የሶማሊያ ታጣቂዎች የአሜሪካን የጦር ሄሊኮፕተሮች የጣሉበት ወቅት በነዋሪዎች ሲታወስ

በአሜሪካ ጥቃት በርካታ ቤተሰቦቿን ያጣችው ቢንቲ አሊ ዋርድሄሬ

የፎቶው ባለመብት, Netflix

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ ጥቃት በርካታ ቤተሰቦቿን ያጣችው ቢንቲ አሊ ዋርድሄሬ
    • ፀሐፊ, አብዲሽኩሪ ሐይቤ-ቢቢሲ ሶማሊ
    • ዘገባው ከ, ናይሮቢ

በሆሊዉድ ተሠርቶ ዕውቅና ያገኘው 'ብላክ ሃውክ ዳውን' የተሰኘው ፊልም አሜሪካ በሶማሊያ ያደረገችው የከሸፈ ዘመቻ ሌላ መጠሪያ ሆኗል።

የሞቃዲሾው ጦርነት ይሰኛል።

ወቅቱ መስከረም 1986 ዓ.ም. ነበር።

አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎችን ገድሏል ያለችው መሐመድ ፋራህ ሃሰን ጋራድ ወይም ጄኔራል አይዲድን በሞቃዲሾ ለመያዝ የጦር ሄሊኮፕተሮቿን አሰማራች።

ጄኔራል አይዲድ በሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት ስሙ የገነነ የጦር አበጋዝ ነበር።

የአሜሪካ ዕቅድ ሳይሳካ ሁለት የጦር ሄሊኮፕተሮቿ ተመትተው ወደቁ።

18 አሜሪካውያን ወታደሮች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሶማሌዎች አለቁ።

ኔትፍሊክስ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ አንድ ዘጋቢ ፊልም ሠርቷል።

ቢቢሲ በበኩሉ ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት አሜሪካ የፈጸመችው ወታደራዊ ዘመቻ የማይሽር ጠባሳ አድርሶብናል ያሉ ሶማሌዎችን አናግሯል።

ሶማሊያ በወቅቱ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የነበረች ቢሆንም፣ የሞቃዲሾ ነዋሪዎች ሁኔታውን ተቀብለው ኑሯቸውን እየመሩ ነበር።

እሁድ መስከረም 23/1986 ዓ.ም. ዕለቱ ሞቃታማ ቢሆንም የውቅያኖሱ ነፋሻማ አየር ተጨምሮበት ሞቃዲሾን ቀዝቀዝ አድርጓታል።

በወቅቱ 24 ዓመቷ የነበረው ቢንቲ አሊ ዋርድሄሬ እናቷን ለመጠየቅ ከቤት ወጣች።

"እርግት ያለ ቀን ነበር" ትላለች ቢንቲ ቀኑን ስታስታውስ።

ልክ እንደ ሌላው የከተማው ነዋሪ አሜሪካውያን የጦር አበጋዙን መሐመድ ፋራህ አይዲድ ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጁ እንደሆነ አታውቅም ነበር።

ከዚያ በኋላ የተፈጠረው ነገር ሕይወቷን ቀየረው።

አሜሪካውያን ወታደሮች ከብላክ ሃውክ ዳውን ሄሊኮፕተር ለመውረድ ሲዘጋጁ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካውያን ወታደሮች ከብላክ ሃውክ ዳውን ሄሊኮፕተር ለመውረድ ሲዘጋጁ

አሜሪካ ወታደሮቿን ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ በሶማሊያ አሰማርታ ነበር።

ወታደሮቹ የተሰማሩትም የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ በተከሰተው ረሃብ እርዳታ ለማድረግ የገባው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮን ለማገዝ ነው ተባለ።

ሰኔ ወር 1986 ዓ.ም. ላይ 24 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት ተገደሉ። በዚህም ግድያ ውስጥም ጄኔራል አይዲድ እንዳለበት ተገለጸ። ጄኔራሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ጥቃቶች ዋነኛ ዒላማ ሆነ።

የአሜሪካ ወታደሮች በሐምሌ ወር ላይ በፈጸሙት ወረራ 70 ሶማሌዎች ተገደሉ። ይህንንም ተከትሎ አሜሪካውያን በሶማሊያውያን ዘንድ የሚታዩበት መንገድ ለዘላለም ተቀየረ።

