ከፍተኛ ሙቀት በተመዘገበባቸው የአውሮፓ አገራት ሰደድ እሳት ተስፋፋ

የእሳት አደጋ ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በአውሮፓ አገራት ከፍተኛ ሙቀት ተመዝግቦ በሚገኝበት ወቅት በሺዎች የቀሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በተለያዩ አገራት የተነሳውን የሰደድ እሳት ለማጥፋት እየታገሉ ነው።

በፖርቹጋል፣ ስፔን፣ ግሪክ እና ፈረንሳይ የተነሳው የሰደድ እሳት ከቦታ ቦታ እየተዛመተ ነው።

በደቡባዊ ፈረንሳይ 11ሺህ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲወጡ ተደርገዋል። በደቡባዊ ስፔን ደግሞ 2 ሺህ 300 ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።

በደቡብ ፈረንሳይ ብቻ እሳቱ ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት አውድሟል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእሳት አደጋ ሠራተኞች የሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር እየጣሩ ሲሆን፤ በሰሜን ፖርቱጋል ውሃ የሚረጭ አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ አብራሪው ሕይወቱ አልፏል።

ከማክሰኞ ጀምሮ በፖርቱጋል እስከ 47 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ሙቀት የተመዘገ ሲሆን፤ በስፔን ደግሞ ሙቀቱ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ነበር። ይህም ለሰደድ እሳቱ መዛመት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ተብሏል።

በፈረንሳይ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት የተመዘገበ ሲሆን፤ በቀጣይ ሳምንትም የሙቀት መጠኑ ሊጨምር እንደሚችል ይጠበቃል።

እስካሁን በስፔን እና ፖርቹጋል ከከፍተኛው ሙቀት ጋር በተያያዘ ከ300 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

በተመሳሳይ በዩናትድ ኪንግድም ከፍተኛ የሙቀት መጠን ማስጠንቀቂያ በአገሪቱ ሜትሮሎጂ ተቋም ተሰጥቷል።

ለንደን፣ ማንችስተር እና ዮርክ አካባቢን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊደርስ ስለሚችል ሰዎች ጥንቃቄ ያድርጉ ተብሏል።

የአየር ትንበያ ተቋሙ ሙቀቱ በሕይወት ላይ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል የተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች መለወጥ አለባቸው ብሏል።

በሜዲትራኒያነe አካባቢ ያሉ አገራትም በሙቀት እና በሰደድ እሳት ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

የጣሊያን መንግሥት ከፍተኛ ድርቅ በተከሰተበት ፖ ቫሊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

በግሪክ ደግሞ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ከመዲናዋ አቴንስ በስተደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 50 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ የተቀሰቀሰን የሰደድ እሳት ለማጥፋት ትግል ላይ ናቸው። በዚህ የግሪክ ክፍል 7 መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንዲወጡ ተደርጓል።

እንዲሁም ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟታል። በሰሜን ሞሮኮ ሰደድ እሳቱ አንድ መንደርን ሙሉ በሙሉ ያወደመ ሲሆን፤ የአገሪቱ መንግሥት በበርካታ መንደሮች ውስጥ ይኖኑ የነበሩ ነዋሪዎችን ማስወጣት ግድ ብሎታል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአካባቢ አየር ለውጥ ምክንያት የሚከሰተው የሙቀት መጠኑ እና የሚዘልቅበት ጊዜ እየተራዘመ መጥቷል።

የዓለማችን የሙቀት መጠን እየጨመረ ሲሆን፤ መንግሥታት የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ካልጀመሩ በአየር ለውጥ ምክንያት የሚከሰተው አደጋ የከፋ እየሆነ ይሄዳል።