አቶ ሀለፎም ደግሞ ሹመት የሰጠህ ዶክተር ረዳኢ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕገወጥ የተባለ ሰው ስለሆነ ሥልጣን ላስረክብህ አልችልም። ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ደብዳቤ ይዘህ ከመጣህ ግን ሥልጣን አስረክብሃለው አለው፤ በዚህን ጊዜ አቶ ዘመንፈስ ቅዱስ ማኅተብ ከፀሐፊዋ በኃይል አስገድዶ ወስዶ ለጣቢያው ሠራተኞች የስብሰባ ጥሪ ማስታወቂያ ለጠፈ" ብሏል።
ይህን ተከትሎ አቶ ሐለፎም "እኔ እያለሁ ለምን ማህተም ነጥቀህ ማስታወቂያ ትለጥፋለህ? በማለት የተለጠፈውን ማስታወቂያ እንዳነሱት እና በዚህም የተነሳ ውጥረት እንደተፈጠረ ተናግሯል።
ይህ ፍጥጫ ከጠዋቱ 3፡30 እስከ ቀትር 6፡00 ሰዓት የቆየ ሲሆን፣ በመጨረሻ ከቀዳማዊ ወያነ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ተጠርቶ ሁለቱንም ግለሰቦች እና ጣቢያውን ለመቆጣጠር የመጡትን ታጣቂዎች ይዘዋቸው መሄዳቸውን የጣቢያው ሠራተኞች በቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አቶ ዘመንፈስቅዱስ በመቀለ ከተማ ምክትል ከንቲባ ነኝ በሚሉት ዶክተር ረዳኢ መሾማቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ሆኖም በህወሓት መሪዎች በተፈጠረ መከፋፈል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፣ ዶ/ር ረዳኢን በማገድ በምትካቸው አቶ ብርሃነ ገብረ የሱስን መሾማቸው ይታወቃል።
ሆኖም ይህን ሹመት የከተማው ምክር ቤት ውድቅ አድርጎታል።
በአሁኑ ሰዓት መቀለ በሁለቱም ህወሓት ክንፎች የተሰየሙ ከንቲባዎች ቢኖሯትም ላለፉት ሦስት ወራት ያለ ከንቲባ ቆይታለች።
ቢቢሲ የረቡዕ ጠዋቱን ከስተት በተመለከተ ለጣቢያው ነባር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃለፎም እንዲሁም ተሾሚያለሁ ለሚሉት አቶ ዘመንፈስቅዱስ ስልክ ደውሎ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልሰመረም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር አንድነት ነገሰ በበኩላቸው ጣቢያውን ለመቆጣጠር የተደረገውን ሙከራ አረጋግጠው ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።
ኤፍ ኤም መቀለ 104.4 ጣቢያ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሕግ መሠረት በትግራይ ክልል ቴሌቪንዥን ፈቃድ የሚንቀሳቀስ ሆኖ ከተመሠረተ እና 16 ዓመታት ያስቆጠረ የሬዲዮ ጣቢያ ነው።