አሜሪካ ልዩ ወታደሮቿንም አሰፈረች።

መስከረም 23/1986 ዓ.ም. ጄኔራል አይዲድ ከከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ጋር በአንድ ሆቴል ስብሰባ እንደሚቀመጥ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የደኅንነት መረጃዎችን አገኙ። አሜሪካውያን 90 ደቂቃ ይፈጃል ብለው ያቀዱትን የአየር ጥቃት ጀመሩ። ሆኖም ያላሰቡት ሆኖ ውጊያው ለ17 ሰዓታት ያህል ድረስ ዘለቀ።

ለቢንቲ በወቅቱ ያልተለመደ ነገር እየተከሰተ ለመሆኑ ያሳያት የጆሮ ታምቡር የሚበሳ የፍንዳታ ድምጽ መስማቷ ነበር።

በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 9፡30 ሆኗል ፍንዳታው ሲጀምር።

የሞቃዲሾ ነዋሪዎች የተኩስ ድምጽን ቢላመዱም የፍንዳታው ከባድ መሆን፣ ቀጥሎም አስደንጋጭ ማዕበል መከተሉ አዲስ ክስተት ስለመከሰቱ ፍንትው ያለ እውነታ ነበር።

ነዋሪዎች ተበታትነው በየአቅጣጫው መሮጥ ጀመሩ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢንቲ እየሆነ ያለውን ነገር ለመረዳት ዘመዷ ቤት ጣሪያ ላይ ወጣች።

እዚያም ሆና ፍልሚያው ሰፈሯ ላይ እየተደረገ መሆኑን ተረዳች። ሁለት የአሜሪካ ብላክ ሃውክ የተሰኙት የጦር ሄሊኮፕተሮች ተመትተው ወደቁ።

አንደኛው ከሰዓት 10፡20፣ ሁለተኛው የመጀመሪያው ከወደቀ ከ30 ደቂቃ በኋላ። የአሜሪካ ወታደራዊ ግብረ ኃይል ተከበበ፣ ከዚያም እነሱን የማዳን ተልዕኮ ተጀመረ።

ለሕይወቷ የፈራችው ቢንቲ ወደ ቤቷ ሮጠች።

"እስከ ዛሬ ድረስ ጎዳናዎች ላይ ያየኋቸው ተበጣጥሰው የወደቁት አስክሬኖች ይመላለሱብኛል" ትላለች ቢንቲ።

ቢንቲ ቤቷ የደረሰችው ምሽት 12 ሰዓት ገደማ ነበር። ሁሉም ሰው ደህና ሆኖ በማግኘቷ ተረጋጋች።

ፍልሚያው ትንሽ ቀለል ማለቱን ተከትሎ ለአጭር ጊዜም ቢሆን መረጋጋት መጥቶ ነበር።

ባለቤቷ ከጎረቤት ጋር ስለ ጦርነቱ ሲወያይ ቢንቲ ሻይ አቀረበች። ነገር ግን መኖሪያ ቤታቸው በከባድ መሳሪያ መመታቱን ተከትሎ ባለቤቷ የቀረበለትን ሻይ እንኳን የመቅመስ ዕድል አላገኘም።

ቢንቲ እጇ በከፊል የተቆረጠ መሰላት። መሬት ላይ ወደቀች፣ አንዲት ሴት ላይዋ ላይ ተከመረችባት።

"ጭንቅላቴ ላይ ሙቅ ውሃ የፈሰሰ መሰለኝ። ቧምቧውን ማን ከፈተው ብዬ አሰብኩ" ስትል ታስረዳለች።

ከዚያም የረጠባት ነገር ላይዋ ላይ የነበረችው ሴት ደም ነበር። ውጊያውን ፈርታ ቤታቸው ልትጠለል የመጣችው ጎረቤታቸው ተገደለች።

በዚያች ምሽት የቢንቲ ባለቤት መሐመድ አደን፣ የ14 ዓመት ልጇ አብዱልቃድር መሐመድ፣ ሌላኛው ልጇ የ13 ዓመቱ አብዱራህማን መሐመድ ተገደሉ።

