'ከአስከሬን ጋር መሥራት ትሑት ያደርጋል' የምትለው የአስከሬን መርማሪ

አስከሬን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማስጠንቀቅያ፡ በዚህ ዘገባ ውስጥ የሟቾች ሁኔታ ዝርዝር ገለጻ ስላለው አንዳንድ ሰዎችን ሊረብሽ ይችላል።

ዶ/ር ሺርሊ ቫሱ በሥራዋ ፈር ቀዳጅ በመሆን በርካታ ሽልማቶችን ተቀብላለች። ነገር ግን ቤተሰቦቿ ከሥራዋ ጋር በተያያዘ ዘወትር ስለ እርሷ ስጋት ይንጣቸዋል።

ለሦስት አስርታት ዶ/ር ቫሱ በአደጋ፣ በፀብ ወይንም በአጠራጣሪ ሁኔታ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን መርምራለች።

ዶ/ር ቫሱ የ33 ሚሊዮን ሕዝቦች መኖርያ በሆነችው እና በደቡብ ሕንድ ግዛት በምትገኘው ኬራላ የአስከሬን ምርመራ ባለሙያ ነበረች።

ይህ ደግሞ በአካባቢዋ የተለመደ የሥራ መስክ አይደለም፤ በተለይ ለሴት። ከሞት ጋር ተያይዞ ባሉ ባሕላዊ አስተሳሰቦች የተነሳ ሴቶች የሞቱ ሰዎች ከሚቃጠሉበት አካባቢ ራሳቸውን ያርቃሉ።

ዶ/ር ቫሱ 20 ሺህ ያህል አስከሬኖችን መርመራለች። ገና የሕይወትን ምንነትን ካላጣጠሙት ጨቅላ ህጻናት እስከ በምርኩዝ የሚሄዱ አዛውንት ድረስ ሞተው አስከሬናቸውን መርምራለች።

የመጀመርያው አስከሬን

ዶ/ር ቫሱ የመጀመርያው አስከሬን ለምርመራ እርሷ ወደምትሥራበት ጠረጴዛ የመጣው እኤአ በ1981 የድኅረ ምረቃ ተማሪ እያለች ነው።

በወቅቱ መምህሯ ከፏፏቴ ስር 13 ሜትር ጥልቀት ውስጥ ገብቶ የሞተን ግለሰብ አስከሬን ራስ ቅል እና የእጁን አጥንቶች እንድትመረምር ጠየቋት።

“አጥንቱ በአጠቃላይ ሥነ ሕይወታዊ ይዘቱን አጥቶ ነበር” ትላለች ዶ/ር ቫሱ ስታስታውስ።

በወቅቱ ከሁለት ሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን ምርመራ ያደረገች ሲሆን፣ ሟች ዕድሜው 14 ወይንም 15 የሚገመት ወንድ መሆኑን፣ የራስ ቅሉ ከጀርባ አጥንቱ ጋር የተገናኘበትን በማየት መለየታቸውን ታስታውሳለች።

የአስከሬን ምርመራ ሪፖርቱ ላይ በወቅቱ የጻፈችው “የእጁ የላይኛው አጥንቶች አካሉን ለመቆራረጥ ታስቦ የተለያየ ስፍራ ተተልትሏል. . . ግድያ ነው የተፈጸመበት” ስትል ነበር ።

ዶ/ር ቫሱ በወቅቱ ካሜራ አልነበራትም። ስለዚህ አጥንቶቹን ወደ ፎቶ ስቱዲዮ በመውሰድ ጠረጴዛ ላይ በመደርደር ፎቶ አስነስታ መሰነድ ነበረባት።

ይሁን እንጂ ፎቶ እንዲያነሳ የተጠየቀው ባለሙያ ደንግጦ ለፖሊስ የድረሱልኝ ጥሪ አሰማ።

የዶ/ር ቫሱ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር፣ ቫሱ ከጥርጣሬ ነጻ እንድትሆን የሆነውን ለፖሊስ ማስረዳት እና የተማሪያቸውን ሥራ ማስረዳት ነበረባቸው።

በወቅቱ ሟች በአካባቢው ነዋሪ የሆነ እና ለ41 ቀናት ጠፍቶ የነበረ መሆኑ ተደርሶበታል።

በግድያ ወንጀሉም የ18 ዓመቱ የአክስቱ ልጅ የተጠረጠረ ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን ማንም በወንጀሉ ሳይጠየቅ ቀርቷል።

