ትራምፕ፤ መስክ የሚያቋቁመውን የፖለቲካ ፓርቲ በአሜሪካ ያለው የሁለት ፓርቲ ሥርዓት ነው ሲሉ አጣጣሉ

ትራምፕ እና መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ የቅርብ አጋራቸው ቱጃሩ ኤለን መስክ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ማቀዱን፤ በአሜሪካ ያለው የሁለት ፓርቲ ሥርዓት ነው በማለት "አስቂኝ" ሲሉ አጣጣሉ።

"ሦስተኛ ፓርቲ መመሥረት አስቂኝ ይመስለኛል" ሲሉ ትራምፕ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"በአሜሪካ ሁልጊዜም ቢሆን ያለው የሁለት ፓርቲ ሥርዓት ነው፤ ያለው እናም ሦስተኛ ፓርቲ መመሥረት ግራ መጋባትን ያመጣል" ብለዋል።

ለሳምንታት ያህል ሃሳቡን ሲያንሸራሽር የቆየው ቱጃሩ ኤለን መስክ ሁለቱ የአሜሪካ አንጋፋ ፓርቲዎችን ሪፐብሊካን እና ዲሞክራቲክን የሚገዳደር "ዩኒፓርቲ" የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሜያለሁ ብሏል።

ትራምፕ እና መስክ አጋርነታቸው የጠበቀ ነበር።

የቴስላ ኃላፊው መስክ የፌደራል መንግሥት ወጪዎችን ለመቀነስ ሥልጣን የተሰጠው የመንግሥት ቅልጥፍና መሥሪያ ቤት (ዶጅ) ተብሎ የሚጠራው ተቋምን ይመራ ነበር።

መስክ ለአሜሪካ ብሔራዊ ዕዳ መቆለል አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የሚላቸውን የመንግሥት ፖሊሲዎች በተደጋጋሚ ሲተች ይደመጣል።

አዲሱ ፓርቲ በመጪው ጊዜ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩን ሊደግፍ ቢችልም "የቀጣዮቹ 12 ወራት ትኩረቱ በምክር ቤቱ እና በሴኔት ላይ ነው" ሲል መስክ እሁድ ዕለት አስታውቋል።

ትራምፕ በተጨማሪ "ኤሎን መስክ ሙሉ በሙሉ ሃዲዱን ስቶ ባለፉት ሳምንታት እንዲህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ መግባቱን ማየቴ አሳዝኖኛል" ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ትራምፕ በተጨማሪም "ሁሉም ነዋሪዎች በአጭር ጊዜ የኤሌክትሪከ መኪና እንዲገዙ የሚያስገድድ" "የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ትዕዛዝ" መመሪያ እንዲሆን ጫና አድርጓል ሲሉ መስክን ተችተውታል።

በቅርቡ ሕግ ሆኖ የጸደቀው የፕሬዚዳንት የግብር እና ወጪ ዕቅድ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የነበረውን የግብር እፎይታ እንዲያከትም አድርጎታል።

የግብር እፎይታውን በዋነኝነት የሰረዙበትን ምክንያት ያብራራሩት ትራምፕ ቀድሞውኑ መስክ ያቀረበውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ትዕዛዝ (Electric Vehicle mandate) ከጅምሩ መቃወማቸውን አክለዋል።

"ሰዎች የፈለጉትን መኪና፤ በቤንዚን፣ በናፍጣ የሚሠራ ወይም ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ መግዛት ይችላሉ። ከአሁኑ በኋላ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ትዕዛዝ የሚባል የለም" ብለዋል።

በቅርቡ የጸደቀው በጀት ለድንበር ቁጥጥር፣ ለመከላከያ እንዲሁም ለኃይል ምርቶች ጭማሪ ያደረገ ሲሆን፣ በአወዛጋቢ ሁኔታም የጤና አጠባበቅ እና የምግብ ድጋፍ መርሃ ግብሮችን በጀት ቀንሷል።

የትራምፕን የወጪ ዕቅድ በተደጋጋሚ በመተቸት ከፕሬዚዳንቱ ጋር እሰጣገባ የገባ ውስጥ የገባው መስክ በሳምንቱ መጨረሻ ከትችቱ በኋላ ነው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለመቋቋም መነሳቱን ያሳወቀው።