የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከሠራተኞች ደመወዝ የፓርቲ አባልነት መዋጮ እንዳይቆርጡ የሚከለክል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ

የየብልፅግ ፓርቲ ቅስቀሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት መዋጮን ከሠራተኞቻቸው ደመወዝ ላይ "በቀጥታ" እየቆረጡ ለፓርቲዎች እንዳያስገቡ የሚከለክል ረቂቅ ሕግ አዘጋጀ። ረቂቁ ሕጉ፤ በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ጊዜ ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ በማይቻልበት ጊዜ ምርጫው "በተለያየ ጊዜ" ሊካሄድ እንደሚችልም ይደነግጋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ እነዚህን ጉዳዮች ያስተዋወቀው ለውይይት ባቀረበው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ነው።

ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት ያለው ይህ ረቂቅ፤ ላለፉት አምስት ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የተመለከተ አዋጅን የሚተካ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ የተሻሻለው በሥራ ላይ ያለው ሕግ የጸደቀው ጥቅምት 2012 ዓ.ም. ነበር። በዘጠኝ ክፍሎች እና በ177 አንቀጾች ተዋቀረው አዲሱ ማሻሻያ ምርጫን እንዲሁም የፓርቲዎችን ምዝገባ እና እንቅስቃሴ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለውጦችን አድርጓል።

የምርጫ መራዘም

አዲሱ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ካካተታቸው አዲስ ጉዳዮች መካከል አንዱ፤ በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ጊዜ ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ በማይቻልበት ጊዜ ተግባራዊ የሚደረግ የምርጫ መራዘምን የሚመለከተው ይገኝበታል።

የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች አባላትን ለመምረጥ የሚደረገው ጠቅላላ ምርጫ፤ በየአምስት ዓመቱ "በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ" እንደሚካሄድ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ጠቅላላ ምርጫን በሁሉም ቦታ በተመሳሳይ ጊዜ የማድረግ ነገር ሊሳካ የማይችልባቸው ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ረቂቁ ይጠቁማል።

ረቂቅ ሕጉ፤ "በተመሳሳይ ጊዜ ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን የማያስችሉ" በሚል የዘረዘራቸው ጉዳዮች "የፀጥታ ችግር፣ ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ አደጋን የመሰሉ ሁኔታዎችን" ነው። እነዚህን ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ምርጫ ቦርድ ስለ ጉዳዩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር "በመመካከር ምርጫውን በተለያየ ጊዜ እንዲካሄድ" ሊያደርግ እንደሚችል ሰፍሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ከዚህ ቀደም በማሻሻያ ረቂቁ ላይ በጠቀሳቸው የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ጠቅላላ ምርጫን በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ጊዜ አድርጓል። በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይህ ጉዳይ ጎልቶ ታይቷል።

ድምፅ ለመስጠት የተሰለፉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, National Election Board of Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዲስ መንግስት መመስረት ያስቻለ ምርጫ የተካሄደው ሰኔ 16/2016 ዓ.ም. ነበር

በመተከል እና ካማሺ ዞኖች በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ አዲስ መንግሥት መመሥረት በሚያስችል ደረጃ ምርጫ የተካሄደው፤ ከሌሎቹ የሀገሪቱ ክልሎች ከሦስት ዓመታት በኋላ ነው። ሰኔ 2013 ዓ.ም. በተካሄደው በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተመረጡት ፌደራል እና የክልል ምክር ቤቶች በይፋ የተመሠረቱት መስከረም 2014 ዓ.ም. ነበር።

በወቅቱ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በአብላጫዎቹ የምክር ቤት ወንበሮች ተወካዮችን ማስመረጥ ያልቻለው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንጻሩ፤ ሰኔ 2016 ዓ.ም. ምርጫ አድርጎ ሐምሌ ላይ ምክር ቤቱን መሥርቷል።

ምርጫ ቦርድ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ጨምሮ እንደ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ እና አፋር ባሉ ክልሎች በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫን እያራዘመ በተለያዩ ጊዜያት ሂደታቸውን ቢያከናውንም፤ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ምርጫ ማራዘምን የሚመለከት ክፍል የለውም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ማሻሻያ ያደረገው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ፤ ዕጩዎች እና መራጮች ከተመዘገቡ በኋላ ስለሚራዘም ምርጫም አዲስ አሠራር አስፍሯል። በረቂቁ መሠረት፤ ምዝገባ ከተደረገ በኋላ የተራዘመ ምርጫ በስድስት ወራት ውስጥ ካልተካሄደ፤ "የዕጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ በአዲስ መልክ" ይካሄዳል።

በተራዘመ ምርጫ የተመረጡ አሸናፊዎች የተወካይነት ቆይታም በሚቀላቀሉት ምክር ቤት ቀሪ ሥራ ዘመን እንደሚወሰን ረቂቁ አስፍሯል። "አንድ ምክር ቤት የሥራ ዘመኑ ሊጠናቀቅ የቀረው ጊዜ አንድ ዓመት እና ከዚያ በታች ከሆነ የተራዘመው ምርጫ አይካሄድም" ሲል ምርጫ ቢራዘምም ሊካሄድ የማይችልበትን ሁኔታም አስቀምጧል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የአባልነት መዋጮ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለውይይት ባቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ ካካተታቸው አዳዲስ ጉዳዮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎችን የገቢ ምንጭ የሚመለከተው ማሻሻያ ይገኝበታል። በሥራ ላይ ያለውም ሆነ ማሻሻያው በቀዳሚነት የሚጠቅሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጭ ከአባላት የሚሰበሰብ መዋጮ መሆኑን ነው።

ይህ ዓይነቱ መዋጮ አባላት በፈቃዳቸው ለፖለቲካ ፓርቲው የሚያዋጡት ነው። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የገዢው ፓርቲ አባል የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የአባልነት መዋጮ የሚከፍሉት በተቀጠሩበት መሥሪያ ቤት አማካኝነት ከወርሃዊ ደመወዛቸው ላይ ተቀናሽ እየተደረገ ነው።

የገዢው ፓርቲ አባላት የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች በፈቃዳቸው ይህንን መዋጮ የሚያደርጉ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥት ሠራተኞች ያለፍቃዳቸው ከደመወዛቸው ላይ መዋጮ መቆረጡን በመጥቀስ ቅሬታ የሚያቀርቡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው የማሻሻያ ረቂቅ፤ መሥሪያ ቤቶች ከሠራተኞቻቸው ደመወዝ ላይ የአባልነት መዋጮ የሚቁርጡበትን አሠራር ይከለክላል።

ረቂቁ፤ የመንግሥት ሠራተኛ ከሆነ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሚሰበሰብ የአባልነት መዋጮን "መሥሪያ ቤቱ በቀጥታ ከሠራተኛው ደሞዝ በመቁረጥ አባል ወደ ሆነበት የፖለቲካ ፓርቲ የባንክ ሂሳብ ማስገባት አይችልም" ሲል ክልከላ አስቀምጧል።

ረቂቁ፤ በገቢ ምንጭ ላይ የጣለው ክልከላ ይህ ብቻ አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች "ከማናቸውም ሰው የሚሰጥን ስጦታ ወይም እርዳታን" በግላቸው እንዳይቀበሉ ከልክሏል። በረቂቁ መሠረት ይህንን ዓይነቱን ስጦታ ወይም እርዳታ መቀበል የሚችሉት "በፓርቲው በኩል" ነው።

በዚህ ዓይነት መልኩ እርዳታ የተቀበለ ዕጩ "ድርጊቱ በተፈጸመ ወይም መፈጸሙን ባወቀ በ48 ሰዓት ውስጥ" ለምርጫ ቦርዱ ማሳወቅ እና "በዕጩነት ላቀረበው ፓርቲ የተደረገውን ስጦታ ወይም እርዳታ ማስረከብ" እንዳለበት ረቂቁ ላይ ተቀምጧል።

ድምፅ ለመስጠት የተሰለፉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, National Election Board of Ethiopia

ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተጣለው አስገዳጅ የፆታ ተዋጽዖ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ፤ ቦርድ በረቂቁ ካካተታቸው ለውጦች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተጣለው አስገዳጅ የፆታ ተዋጽዖ አንዱ ነው። የፆታ ተዋጽዖ አስገዳጅ ሆኖ ከቀረበባቸው የረቂቁ ክፍሎች መካከል አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን ይመለከታል።

ይህ የፆታ ስብጥር ጉዳይ የተቀመጠው ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ በሚያትተው የረቂቁ ክፍል ላይ ነው። በሥራ ላይ ባለው አዋጅ፤ ስለ መተዳደሪያ ደንብ ባሰፈረበት ክፍል ላይ ለፓርቲ ኃላፊነት የሚደረጉ ምርጫዎች "የፆታ ተዋጽፆን ያገናዘቡ" መሆን አንዳለባቸው ጠቅሷል።

አዲሱ ረቂቅ በበኩሉ ይህንን የፆታ ተዋጽዖ በቁጥር ተክቶታል። የማንኛውም ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ "የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች ቢያንስ 30 በመቶው አመራሮች ሴቶች እንደሚሆኑ የሚገልጽ ድንጋጌ" መያዝ እንዳለበት በረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

ረቂቁ፤ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው ዕጩዎች የፆታ ተዋጽዖ ላይም ተመሳሳይ የቁጥር አስገዳጅነት አካትቷል። ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ግንባር እና ቅንጅቶች ከሚያቀርቧቸው ዕጩዎች መካከል "ቢያንስ 20 በመቶውን" ሴቶች እንዲያደርጉ ረቂቁ ያስገድዳል።

"ይህን ሳያሟላ የዕጩዎቹን ዝርዝር ያቀረበ የፖለቲካ ፓርቲ፤ የዕጩዎች ምዝገባ እስኪጠናቀቅ ባለው ጊዜ ውስጥ ቦርዱ በሚወሰነው ቀናት አስተካክሎ ማቅረብ ይኖርበታል" ሲል ስለ ፆታ ስብጥሩ አስገዳጅነት ይጠቅሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለውይይት ባቀረበው ረቂቅ አዋጅ የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን የተመለከተ ማሻሻያም ይዟል።

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም የሚያስፈልጉት መሥራች አባላት ከሀገሪቱ አምስት ክልሎች የተወጣጡ መሆን አለባቸው።

የሀገሪቱ ክልሎች ከዘጠኝ ወደ 12 ከማደጋቸው በፊት የወጣውን አዋጅ የሚያሻሽለው አዲሱ ረቂቅ በአንጻሩ መሥራች አባላት የሚወጣጡባቸውን ክልሎች ብዛት በሁለት ጨምሮታል። ረቂቁ፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሀገር አቀፍ ሆኖ የሚመዘገበው ቢያንስ በሰባት ክልሎች መደበኛ ነዋሪ የሆኑ መሥራች አባላት ሲኖሩት እንደሆነ አስፍሯል።

አዲሱ ረቂቅ፤ ምርጫ ቦርድ በምሥረታ ላይ ላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚሰጠው ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ የቆይታ ጊዜ ላይም ለውጥ አድርጓል። የመሥራች አባላትን ፊርማ ለመሰብሰብ እና ለተያያዥ የምሥረታ ሥራዎች የሚሰጠው ይህ ፈቃድ የቆይታ ጊዜው ሦስት ወራት ነበር። መሥራቾቹ ተጨማሪ ጊዜ ካስፈለጋቸው ለተጨማሪ ሦስር ወር ሊራዘምላቸው እንደሚችል በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ተደንግጓል።

ማሻሻያው፤ የጊዜያው ፈቃዱን የቆይታ ጊዜ ወደ ስድት ወራት ያሳደገው ሲሆን፣ ተጨማሪ ሦስት ወራት ሊፈቀድ እንደሚችልም ይገልጻል። ይሁንና ይህ ፈቃድ በሚሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲ መሥራቾች ላይ ክልከላ ጥሏል።

ይህም "ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ መሥራቾች ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት፣ የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ ወይም ተመሳሳይ ድርጊቶችን ማካሄድ አይችልም" የሚል ነው።