የግነዛ ባለሙያ አስከሬኑን በነጭ ጨርቅ በመጠቅለል ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአስከሬን ምርመራ ከተደረገ በኋላ ገናዦች የሟችን በድን ወስደው በነጭ ጨርቅ በመጠቅለል ለቤተሰቦቹ ያስረክባሉ።

በአስከሬን ምርመራ ምን ይከናወናል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአስከሬን ምርመራ ዋነኛ ዓላማ ሟች የሞተበትን ምክንያት እና ሰዓት መለየት ሲሆን፤ እንዲሁም የሟች ማንነት የማይታወቅ ከሆነ ለዚያ የሚረዳ ልየታ ይደረጋል።

ዶ/ር ቫሱ በኮዚህዴ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ክፍልን የተቀላቀለችው እኤአ በ1982 ነው።

በቀን ሁለት ወይንም ሦስት እያንዳንዳቸው 90 ደቂቃ የሚፈጁ የአስከሬን ምርመራዎችን ታከናውናለች።

ሥራ በበዛበት ቀን ደግሞ እስከ ሰባት አስከሬን ለምርመራ ጠረጴዛዋ ላይ ይመጣል።

በተደጋጋሚ የተቃጠለ፣ የተተለተለ፣ የበሰበሰ፣ በመኪና ግጭት አደጋ የሞተ፣ ለመለየት አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ አካላቸው የጎደለ፣ እንዲሁም ከተቀበረበት የወጣ አስከሬን ወደ ስራ ክፍሏ ይመጣል።

ዶ/ር ቫሱ መጀመሪያ ከውጪ በዕይታ የሚለዩ ሥራዎችን እንደሚከናወኑ ትናገራለች።

በዚህም “ጉዳት ካለ፣ ምልክቶች እንዲሁም ለጥርጣሬ የሚጋብዙ ነገሮች ይለያሉ።”

ከዚያ በኋላ ደረት፣ ሆድ እቃ፣ ዳሌ እና ሌሎች ውስጣዊ የአካል ክፍሎች ላይ ምርመራ ይደረጋል።

ይህንንም ለማድረግ እንዲቻል ለምርመራም ከሟች አካል ላይ ናሙና ይወሰዳል።

በስተመጨረሻም የራስ ቅሉ ተከፍቶ አንጎሉ ላይ ምርምራ ይከናወናል።

ሟች በጥይት ተመትቶ ከሆነ የሞተው ጥይቶቹን ለመለየት ሙሉ አካሉ ራጅ ይነሳል።

ሟች የቲቢ ታማሚ ከነበረ ወይንም ደግሞ ለካንሰር ሕክምና የሚሰጥ ጨረራ ለመከላከል የተገጠመለት መሳሪያ ከነበረ አብረዋት የሚሠሩ ሁለቱ ዶክተሮች ተጋላጭነት ለመቀነስ ሥራውን ይካፈላሉ።

ዶ/ር ቫሱ በየዓመት አንድ ወይንም ሁለት የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ሌላኛቸውን ወንጅው ለምርመራ የሟች አስከሬን እንደሚመጣላት ታስታውሳለች።

ይህንንም “የሙያችን አንዱ አካል ነው” ትላለች።

ከረዥም ፋታ በኋላ በሐዘን ስሜት ውስጥ ሆና “ የሕጻናትን አስከሬን ማየት ግን ያሳዝናል” ብላለች።

ዶ/ር ቫሱ ቢቢሲን በዙም ስታዋራ
የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ቫሱ ቢቢሲን በዙም ስታዋራ

“ሕገ ወጥ ጽንስ ማቋረጥ”

ዶ/ር ቫሱ በሰሜን ኬራላ ኮዚኮዴ በምትሠራበት ወቅት የወጣት ነፍሰ ጡር ሴቶች ሞት ቁጥር መጨመሩን አስተዋለች።

እነ ዶ/ር ቫሱ የአስከሬን ምርመራ ሲያደርጉ ያልተለመደ ነገር በማግኘታቸው፣ የነፍሰ ጡሮቹ ሞት ከሕገ ወጥ ጽንስ ማቋረጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን አንደሚችል ጠረጠሩ።