ሌሎች አራት ልጆቿ እና አብሯቸው ይኖር የነበረው ወንድሟ ቆሰሉ። ወንድሟ በደረሰበት ጉዳት በኋላ ላይ ሕይወቱ አለፈ።

በወቅቱ ገና የአራት ዓመት ሕጻን የነበረችው ኢፍራህ ዓይነ ስውር ሆነች።

የቢንቲ የበኩር ልጅ እና የልጅ አባት በአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ አሁንም ትግሉን ቀጥሏል። እስከ አሁን ድረስ አውሮፕላን ሲያይ ወይም ድምጹን ሲሰማ ይደበቃል።

የአሜሪካ ወታደራዊ መኪና በሞቃዲሾ መዲና ላይ ሲቃጠል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ወታደራዊ መኪና በሞቃዲሾ መዲና ላይ ሲቃጠል

በዚያች እሁድ ዕለት ታዋቂው ፎቶግራፈር አህመድ መሐመድ ሐሰን ወይም አህመድ ፋይፍ ቪዲዮ እየቀረጸ ነበር።

በወቅቱ 29 ዓመቱ የነበረው አህመድ ፋይፍ ከዚያ ቀደም የጎሳ ጦርነቶችን፣ ረሃብ እና ሌሎች ክስተቶችን በካሜራው ሲያስቀር ነበር።

የሄሊኮፕተሮች ድምጽ፣ እና የከባድ መሳሪያዎች ድምጽ ከዚህ በፊት ከነበሩ የተኩስ ልውውጦች የተለየ ክስተት መሆኑን ለመረዳት ረጅም ጊዜ አልፈጀበትም።

እንዲህ ዓይነት ክስተት ከዚህ ቀደም ያጋጠመው ለፀረ አሜሪካዊነት ስሜት መነሻ የሆነው እና ለዚህም ውጊያ በር የከፈተው አሜሪካ በሐምሌ ወር የፈጸመችው ወረራ ነበር።

አህመድ ካሜራው ከእጁ አትለየውም ነበር። ይህንንም ትርምስ ሲያይ ወዲያውኑ ካሜራውን አንስቶ መቅረጽ ጀመረ።

በመጀመሪያው ቀን በአሜሪካ ወታደሮች እና በሶማሊያውን መካከል የተካሄደውን ፍልሚያ በካሜራው አስቀረ። በሁለተኛው ቀን አሜሪካዊው ፓይለት ማይክል ዱራንት ወደ ተያዘበት ስፍራ ተወሰደ።

ማይክል በሶማሌ ተዋጊዎች ሮኬት ተመትቶ የወደቀውን ሁለተኛውን ብላክ ሃውክ ሄሊኮፕተር እያበረረ ነበር። ሄሊኮፕተሩ መውደቁን ተከትሎ በውስጡ የነበሩ ሦስት ወታደሮች እንዲሁም ሊታደጓቸው የመጡ ሁለት ሰዎች ሲዋጉ ተገደሉ።

"ከፍተኛ ፍልሚያ ነበር። ሁለተኛው ሄሊኮፕተር በወደቀበት ስፍራ 25 ሶማሌዎች ተገድለዋል። ይሄ ምን ያህል የተፋፋመ ፍልሚያ እንደነበር የሚያሳይ ነው" ሲል ፓይለቱ ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

ታዋቂው ፎቶግራፍር አህመድ መሐመድ ሐሰን ወይም አህመድ ፋይፍ

የፎቶው ባለመብት, Netflix

የምስሉ መግለጫ, ታዋቂው ፎቶግራፈር አህመድ መሐመድ ሐሰን ወይም አህመድ ፋይፍ

አብራሪውን በሕይወት ቢያቆዩት ዋጋ ሊኖረው እንደሚችል ያመኑት ታጣቂዎቹ በቁጥጥራቸው ስር አቆዩት።

አህመድም መወዛገብ የሚታይበትን ፓይለት ቀረጸው። ትንፋሽ በላይ በላዩ ላይ እየተነፈሰ እና ወደ ጎንም ሰረቅ እያደረገ ከካሜራ ውጪ እየተመለከተ ማንነቱን አረጋገጠ። በዚያን ወቅት አሜሪካም ሆነ ጄኔራል አይዲድ ፓይለቱ መያዙን አላወቁም ነበር።

"የቀረጽኳቸውን ቪዲዮዎች በየቀኑ ከሞቃዲሾ ወደ ናይሮቢ በሚበረው የተባበሩት መንግሥታት አውሮፕላን እልከው ነበር።"

