ዋትስአፕ መንግሥታት ኢንተርኔትን ቢዘጉም ሰዎች መልዕክት እንዲለዋወጡ አስችላለሁ አለ

ዋትስአፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓለም ዙሪያ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ኢንተርኔት ተቋርጦባቸውም መልዕክት እንዲለዋውጡ አስችላለሁ አለ።

በሜታ ባለቤትነት የሚተዳደረው የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያው በኢራን ያጋጠመው ዓይነት ‘ዳግም አይከሰትም’ ብሏል።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ መንግሥታት ኢንተርኔትን ቢያቋርጡም ሆነ ክልከላ ቢጥሉ በሌላ ስፍራ በሚገኙ ሰርቨሮች አማካይነት ሰዎች ዋትስአፕን መጠቀም እንዲችሉ ይደረጋል ብሏል።

የቴክኖሎጂ ባለሙያው ጁራስ ጁረሴናስ ዋትስአፕ ይህን ማድረጉ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ በሚደረግባቸው አገራት ያሉ ሰዎች በነጻነት በዋትስአፕ ግንኙነት መፍጠር እንዲችሉ ያስችላል ብለዋል።

በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች የኢንተርኔት ግንኙነታቸው ሌላ ዓላማ ባላቸው አካላት እንዲቋረጥ ቢደረግም የኢንተርኔት አገልግሎታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል ነው ይላሉ ይህ ባለሙያ።

ድርጅቱ አዲስ አግልግሎቱን ይፋ እንደሚያደርግ ባስታወቀበት መግለጫው ሰዎች ሰብአዊ መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት ገልጾ፤ “ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ እንዳያገኙ ተከልክለዋል” ብሏል።

ዋትስአፕ “ሰዎች በነጻነት መልዕክት እንዲለዋወጡ” በጎ ፍቃደኞች ‘ፕሮክሲ ሰርቨሮችን’ እንዲለግሱ ጠይቆ፤ ፕሮክሲ ሰርቨሮች ወደ ሥራ እንዴት ማስገባት እንደሚቻል ምክር ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ብሏል።

“በፕሮክሲ አማካይነት መገናኘት ዋትስአፕ ከሚያቀርበው ከፍተኛ ግለኝነት (ፕራይቬሲ) እና ደኅንነት ጋር ተመሳሳይ ነው” ብሏል የቴክኖሎጂ ኩባንያው።

የግል መልዕክቶች በላኪው እና በተቀባዩ ብቻ እንጂ በዋትአፕም ሆነ በፕሮክሲ ሰርቨሮቹ አማካይነት ሊታዩ እንደማይችሉ በመግለጽ የመልዕክት ሚስጢራዊነት የተጠበቀ መሆኑን ገልጿል።

እንደ ስታቲስታ ከሆነ ዋትስአፕ በወር ንቁ የሆኑ 2 ቢሊዮን ተጠቃሚዎችን በመያዝ የዓለማችን ቁጥር አንድ መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ ነው።

ከዋትስአፕ በመቀጠል ዊቻት እና ፌስቡክ ሜሴንጀር እያንዳንዳቸው 1.2 ቢሊዮን እና 988 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን በመያዝ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ዋትስአፕ ሰዎች የጸሑፍ መልዕክት፣ የድምጽ እና የቪዲዮ ጥሪ ማድረግ በተጨማሪ ተጠቃሚዎች ምሥሎችን እንዲላላኩ ያስችላል።