“በማሕጸናቸው ጫፍ ላይ የመቆረጥ ምልክት አገኘሁ” ስትል ታስታውሳለች። “የሕክምና ባለሙያ ጽንስ ሲያቋርጥ እንዲህ ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት ምልክት አይተውም።”

በኋላ በተደረገው ማጣራትም የነፍሰ ጡር ሴቶቹ ሞት በጣም ስቃይ የታከለበት ዩትራይን ሴፕሲስ (Utrine sepsis) መሆኑን አረጋገጥን።

ፖሊስ ባደረገው ምርመራም እርሷ በምትሰራበት ሆስፒታል በማሕጸንና ጽንስ ክፍል ይሠሩ የነበሩ ረዳቶች በቤታቸው በተሰረቀ መሳሪያ የጽንስ ማቋረጥ አገልግሎት ሲሰጡ ተያዙ።

በስተመጨረሻም ስድስት በዕድሜ የገፉ ሴቶች በቁጥጥር ስር ውለው ታስረዋል።

ለተፈጸመ ወንጀል ማስረጃ ከመስጠት በተጨማሪ የአስከሬን ምርመራ በአደጋ ምክንያት የገጠመ ሞትን የማረጋገጫ ማስረጃ ለማግኘት ይረዳል።

ዶ/ር ቫሱ የ98 ዓመት እናቱ ከአልጋ ላይ ወድቀው የሞቱበት ግለሰብ፣ በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ እንዳይያዝ ፈርቶ ለምርመራ የእናቱን አስከሬን ማምጣቱን ታስታውሳለች።

የዶ/ር ቫሱ ምርመራም አዛውንቷ በአደጋ ምክንያት መሞታቸውን አረጋግጧል።

“አዳጊ ሕጻናት እና በዕድሜ የገፉ ሰዎች በመውደቅ ብቻ ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ” የምትለው ዶ/ር ቫሱ “የወደቀችበት አቅጣጫ የህብለ ሰረሰሯን እና አእምሮዋን የሚያገናኘው ስፍራ ቀንጥሶታል” ብላለች።

በሕንድ የአስከሬን ምርመራ ለማካሄድ የሚያገለግሉ መሰረታዊ መሳርያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሕንድ የአስከሬን ምርመራ ለማካሄድ የሚያገለግሉ መሰረታዊ መሳሪያዎች

በዱር አውሬ የተበላ አካል

በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ከኮዚሆዴ 110 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው የእንስሳት ማቆያ ስፍራ ዶ/ር ቫሱ እና ሌላ ዶ/ር አመሩ።

የጉዟቸው ዓላማ የነበረው በነብር ተበልታ የሞተች ሴትን አስከሬን ለመመርመር ነበር።

የሴትየዋ ጭንቅላት እና አንገቷ ብቻ ነበር ተያይዞ ያለው ትላለች ዶ/ር ቫሱ።

በቦታው ላይ ሲደርሱ ሴትየዋ ከአንድ ዛፍ ላይ በለበሰችው ሻርፕ ራሷን ልታንቅ ስትሞክር፣ ሻርቧ ተቀድዶ መውደቋ ይታያል።

የአስከሬን ምርመራው ግን የሴትየዋ ሞት ራሷን ለማጥፋት በተደረገ ሙከራ አለመሆኑን አሳየ።

“ሴትየዋ ራሷን በለበሰችው ቢጫ ሻርፕ በዛፉ ቅርንጫፍ ላይ ለማንጠልጠል ስትሞክር፣ ጨርቁ ተበጥሶ መውደቋን ለማሳየት ነው የተሞከረው” ትላለች ዶ/ር ቫሱ የነበረውን ሁኔታ ስታስታውስ።

“በከፍታ ላይ ስቅላት ሲፈጸም የሚተወው ምልክት የተለየ ነው። ይህ ግን በግልጽ በሦስተኛ አካል በጎን በኩል የተደረገ መታነቅ ነው።”

ከዚያም ወንጀሉን የፈጸመው ግለሰብ ዛፍ ላይ ወጥቶ በዛፉ ቅርንጫፍ ላይ ሻርፗን ቀድዶ አንጠለጠለው።

ፖሊስ ሞቱን በእንስሳት ማቆያ ውስጥ ይሰራ ከነበረ የዝሆን አሠልጣኝ ጋር ያገናኛው ሲሆን፣ በወቅቱም ባለቤቱ እና ረዳቱ ተያይዘው መጥፋታቸውን በማስመልከት ቅሬታ ያቀርብ ነበር ተብሏል።

