ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመንግሥት ሰራተኞች ከስራቸው እንዲለቁ የስምንት ወር ደመወዝ አቀረቡ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስራቸው ለመልቀቅ ለሚስማሙ ሁሉም የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የስምንት ወር ደመወዛቸውን እሰጣለሁ አሉ።

ትራምፕ የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶችን መጠን ለመቀነስ በያዙት ዕቅድ ነው ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት።

አስተዳደራቸው በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ለፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች በላከው ኢሜይል ስራቸውን በገዛ ፈቃድ መልቀቅ ለሚፈልጉ እና በዚህ ፕሮግራም መካተት ለሚፈልጉ እስከ ጥር 29/ 2017 ዓ.ም ቀነ ጊዜ እንደተሰጣቸው አትቷል።

በተቀመጠው ቀነ ገደብ ወቅት ስራቸውን ለመልቀቅ ከተስማሙ የስምንት ወር ደመወዛቸውን እንደ የስንብት ፓኬጅ እንደሚያገኙ ከተላከው ኢሜይል መረዳት ይቻላል።

የትራምፕ አስተዳደር እስከ 10 በመቶ የሚደርሱት ወይም 200 ሺህ የሚሆኑት ሰራተኞች ይህንን ፓኬጅ እንደሚቀበሉ እንደሚጠብቅ የቢቢሲ አሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

በአሜሪካ የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ሰራተኞች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ ይሆናል።

የትራምፕ ከፍተኛ ባለስልጣን ይህ እርምጃ መንግሥትን እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ያህል ለማዳን እንደሚያስችለው ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ማክሰኞ ዕለት በተጻፈው ኢሜይል ላይ በዚህ የሚስማሙ ሰራተኞች "መልቀቅ" በሚል ርዕስ ኢሜይላቸውን አርቅቀው እንዲመልሱ ተጠይቀዋል። የሚለቁ ሰራተኞች እስከ መጪው መስከረም ድረስ የሚሆን ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያገኙ ይሆናል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሆኖም የፖስታ ቤት ሰራተኞች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት እንዲሁም የተወሰኑ የብሔራዊ ደህንነት ሰራተኞች በዚህ ፓኬጅ እንዳልተካተቱ ኢሜይሉ አትቷል።

በስራቸው ላይ ለመቆየት የወሰኑ ሰዎች ለወደፊቱ ሊቀነሱ እንደሚችሉ የሰራተኞች አስተዳደር ጽህፈት ቤት የወጣው ይህ ኢሜይል አስጠንቅቋል።

"ከስራችሁ አትቀነሱም የሚለውን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ ማረጋገጫ ልንሰጣችሁ አንችልም ነገር ግን የምትቀነሱ ከሆነ በክብር ይሆናል" ይላል።

ትራምፕ የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ በርቀት ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች በሳምንት አምስት ቀን በቢሯቸው እንዲገኙ ቀደም ብለው መልዕክት ልከዋል።

የዋይት ሃውስ የፖሊሲ ምክትል ኃላፊ ስቴፈን ሚለር ትራምፕ የፌደራሉ መንግሥት ሁለት ሚሊዮን ሰራተኞችን ትኩረት ውስጥ በማስገባት "መንግሥታቸውን መቆጣጠራቸው አስፈላጊ ሆነው አግኝተውታል" ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን መጠን እንዲሁም የፌደራል ወጪዎችን ለመቀነስ ደጋግመው ቃል ሲገቡ ነበር።

በፌደራል መንግሥቱ በጀቶችን፣ ወጪዎችን መቀነስ እንዲሁም የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ቁጥር በመቀነስ ላይ ያተኮረ አማካሪ አካል እንዲመሩ ኤለን መስክ እና ቪቬክ ራማስዋሚን ትራምፕ መሾማቸው ይታወሳል። ሆኖም ራማስማዋዚ ይህ "የመንግሥት ቅልጥፍና ክፍል" የተሰኘውን መስሪያ ቤት መልቀቁን ማስታወቁ ይታወሳል። ማክሰኞ ለመንግሥት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የተላከው ኢሜይል በአውሮፓውያኑ 2022 መገባደጃ ላይ መስክ ትዊተርን (የአሁኑን ኤክስ) ከገዛ በኋላ ከላከው ኢሜይል ጋር ተመሳሳይነት አለው። መስክ ሰራተኞች በኩባንያው ውስጥ ለመቆየት ከፈለጉ በኢሜይል ምላሻቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቋል።