የዓለም 'መጥፊያ ሰዓት' ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወደ መጨረሻው እየተቃረበ መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሰው ልጆችን የመጥፊያ የምጽዓት ሰዓትን ለመጠቆም በተምሳሌትነት የተቀመጠው ሰዓት አንድ ሰከንድ የቀነሰ ሲሆን፣ በዚህም የዓለም መጥፊያ ጊዜ ከመቼው በበለጠ ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ነው ተብሏል።
ባለፈው ዓመት ይህ ሰዓት እኩለ ሌሊት ላይ ለመድረስ 90 ሰከንድ (1 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ) ቀርቶት ነበረ። በዓለም ዙሪያ ባሉ ጦርነቶች እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጠረው ስጋት ምክንያት አሁን አንድ ሰከንድ ቀንሶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሳይንቲስቶች አመልክተዋል።
ይህ ተምሳሌታዊ 'የምጽዓት ቀን ሰዓት' መቁጠር ሲጀምር ማብቂያውን እኩለ ሌሊት ያደረገ ሲሆን፣ በሰዓቱ ቀማሪዎች ስሌት መሠረት የዓለም ጥፋት የሚከሰተው የቀሩት ሰከንዶች እየቀነሱ ሄደው በመሟጠጥ ዜሮ ዘሬ ላይ ሲደርስ ነው።
ይህም በፈረንጆች የሰዓት አቆጣጠር እኩለ ሌሊት የሚሆነው ዜሮ ዜሮ ሲሆን በመሆኑ በዓለም ላይ ያሉ ኃያላን አውዳሚ የጦር መሳሪያ ሲጠቀሙ እንዲሁም ተፈጥሮዊ ክስትቶች እየተባባሱ ዕልቂትን ከሚያደርሱበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ የቀሩት 89 ሰከንዶች አንድ በአንድ ወደ ኋላ እየቀነሱ በመሄድ ሰዓቱ ዜሮ ዜሮ ላይ ሲሆን የዓለም ፍጻሜ ይሆናል በሚል ስሌት ነው ሰዓቱ የሚቆጥረው።
ይህ የሰዓት ቀመር በሳይንቲስቶቹ ሲዘጋጅ በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ ያሉ አስጊ ሁኔታዎች ከግንዛቤ የሚገቡ ሲሆን፣ በተለይ አውዳሚው የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ የሚያውሉ አገራት ወደ ጦርነት ሲገቡ የዓለም ጥፋት ስጋት ይጨምራል።
በዚህም ወቅት የሰዓቱ ቀማሪ ሳይንቲስቶች የስጋቱን ዕውን የመሆን መጠን በማስላት ከቀሩት ሰከንዶች ላይ ቅናሽ ያደርጋሉ።
በተቃራው ደግሞ ዓለም ሰላም በምትሆንበት እና የተፈጥሮ አደጋዎች በማያሰጉበት ጊዜ እንደየሁኔታው በሰዓቱ ላይ ሰከንዶችን በመጨመር ዓለምን "ከምጽዓት ቀን" ያርቋታል።
አሁን የተቀነሰው አንድ ሰከንድ ምድር ከዚህ ቀደም ተጨምረው ከነበሩት ላይ የተቀነሰ ሲሆን፣ አሁን የቀሩት ሰከንዶች አንድ ደቂቃ ከ29 ሰከንዶች (89 ሰከንዶች) በመሆኑ ከዚህ በፊት ካልተደረሰበት ሰዓት ላይ መደረሱን ሳይንቲስቶች አመልክተዋል።
በየዓመቱን ሰዓቱን የሚያሻሽለው 'ቡሌቲን ኦፍ ዘ አቶሚክ' ሳይንቲስትስ እንዳለው፣ የኒውክሌር ስጋት፣ በሥነ ሕይወት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚታዩ ማሻሻያዎችን ያላግባቡ መጠቀም እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጆችን ወደ መጥፋት ያቃረቡ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
የተቋሙ ኃላፊ ዳንኤል ሆልዝ እንዳለው ሰዓቱ መለወጡ "ለዓለም መሪዎች ማስጠንቀቂያ" ነው።
ሰዓቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀመጠው በአውሮፓውያኑ 1947 ሲሆን፣ ለእኩለ ሌሊት ሰባት ሰከንዶች እንዲቀሩት ተደርጎ ነበር የተጀመረው። ይህ የምጽዓት ቀን ቆጣሪ ሰዓት አምና 90 ሰከንድ ላይ ነበር የቆመው።
ቺካጎ የሚገኘው መንግሥታዊ ያልሆነው ተቋም እንዳለው ከሆነ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት "በድንገተኛ ውሳኔ ወይም በተሳሳተ ስሌት" ወደ ኒውክሌር ግጭት ሊሚያመራ ይችላል።
እንዲሁም "በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ግጭት ከቁጥጥር ወጥቶ የለየለት ጦርነት ሊሆን ይችላል" ብሏል ተቋሙ።
የተቋሙ ሳይንቲስቶች እንዳሉት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ዓለም መግታት የሚያደርገው ጥረት ደካማ ሲሆን፣ አብዛኞቹ መንግሥታት ፖሊሲ ባለማስተካከል እና ገንዘብ ባለመመደብ ይወቀሳሉ።
ይህም የዓለምን ማኅበረሰብ ደኅንነት እና ምጣኔ ሃብትን የሚጎዳ ነው።
"በወታደራዊ እንቅስቃሴ ላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት መጠቀም በዩክሬን እና መካከለኛው ምሥራቅ ታይቷል። ሌሎች አገራትም በተመሳሳይ ይሄን ለማድረግ እየሞከሩ ነው" ብሏል ተቋሙ።
የሐሰተኛ መረጃ እና የሴራ ትንታኔ ሥርጭት እነዚህን ሁሉ ስጋቶች እንደሚያባብስ ተቋሙ ገልጿል። "የመረጃ ትስስርን የሚበጣጥስ እና እውነትን ከሐሰት ለመለየት የሚያስችግር እንዲሆን አድርገዋል" ሲል ይገልጸዋል።
አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ "በጋራ የሰው ልጆችን ሥልጣኔ የማጥፋት አቅም አላቸው" ብሏል ተቋሙ።
"እነዚህ አገራት ዓለምን ከመጥፋት አፋፍ ማትረፍ አለባቸው" ሲልም እርምጃ ለመውሰድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
ይህ የ'ምጽዓት ቀን' ሰዓት መቁጠር የጀመረው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጃፓን ከተሞች በሆኑት ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በአሜሪካ አውቶሚክ ቦምብ ዕልቂት ከተፈጸመ በኋላ በ1947 (እአአ) ነው።
የዚህ ሃሳብ ጠንሳሾቹ ደግሞ የአውቶሚክ ቦንቡን የገነባው ሮበርት ኦፐንሃይመር እና ባልደረቦቹ ሳይንቲስቶች ሲሆኑ፣ ዓላማውም ተመሳሳይ ጥፋት እና ዕልቂት በዓለም ላይ እንዳይከሰት መሪዎችን እና የዓለምን ሕዝብ ለማስታወስ ነው።