በኋላም ምርመራው ቀጥሎ ምክትል የዝሆን አሠልጣኙ እና የግድያው ሴራ ይፋ ሆኗል።

ዶ/ር ቫሱ ሽልማት ስትቀበል

የፎቶው ባለመብት, Dr Shirley Vasu

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ቫሱ ሽልማት ስትቀበል

በርካታ ሞቶች

በተፈጥሮ አደጋ አልያም በመኪና ግጭት በርካታ ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜ ቢሞቱ እንኳ የሁሉም ሟች አስከሬን መመርመር ያስፈልጋል።

“ለአስከሬን ምርመራ ሙያ በጅምላ የደረሰ ጥፋት ብሎ ነገር የለም” ትላለች ዶ/ር ቫሱ።

“የአስከሬን ምርመራ ባለሙያ አንድ ግለሰብ ለሞቱ ምክንያት የሆነውን እና የገጠመውን የተለየ ሁኔታ ለይቶ ማወቅ አለበት።”

እኤአ በ2021 ሰኔ ወር ላይ በሰሜናዊ ኬራላ ባቡር ሀዲዱን ስቶ ወንዝ ውስጥ ገባ።

ይህም ለ59 ሰዎች ሞት ሰበብ ሆኖ ተመዘገበ። የመጀመርያ ደረጃ ምርመራው የሚያሳየው የሞታቸው ምክንያት ውሃ ውስጥ መስጠም መሆኑን ነበር።

ዶ/ር ቫሱ እና ባልደረቦቿ በአጠቃላይ ለሟቾቹ የአስከሬን ምርመራ ሲያደርጉ የተረዱት አንድ ሰው ብቻ ውሃ ውስጥ ሰጥሞ መሞቱን ነው።

ቀሪዎቹ ግን የራስ ቅላቸው ላይ በደረሰባቸው ምት፣ ቀሪዎቹ በባቡሩ ስብርባሪ እና በሻንጣ በደረሰባቸው ምት እና ግጭት ነው የሞቱት።

በዚያው ዓመት ከኮዚኮዴ 50 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ማላፑራም የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ በእሳት ተያይዞ 44 ሰዎች ሞቱ።

የሟቾቹ አስከሬን በደረሰባቸው ቃጠሎ ከስሎ የነበረ ሲሆን ዶ/ር ቫሱ የአስከሬኖቹን ማንነት ለመለየት የዘረ መል ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል መሳርያ አልነበራትም።

“የአካላቸውን ሁኔታ ከተገኙት ንብረቶች እንደ ሰዓት፣ የእጅ አንባር፣ ጫማ፣ ልብስ እና ቦርሳ ጋር በማገናኘት እና በመገምገም ነው ለመለየት የሞከርነው” ስትል ታስታውሳለች።

የአስከሬን ምርመራው ለመለየት የሚያስችሉ ሌሎች እንደ ብረት እና ከዚህ ቀደም የተደረጉ የቀዶ ሕክምናዎች ተጨማሪ ነገሮችን እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

“አንድ ረዥም ሰው ሆዱ ባልተፈጨ ሩዝ በሥጋ የተሞላ ነበር” ስትል ታስታውሳለች ዶ/ር ቫሱ።

በኋላም የሟች ጓደኞች ከአደጋው ቀደም ብለው በጋራ ሩዝ በሥጋ እየበሉ እንደነበር በመመስከራቸው ማንነቱን ለመለየት ረድቷል።

ዶክተር በኮምፒውተር ስክሪኑ ላይ የሰው ራስ ቅልን ሲመረምር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በአሁን ወቅት የአስከሬን ምርመራ ማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳርያዎች ይገኛሉ።

የቴክኖሎጂ መሻሻል

ዶ/ር ቫሱ በ34 ዓመት የአስከሬን መመርመር ሥራዋ ለሙያዋ የሚያግዙ መሳሪያዎች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን አይታለች።

በአንድ ወቅት አስከሬን ለመመርመር አደገኛ የሆነውን መርዝ፣ አስከሬን ለማድረቅ የሚያገለግለውን ፎርማልዴሀይድ ትጠቀም የነበረው ዶ/ር ቫሱ አሁን በዘመናዊ መሳሪያዎች መተካቱን ትገልጻለች።

