የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር የሊቢያ የጦር ወንጀል ተጠርጣሪን በመልቀቅ ምርመራ ተከፍቶባቸው እንደነበር ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በጦር ወንጀሎች ሲፈለግ የነበረውን ሊቢያዊ አገራቸው በአስደንጋጭ ሁኔታ መልቀቋን ተከትሎ ምርመራ ተከፍቶባቸው እንደነበር ተናገሩ።
ሜሎኒ ማክሰኞ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ሃብት አቃብያነ ህግ በምዝበራ እና ከወንጀለኛ ጋር በመተባበር ጠርጥረዋቸው ምርመራ ከፍተውባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
አልማስሪም በመባልም የሚታወቀው ኦሳማ ናጂም የሊቢያ የፍትህ ፖሊስ ኃላፊ እና በትሪፖሊ አቅራቢያ በምትገኘው ሚቲጋ የተሰኘው የማጎሪያ ካምፕ ዳይሬክተር ነው።
ናጂም ከዘጠኝ ቀናት በፊት በጣሊያን ቢያዝም ከቀናት በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ "በቴክኒካል ምክንያት" ነጻ መውጣቱን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ስለ ጉዳዩ አልተማከርኩም ያለው አለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ለናጂም ሌላ የእስር ዕዝ ከማውጣት ባለፈ የጣሊያን ባለስልጣናት ማብራሪያ እንዲሰጡት ጠይቋል።
ሜሎኒ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት የሮም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ናጂምን የፈታው የፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ ለጣሊያን ፍትህ ሚኒስቴር ስላልተላከ ነው ብለዋል።
"በወቅቱ በጣሊያን ግዛት ውስጥ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስ በሚል እሱን ለማባረር እና በልዩ በረራ በአስቸኳይ ወደ አገሩ እንዲመለስ ወስነናል" ሲሉ ሜሎኒ ተናግረዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ካርሎ ኖርዲዮ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት ከሆነ ናጂም የተባረረው በደቀነው "አደጋ" ምክንያት ነው ማለታቸው በተቃዋሚዎች መሳለቂያ አድርጓቸው ነበር።
ናጂምን ለመልቀቅ የተደረሰው ውሳኔ በተቃዋሚዎች እና እንደአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ ነቀፌታ ቀርቦበት ነበር። ናጂም "አሰቃቂ ጥሰተኞችን" የፈጸመ ግለሰብ እንደሆነም አምነስቲ አስታውሷል።።
ናጂም ትሪፖሊ ውስጥ ከጣሊያን መንግስት አውሮፕላን ሲወርድ የተሰበሰቡ ሰዎች በደስታ ሲቀበሉት የሚያሳዩ ቪዲዮዎች መለቀቃቸው ደግሞ ትችትን ፈጥሯል።

የፎቶው ባለመብት, @MarcoFattorini /X
አቃቤ ህግ ካርሎ ኖርዲዮ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማትዮ ፒያንቴዶሲ እና የስለላ ጉዳዮች የበላይ ኃላፊ የሆኑት አልፍሬዶ ማንቶቫኖ ምርመራ እንደከፈቱባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። በጣሊያን ምርመራ ተጀመረ ማለት መደበኛ ክሶች የግድ ይከተላሉ ማለት አይደለም።
የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ለምርመራው ፖለቲካዊ ምክንያቶች መኖራቸውን ፍንጭ የሰጡ ይመስላል።
ቅሬታውን ያቀረቡት ጠበቃ ሉዊጂ ሊ ጎቲ የቀድሞ የግራ ክንፍ ፖለቲከኛ እንደነበር ጠቁመው ጉዳዩን የሚመሩት ዓቃቤ ህጉ ፍራንቸስኮ ሎ ቮይ ደግኖ በቅርቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማትዮ ሳልቪኒ ላይ በሌላ ጉዳይ መርምራ አካሂደዋል።
ሜሎኒ ቪዲዮውን ያጠናቀቁት "በጉዳዩ ሽብርክ እንደማይሉ" በመግለጽ ነው።
"ጣሊያን እንድትለወጥ እና እንድትሻሻል በማይፈልጉት መካከል ያልተወደድኩት ለዚህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መንገዴን ለመቀጠል ያሰብኩበት ምክንያት ጣሊያኖችን በመጠበቅ ስለሆነ ያለ ምንም ፍርሃት ጭንቅላቴን ቀና አደርጋለሁ" ብለዋል።
የናጂምን መፈታት ካወገዙት መካከል የመጀመሪያው የሆኑት የተቃዋሚው ኢታሊያ አላይቭ (IV) ፓርቲ ባልደረባ ማቲው ሬንዚ በበኩላቸው ሜሎኒ ምርመራውን "የተለመደውን እየተጠቃሁ ነው" የሚለውን ስሜት ለመፍጠር እየተጠቀመችበት ነው ሲሉ ተችተዋል።
ቀኝ ዘመም እና ፀረ ስደተኛ የሆነው የጣሊያን ወንድማማቾች ፓርቲ መሪ የሆኑት ጆርጂያ ሜሎኒ እአአ ከ2022 ጀምሮ ጣሊያንን የመራውን የቀኝ ክንፍ ጥምረት መርተዋል።
ስደተኞችን ለመቆጣጠር፤ ከሰሜን አፍሪካ ወደ ኢጣሊያ የሚሄዱትን ጀልባዎች ለማስቆም፤ ህገ ወጥ ጉዞዎችን እና የሰዎች ዝውውርን እንደሚያስቆሙ ደጋግመው ቃል ገብተዋል።
ሜሎኒ ከእርሳቸው በፊት እንደነበሩት መሪዎች ከሊቢያ ባለስልጣናት እና ሚሊሻዎች ጋር በመተባበር ህገ-ወጥ ስደትን ለመቅረፍ በተደረጉ አወዛጋቢ ስምምነቶች ተሳትፈዋል።
በዚህም የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት የስደተኛ ጀልባዎችን ለሚከላከለው የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ስልጠና እና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።












