ቢቢሲ በጦርነት ቀጣና ለሚገኙ ሕፃናት ትምህርት መስጠት ጀመረ

የ10 ዓመቱ የጋዛ ነዋሪ ታሬቅ
የምስሉ መግለጫ, ታሬቅ ትምህርት ቤቱ ፈርሲ ሲመለከት ማዘኑን ይናገራል

የ10 ዓመቱ ታሬቅ የጋዛ ነዋሪ ነው። የ14 ዓመቷ ሳፋ ደግሞ ሱዳን ነው የምትኖረው።

2 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖሩት ሕፃናት ተገናኝተው አያውቁም። ነገር ግን የሚያመሳስላቸው አንድ መራር እውነታ አለ። ሁለቱም ከትምህርት ገበታ ርቀዋል።

"ትምህርት ቤቴ ፈራርሶ ስመለከት በጣም አዘንኩ። ወደ ድሮው መልኩ ቢመለስ ምኞቴ ነው" ሲል የጋዛው ታሬቅ ለቢቢሲ ይናገራል።

"በዚህ ሁሉ መሐል ትምህርት መቅሰሜን አላቋረጥኩም። ቤት ውስጥ እማራለሁ። ወደ ትምህርት ስመለስ ዝግጁ ሆኜ መጠበቅ እፈልጋለሁ" ይላል።

ሳፋ የወደፊት ሕልሟ የልብ ቀዶ ጥገና ባለሙያ መሆን ነው። "አሁንም ተስፋ አልቆርጥም" ትላለች። ነገር ግን የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ትልቅ ጠባሳ ጥሎባታል።

"በየመንገዱ ሬሳዎች ወድቀው አይቻለሁ። በዚህ ምክንያት ነው ሰዎች የሚሞቱበት ሳይሆን የሚድኑበት ምክንያት መሆን የምፈልገው።"

የ14 ዓመቷ ሱዳናዊት ሳፋ እና ሌሎች ሕፃናት በመጠለያ
የምስሉ መግለጫ, የ14 ዓመቷ ሱዳናዊት ሳፋ የወደፊት ሕልሟ የልብ ሐኪም መሆን ነው

ታሬቅ እና ሳፋ በጦርነት ምክንያት ከትምህርታቸው ከራቁ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ሕፃናት መካከል ናቸው። ዩኒሴፍ የተሰኘው የተባበሩት መንግሥታት ክፍል እንደሚለው በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪማ 30 ሚሊዮን ሕፃናት በጦርነት ምክንያት ትምህርት አቋርጠዋል።

ድርጅቱ እንደሚያስቀምጠው ግምት ከዚህ መካከል ግማሹ አሊያም 16.5 ሚሊዮኑ ሱዳን ነው የሚገኙት።

ቢቢሲ ዎርልድ ሰርቪስ በጦርነት ምክንያት ትምህርት ላቋረጡ ሕፃናት ዳርስ ወይም መማር የተሰኘውን ፕሮግራም በአረብኛ ቋንቋ ማቅረብ ጀምሯል።

ባለፈው ዓመት ብቻ በጋዛ "ከ600 ሺህ በላይ ሕፃናት ትምህርት አቋርጠዋል" ይላሉ የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ሳሊም ኦዌይስ።

"ግጭት፣ የሰላም እጦት እና ቀውስ ሕፃናት ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ እያደረሰባቸው ያለውን ተፅዕኖ እየተመለከትነው እንገኛለን" ሲሉ ያክላሉ።

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ሁለት ዓመት ቢያልፈውም አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት በስደተኞች መጠለያ ውስጥ ነው የሚገኙት። በመጠለያዎቹ ትምህርት ማግኘት ቀላል አይደለም።

ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የሱዳን የትምህርት ሚኒስትር አሕመድ ኻሊፋ የዚህን ቀውስ ደረጃ ያስረዳሉ።

"አንድም ግዛት ከቀውሱ አላመለጠም" የሚሉት ሚኒስትሩ "ሱዳን 15 ሺህ ያክል የመንግሥት ትምህርት ቤቶች አላት። ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ጉዳት ደርሶባቸዋል" ሲሉ ያብራራሉ።

"በንፅፅር ሰላም በሚባሉ አካባቢዎች እንኳ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህ የሆነው ታጣቂዎች ሆነ ብለው ባደረሱት ጥቃት ነው።"

ዳርስ የተሰኘው ፕሮግራም በቴሌቪዥን
የምስሉ መግለጫ, ዳርስ የተሰኘው ፕሮግራም በቴሌቪዥን፣ በዩቲዩብ እና በራድዮ ይተላለፋል

ዳርስ የተባለው ተሸላሚ ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገው በአውሮፓውያኑ 2023 ነው። አጀማመሩን በአፍጋኒስታን ለሚገኙ ሕፃናት ትምህርት ለመስጠት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ይህን ፕሮግራም ለሕፃናት ትምህርት "ሕይወት አድን" ነው ይለዋል።

ፕሮግራሙ ዕድሜያቸው ከ11-16 ላሉ ሕፃናት የተቀረፀ ነው። በአረብኛ የሚሰጠው ፕሮግራም በየሳምነቱ ሒሳብ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአእምሮ ጤናን የተመለከተ ትምህርቶች ይሰጣል።

እንደ ታሬቅ እና ሳፋ ያሉ በጦርነት ውስጥ ሆነው ትምህርታቸውን ያላቋረጡ ተማሪዎች ታሪክን ይቀርብበታል።

የመጀመሪያው ፕሮግራም በቢቢሲ አረብኛ ቴሌቪዥን እሑድ ዕለት ተላልፏል። በየሳምንቱ እሑድ አዳዲስ ፕሮግራሞች ይቀርባሉ። በሳምንቱ ቀናት ደግሞ በድጋሚ ይታያሉ።

ከቴሌቪዥን በተጨማሪ በቢቢሲ ኒውስ አራቢክ የዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በጋዛ እና በሶሪያ በራድዮ ይሰራጫል።