“አሁን ጀርሞችን ለመግደል የዩቪ ጨረሮች እንጠቀማለን” ትላለች።

“በአስከሬን ማቆያ ክፍልም በቂ የሆነ የአየር ዝውውር እና ጥራት መቆጣጠርያ አለ።”

የሟች አካል መበስበስን ለማዘግየትም የአስከሬን ማስቀመጫ ብልሀቱ ተሻሽሏል። ዶ/ር ቫሱ ለወደፊትም እየተሻሻሉ በሚመጡ ቴክኖሎጂዎች ላይ ተስፋ አላት።

“ጃፓን እና ሲንጋፖር ከቢላ እና ደም ነጻ የሆነ ቨርችዋል የአስከሬን ምርመራ ወደ ማድረግ ተሸጋግረዋል። የሟች አካል በሲቲ ስካን ከተነሳ በኋላ ዶክተሮች ከቆዳው እስከ አጥንቱ ድረስ እያንዳንዱን ነገር ይመረምራሉ።”

ይህ ቴክኖሎጂ በአሜሪካ እና አውሮፓ እንዲሁም በኒው ዴሊሂ ከፍተኛ ሆስፒታል ውስጥ ይገኛል።

አድካሚ ሥራ

በአሁኑ ወቅት በአንድ የግል የሕክምና ኮሌጅ ውስጥ የምታስተምረው ዶ/ር ቫሱ፣ የመጨረሻውን የአስከሬን ምርመራ ያካሄደችው እአአ በ2014 ሲሆን ጡረታ የወጣችው ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ በ2016 ነው።

በሥራ ዘመኗ ሁሉ ባከናወነችው እና ባሳካችው መርካቷን የምትናገረው ዶ/ር ቫሱ፣ በአሁኑ የማስተማር ሥራዋም ደስተኛ ነች።

ከአስከሬን ጋር መሥራት አሉታዊ የሆኑ ስሜቶችን ይቀሰቅሳል ትላለች።

“ወደ አስከሬን ማቆያ ስፍራ በጭራሽ መሄድ አልፈልግም። ያለህን አቅም ሁሉ አሟጦ ይወስዳል።”

ዶ/ር ቫሱ የአስከሬን ምርመራ በምታደርግበት ወቅት ምግብ መመገብ የማትወድ ሲሆን፣ አእምሮዋ በአግባቡ እየሠራ እንዲቆይ ቸኮሌት ብቻ ትወስድ እንደነበር ታስታውሳለች።

በደቡብ ሕንድ ከሞት ጋር ተያይዞ በርካታ ማግለል ይደርሳል። በአንዳንድ የሕንድ ማኅበረሰብ መካከል ሴቶች አስከሬን ወደሚቃጠልበት ስፍራ እንዲሄዱ የማይፈቀድ ቢሆንም ከሞት ጋር ተያይዞ በሚከናወኑ አንዳንድ ሥርዓቶች ግን ይሳተፋሉ።

ዶ/ር ቫሱ ከሥራ በምትመለስበት ወቅትም ወደ ቤተሰቦቿ ከመቀላቀሏ በፊት ገላዋን ታጥባ መግባት እንድትችል ከቤቷ ውጪ የገላ መታጠቢያ አሠርታ ነበር።

የትዳር አጋሯ የሕክምና ባለሙያ ቢሆንም እንኳ “ለማውራት ግን በጣም ይፈራ ነበር” ትላለች።

ልጆቿም ቢሆኑ ስለ እናታቸው የሥራ ሁኔታ ለመጠየቅ አይደፍሩም።

ሁለት እህቶቿ በዳኝነት የሠሩ በመሆናቸው የሟቾችን ጉዳይ በተመለከተ በሚሠሩበት ችሎት ተገኝታ የምስክርነት ቃሏን ብትሰጥም “ከምሥክር ሳጥን ውጪ ስለአስከሬን ምርመራ” በጭራሽ ጠይቀዋት አያውቁም።

የአስከሬን ምርመራ ባለሙያ የሆነችው ዶ/ር ቫሱ ከአስከሬን ጋር መሥራት ዕይታዋን በመቅረጽ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

“በአስከሬን ማቆያ ውስጥ መቆየት ትሑት እንድትሆን ያደርጋል” ትላለች።

“ጋጥ ወጥነት አይኖርም። ንጹህ ሕይወት ለመኖር እንድንጥር ያደርጋል።”