ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው "ወደ ሀገሬ እንዳልገባ ተከልክያለሁ" አሉ

በአሜሪካ የነበሩት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው "ወደ ሀገሬ እንዳልገባ ተከልክያለሁ" ሲሉ ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ነገር ግን ይህ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል እንደጣለባቸው የተገለጸላቸው የጉዞ ዕገዳ ቢኖርም፣ በሌላ ሀገር አየር መንገድ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ገልጸዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ለየካቲት 3/2017 ዓ.ም. የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጠው በአትላንታ አየር ማረፊያ ቢገኙም መሳፈር እንዳልቻሉ አስታውቀዋል።
ለሕክምና በአሜሪካ ከሁለት ዓመታት በላይ የቆዩት አቶ ልደቱ ከአንድ ወር በፊት ገደማ ነው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ እና ቲኬት እንደቆረጡ ያስታወቁት።
የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ሀገራት ሆነው "ግጭት በመፍጠር የክልል እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመጣል" ተንቀሳቅሰዋል በሚል ተላልፈው እንዲሰጡት ጥያቄ ከቀረበባቸው ግለሰቦች መካከል አቶ ልደቱ አያሌው አንዱ መሆናቸው ይታወሳል።
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ አቶ ልደቱን ጨምሮ "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እና በሽብር ወንጀል ቡድን ውስጥ በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ ነበር" የተባሉ ግለሰቦችን ሀብት የመቆጣጠር እርምጃ እንደሚወሰድም አሳውቆ ነበር።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት ተጠቃሽ ከሆኑት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ልደቱ ወደ አሜሪካ ተጉዘው የቆዩት ለህክምና ክትትል ነበር። በመንግሥት በኩልም እንደሚፈለጉ የተገለጸው ከሀገር ውጪ በነበሩበት ጊዜ ነው።
ከጽንፈኛ እና ከሽብር ኃይሎች ጋር በመሥራት በሀገሪቱ ውስጥ ቀውስ እንዲፈጠር ተደራጅተው እየሠሩ ናቸው ከተባሉት በርካታ ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ልደቱ፤ በመግለጫ ስማቸው ተጠቅሶ በቀረበባቸው ውንጀላ ላይ ክስ የሚመሠረት ከሆነ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለሱ ለቢቢሲ በወቅቱ መናገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች ያሉት አቶ ልደቱ አስፈላጊ የሆነውን ሕክምና ማድረጋቸውን በመግለጽ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በሀገር ቤት ሆነው የሰላማዊ ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ እና የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል መወሰናቸውን ከአንድ ወር በፊት ባሠራጩት ዝርዝር ጽሁፍ ገልጸው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የጉዞ ቲኬታቸውን ከኢትዮጵያ መንገድ ቆርጠው በአሜሪካ የነበራቸውን ቆይታ በማጠናቀቅ ሰኞ የካቲት 3/2017 ዓ.ም. ማለዳ ወደ አትላንታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቢያቀኑም ወደ ሀገራቸው ለመጓዝ ሳይችሉ መቅረታቸውን ተናግረዋል።
"ቲኬቱ የተረጋገጠ ነው። ፖስፖርቴም ለሚቀጥሉት 11 ወራት የሚያገለግል ነው" ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ ልደቱ፤ ነገር ግን አየር ማረፊያ ሲደርሱ "በአሜሪካ የኢትዮጵያን ኤምባሲን" አነጋግረው ልዩ ፈቃድ ካላገኙ መጓዝ እንደማይችሉ እንደተናገራቸው ገልፀዋል።
"አየር ማረፊያው ደርሼ 'ቦርዲንግ ፓስ' ሊሠሩልኝ ሲሞክሩ ሲስተሙ እምቢ አላቸው። እገዳ እንደተጣለበኝ ሲነግሩኝ ሥራ አስኪያጁን [የአየር መንገድ] አግኝቼ አነጋግርኩ" በማለት አስረድተዋል።
አክለው ከሥራ አስኪያጁ የተሰጣቸው ምላሽ "እገዳ ስተለጣለብህ እኛ ምንም ማድረግ አንችልም" የሚል እንደሆነ ጠቁመው "አሜሪካ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አመልክተህ በእነሱ በኩል እገዳው ካልተነሳልህ መብረር አትችልም" መባላቸውን ለቢቢሲ አስታውቀዋል።
የፓስፖርታቸው የአገልግሎት ጊዜ አለማብቃቱን፣ አስፈላጊውን የጉዞ ቲኬት በጊዜ ቆርጠው መያዛቸውን እና የሀገሪቱ ዜጋ በመሆናቸው ቪዛ እንደማያስፈልጋቸው የሚናገሩት አቶ ልደቱ፣ የተጣለባቸው የጉዞ እገዳ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