"የሞቃዲሾው ጦርነት ለዓለም የደረሰው እኔ በቀረጽኳቸው ቪዲዮዎች አማካኝነት ነው። በወቅቱ ለሲኤንኤን በፍሪላንስ ዘጋቢነት እሠራ ነበር" ይላል።

አህመድ ያነሳቸው ምሥሎች በዓለም ዙሪያ ባሉ ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን አርዕስተ ዜና ሆኑ። በተጨማሪም አሜሪካ በአህጉሪቷ ውስጥ እያካሄደችው ያለውን የጦርነት ፖሊሲ በሚመለከትም ክርክር አስነሱ።

"ምንም እንኳን በወቅቱ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖ ባላስብም አሁን እኮራበታለሁ" ይላል አህመድ።

ሄሊኮፕተሮቹ በወደቁ በስድስት ወራት ውስጥ አሜሪካ ጦሯን ከሶማሊያ አስወጣች። የሶማሊያ ወታደራዊ ተልዕኮ አለመሳካቱ አሜሪካ በቀጣዩ በአፍሪካ ውስጥ ቀጥታ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ እንዳደረጋት ይጠቀሳል።

 ሳይዳ ኦማር ሞሃሙድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳይዳ ኦማር ሞሐሙድ

በዚያች ዕለት ሳይዳ ኦማር ሞሐሙድ ሴት ልጅ ተገላገለች። ቤተሰቡ ሁሉ እልልታውን አቀለጡት፤ በደስታ ተሞሉ። ቤተሰቦች፣ ዘመዶች እና ጎረቤቶች በቤት ተሰብስበው ለባህላዊ የስም አወጣጥ ሥነ ሥርዓት መዘጋጀት ጀመሩ።

ነግር ግን ፍልሚያው መጀመሩን ተከትሎ ደስታቸው ወደ ሐዘን ተቀየረ።

የመጀመሪያው ሄሊኮፕተር ከነ ሳይዳ ቤት ፊት ለፊት ሲወድቅ ኃይለኛ ትርምስ ተፈጠረ።

ከትንሽ ቆይታ በኋላም ቢያንስ 10 የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ቤታቸው ዘው ብለው እንደገቡ ታስታውሳለች።

ሁሉንም ወደ ሳሎን ሰበሰበቧቸው እና እንዳይንቀሳቀሱ አዘዟቸው። ከዚያም ቤታቸውን ወደ ድንገተኛ ሆስፒታልነት ቀየሩት።

የቆሰሉ ወታደሮች በመመገቢያ ጠረጴዛቸው ላይ እንዲንጋለሉ ተደርገው አስቸኳይ ህክምና ሲደረግላቸው ቤተሰቡ በድንጋጤ ተመለከተ።

"በጣም ፈርተን ነበር። ቤታችንን ምሽግ አድርገውት ነበር" ስትል ሳይዳ ታስረዳለች።

ትርጉም ያለው ስም መስጠት የሚወዱት ሶማሌዎች ይህችን ልጅም አሚና ሬንጀርስ አሏት።

አዲሱ የኔትፍሊክስ ዘጋቢ ፊልም በሞቃዲሾ ጦርነት በሁለቱም ወገን የነበሩ ወገኖችን ቃለ መጠይቅ ይዟል። በተጨማሪም እንደ ቢንቲ ያሉ ሶማሌዎች በጦርነቱ ወቅት ያጋጠሟቸውን አሰቃቂ ሁኔታዎች ይዟል።

ለቢንቲ አሊ ታሪኩን መናገሩ ብቻ በቂ አይደለም። በጦርነቱ የምትወዳቸውን ቤተሰቦች አጥታለች። ሆኖም እንደ እሷ በሶማሌ ቤተሰቦች ላይ ለደረሱ እልቂቶች እውቅና እንዳልተሰጠ ይሰማታል።

"ቤቴን ያወደሙት፣ ባለቤቴን፣ ልጆቼን የገደሉት አሜሪካውያን ናቸው። ለዘላቂ መከራ ዳርገውኛል። ቢያንስ የሠሩትን ጥፋት አምነው ካሳ መክፈል አለባቸው" ትላለች ቢንቲ በተሰባበረ ድምጽ።