እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች ያለው ሐማስ ታጋቾችን እንደማይለቅ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች ሲል የወቀሰው ሐማስ ለጊዜው ታጋቾችን እንደማይለቅ አስታወቀ።
የሐማስ ታጣቂ ክንፍ ቃል አቀባይ ቡድኑ በቅርቡ ሊለቃቸው ያሰባቸውን ታጋቾችን ለጊዜው እንደማይለቅ ተናግረዋል።
በጋዛ የሚገኙ ሶስት ታጋቾች በሚቀጥለው ቅዳሜ ይለቀቃሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። እስራኤል ደግሞ ፍልስጤማዊያን እስረኞችን እንደምትለቅ ይጠበቃል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የሐማስን ድርጊት "የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ የሚያፈርስ ነው" ብለውታል።
የእስራኤል የቅርብ አጋር የሆኑት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሁሉም ታጋቾች በሚቀጥለው ቅዳሜ የማይለቀቁ ከሆነ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊሰረዝ ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
"ሁሉም ታጋቾች ቅዳሜ ቀትር መለቀቅ አለባቸው። ሁሉም። አንድ ወይም ሁለት አሊያም ሶስት አራት ሳይሆን፤ ሁሉም" ብለዋል።
"ይህ የኔ አስተያየት ነው" ያሉት ትራምፕ "እስራኤል የፈቀደችውን ማድረግ ትችላለች" የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 ባደረሰው ጥቃት የታገቱ 73 ሰዎች እና ከአስር ዓመት በፊት የተወሰዱ ሶስት ታጋቾች አሁንም በጋዛ ይገኛሉ።
ታጋቾቹ የማይለቀቁ ከሆነ "ገሀነም ይወርዳል" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
ታጋቾች የማይለቀቁ ከሆነ ከእስራኤል ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ማለትዎ ነው ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ፤ "እናያለን። ሐማስ ምን ማለት ፈልጌ እንደሆነ ያየዋል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ የእስራኤል ጦር ሠራዊት "በጋዛ ለሚከሰት የትኛውም ዓይነት ክስተት እና ማኅበረሰቡን ለመጠበቅ በተጠንቀቅ እንዲዘጋጅ" ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
"የጥቅምት 7 ድርጊት እንዲደገም በፍፁም አንፈቅድም" ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ፋርሀን ሀቅ የተኩስ አቁም ስምምነቱ "የትኛውም መጓተት" ካጋጠመው አደጋ ሊያመጣ ይችላል ብለው ሁለቱ ወገኖች ስምምነቱን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሐማስ፤ እስራኤል ግዴታዋን "የምትወጣ" ከሆነ ታጋቾቹ ቅዳሜ የሚለቀቁበት "መንገድ ይፈጠራል" ማለቱን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል አስነብቧል።
የሐማስ ቃል አቀባይ አቡ ኦቤይዳ እስራኤል የተፈናቀሉ ፍልስጤማዊያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዳይመለሱ እየከለከለች ነው፤ ሰዎች ላይ እየተኮሰች ነው፤ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባም አልፈቀደችም ሲሉ ወቅሰዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ጋዛን በባለቤትነት ማስተዳደር እንደምትፈልግ መናገራቸው ይታወሳል።
ሐማስ ስለትራምፕ አስተያየት የሰጠው ምላሽ የለም።