"ከኤምባሲ ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለም። ስልክ ደውዬ «ለተለያዩ አገልግሎቶች ድረ-ገፃችንን ይጎብኙ» የሚል ምላሽ እንጂ የሚያነሳልኝ አላገኘሁም። የአምባሳደር ፀሐፊ ስልክ ላይ ደውዬም እንዲሁ አልተነሳም" ብለዋል።
ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ ለጉዳዩ እልባት ለማግኘት የኤምባሲውን ድረ-ገፅ ጎብኝተው የእሳቸውን ጉዳይ በሚመለከት መፍትሔ የሚሰጥ አማራጭ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።
"የእኔ ጉዳይ የቪዛ ጥያቄ አይደለም፤ የፓስፖርት ዕድሳት ጉዳይ አይደለም። የእኔ ጉዳይ በረራ መከልከል ነው። ለነገሩ ኤምባሲው የሚመለከተው ነገር አይደለም።"
ቢቢሲ ዋሽንግተን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመደወል በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስልኩ ስለማይነሳ አልተሳካም።
በፀጥታ ኃይሉ ከባድ የሚባል ክስ የቀረበባቸው አቶ ልደቱ በሕክምና ምክንያት ለጥቂት ዓመታት በአሜሪካ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ሀገር ቤት በመመለስ የሚገጥማቸውን ለመቀበል ከቻሉም በፖለቲካው ውስጥ ለመሳተፍ ያለሙበት ጉዞ ተደናቅፏል።
ነገር ግን አቶ ልደቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ወደ ሀገር ቤት ለመግባት ያደረጉት ሙከራ ባይሳካም በቀጣይ በሌላ አየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በሌላ አየር መንገድ ቲኬት ለመቁረጥ እየተዘጋጀሁ ነው። አዲስ አበባ ስደርስ ደግሞ የሚሆነው አያለሁ። ወደ ሀገር እንዳልገባ ለመከልከል የሚያስችል ምንም ዓይነት ሕግ የለም" ብለዋል።
አቶ ልደቱ "በሽብርተኝነት የምፈለግ ሰው አይደለሁ እንዴ?" ሲሉ ወደ ሀገር ቤት መግባት ለምን እንደተከለከሉ ይጠይቃሉ።
"መንግሥት በኢንተርፖል እናስፈልጋቸዋለን፤ እናስመጣቸዋለን እያለ ሲፎክር ነበር። በገዛ ፈቃዴ ወደ ኢትዮጵያ እሄዳለሁ ስል መቀበል ነው የነበረበት እንጂ ልከለከል አይገባም" ያሉት አቶ ልደቱ "ከመሄድ የሚመልሰኝ ነገር የለም" ሲሉ አቋማቸውን ገልፀዋል።
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ በተለይ በአማራ ክልል ውስጥ ካለው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ እና እየተፈለጉ ያሉ ሰዎችን ዝርዝር በፎቶግራፍ አስደግፎ አሠራጭቶ ነበር።
በዚህ መግለጫ ላይ አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ ከ10 በላይ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ ተፈላጊዎች መሆናቸውን እና እነሱንም በመያዝ ለሕግ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተገልጾ ነበር።
ግብረ ኃይሉ እንዳለው "እነዚህ የሽብር ኃይሎች" ከሚኖሩባቸው ሀገራት በዓለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) እንዲሁም ከመንግሥታት የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ጋር በመተባበር "ተላልፈው እንዲሰጡ እየሠራ" መሆኑን አመልክቶ ነበር።
አቶ ልደቱ አያሌው በ1997 ዓ.ም. ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ በመሆኑ ግዙፍ እንቅስቃሴን ፈጥሮ የነበረው የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ጥምረት መሥራች ፓርቲዎች ከሆኑት መካከል አንዱ የነበረው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር ሆነው ለረጅም ጊዜ መርተውታል።
አቶ ልደቱ አወዛጋቢውን ምርጫ ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ለአንድ የሥልጣን ዘመን የቆዩ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ጎልተው የሚታዩ ወጣት ፖለቲከኛ ሆነው ቆይተዋል።
ከአራት ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጸመውን የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ግጭት እና ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ለእስር ከተዳረጉ ፖለቲከኞች መካከል አቶ ልደቱ አንዱ ነበሩ። የቀረበባቸው ክስም በምሥራቃዊቷ ቢሾፍቱ ከተማ አመጽን በማበረታታት እና ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝ ነበር።
ለወራት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ልደቱ የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ለሕክምና ወደ አሜሪካ ቆይተው ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ ነው እገዳ እደተጣለባቸው እንደተነገራቸው የገለጹት።












