ሐማስ እስከ መጪው ቅዳሜ ታጋቾችን ካልለቀቀ ጦርነት እንደምትጀምር እስራኤል አስጠነቀቀች

 የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሐማስ እስከ መጪው ቅዳሜ፣ የካቲት 8/ 2017 ዓ.ም እኩለ ቀን ድረስ ታጋቾችን ካልለቀቀ የጋዛ ተኩስ አቁም ተሽሮ ጦርነት እንደሚጀምሩ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስጠነቀቁ።

ሐማስ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊነት ቁርጠኝነቱን አስታውቆ እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባ ሰብዓዊ እርዳታን ማገድን ጨምሮ መሰረታዊ ቁልፍ የሚባሉ ስምምነቶችን ጥሳለች ብሏል።

እስራኤል በበኩሏ ይህንን አስተባብላለች።

የታጋቾች መለቀቅ ጊዜው መራዘሙን ተከትሎ ቤንያሚን ኔታንያሁ በጦርነት በወደመችው ጋዛ ውስጥ እና በአካባቢው ጦራቸው እንዲሰማራ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት በመጪው ቅዳሜ ሶስት ታጋቾች ይለቀቃሉ የተባለ ቢሆንም ኔታንያሁ እየጠየቁ ያሉት ሶስቱን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ቀሪዎቹን 76ቱን መሆኑን አንድ ሚኒስትር ተናግረዋል።

ሐማስ ለሶስት ሳምንታት የሚፈጀውን የመጀመሪያውን የተኩስ አቁም ስምምነት ምዕራፍ "በማወሳሰብ፣ ወይም በማዘግየት እስራኤል ተጠያቂ ናት" የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ሐማስ የሶስቱ ታጋቾችን የመልቀቅ ጊዜ ለማዘግየት መወሰኑን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እንድትሰርዝ ብለዋል። በተጨማሪም "ሁሉም ታጋቾች" እስከ መጪው ቅዳሜ እስካልተመለሱ ድረስ ጦርነቱ እንዲፋፋም መመሪያ ሰጥተዋል።

ማክሰኞ ለአራት ሰዓታት የፈጀውን የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ ስብሰባ ተከትሎ ኔታንያሁ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት የአሜሪካው አቻቸው ያስተላለፉትን ትዕዛዝ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል።

"ሐማስም ስምምነቱን በመጣስ እና ታጋቾችን ላለመልቀቅ መወሱን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እና በአካባቢው እንዲሰማራ ትላንት ምሽት መመሪያ ሰጥቻለሁ" ሲሉ ኔታንያሁ አክለዋል።

"ይህ እርምጃ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ሲሆን በቅርቡም ይጠናቀቃል" ብለዋል።

ታጋቾች እስካልተለቀቁ ድረስ ጦርነት እንደሚጀምር በማስጠንቀቅ የጸጥታ ካቢኔያቸውን ሙሉ ይሁንታ አግኝቻለሁ ብለዋል።

"ሐማስ ታጋቾቻችንን እስከ ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ካልመለሰ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተሽሮ ቡድኑ እስኪሸነፍ ድረስ ጠንካራ ውጊያ ይቀጥላል" ሲሉ ተናግረዋል።

እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሶስተኛው የጋዛ ህንጻዎች መውደማቸውን የተባበበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

እስካሁን ድረስ ሐማስ 16 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል ደግሞ በእስር ቤቷ የነበሩ 566 ፍልስጤማውያንን ለቃለች።

ለሶስት ሳምንታት በሚቆየው የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም 33 እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲሁም 1 ሺህ 900 ፍልስጤማውያን ይለቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል ከ33ቱ ውስጥ ስምንቱ መሞታቸውን አስታውቃለች።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48,189 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።