የዕጽ አዘዋዋሪው ኤል ቻፖ ልጅ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በሜክሲኮዋ ግዛት አመጽ ተቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ሜክሲኳዊው ዕጽ አዘዋዋሪ ኤል ቻፖ ጉዝማን ልጅ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በሜክሲኮዋ ግዛት ከፍተኛ አመጽ ተቀሰቀሰ።
የአባቱን ሲናሎአ የዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን ይመራል የተባለው ኦቪዲዮ ጉዝማን-ሎፔዝ በኩሊያካና በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ወደ መዲናዋ ሜክሲኮ ሲቲ እንዲዘዋወር ተደርጓል።
በኤል ቻፖ ልጅ እስር የተበሳጩ አደገኛ ቡድን አባላት ከጸጥታ አካላት ጋር ከባድ የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል። መንገድ ዘግተዋል፣ መኪኖችን እና መኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል እንዲሁም በአየር ማረፊያ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ሁለት አውሮፕላኖች በጥይት የተመቱ ሲሆን ሲናሎአ አየር ማረፊያ ከ100 በላይ በረራዎችን ለመሰረዝ ተገዷል።
እስካሁን ቢያንስ የሦስት ፖሊስ አባላት ሕይወት ማለፉ የተገለጸ ሲሆን፤ የግዛቷ አስተዳዳሪ ቢያንስ 18 ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብለዋል።
‘ዘ ማውስ’ ተብሎ የሚጠራው ጉዝማን-ሎፔዝ አባቱ የመሰረተውን ሲናሎአ ካርቴል በመምራት ክስ እንደቀረበበት የአገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ሉዊስ ክሬሴንሲኦ ሳንዶቫል ተናግረዋል።
ሲናሎዓ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን በዓለማችን ላይ ግዙፍ ከሚባሉ ዕጽ አምራች እና አዘዋዋሪ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።
ይህን ቡድን የመሰረተውን እና ለረዥም ጊዜ ሲመራ የቆየው ጆአኪን ‘ኤል ቻፖ’ ጉዝማን እአአ 2019 ላይ በዕጽ ዝውውር እና በሕገ-ወጥ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብሎ አሜሪካ በሚገኝ እስር ቤት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ይገኛል።

የፎቶው ባለመብት, US STATE DEPARTMENT
አሜሪካ ጉዝማን-ሎፔዘ እና ሦስት ወንድሞቹ የሚገኙበትን ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ ብላ ነበር።
ጉዝማን-ሎፔዘን ለመያዝ በተደረገው ኦፕሬሽን አሜሪካ ተሳትፎ ማድረጓን የሜክሲኮ መከላከያ ሚንስትር ገልጸዋል።
ከእስሩ በኋላ ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ የወጡ ምስሎች ቤቶች ሲቃጠሉ እና መንገዶች ተዘግተው አሳይተዋል። መደብሮች ላይ ዘረፋ ተፈጽሟል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ የከተማው ባለስልጣናት ማሳሰቢያ ሰጥተው የነበረ ሲሆን ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ በዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን አባላት እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል ሲደረግ ቆይቷል።
የሜክሲኮ ባለስልጣናት እአአ 2019 ላይ ጉዝማን ሎፔዘን በቁጥጥር ሥር አውለውት የነበረ ቢሆንም በደጋፊዎቹ አማካይነት ሊቃጣ የሚችለውን ጥቃት በመስጋት ለቀውት ነበር።
እንደ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከሆነ ጉዝማን-ሎፔዝ እና ወንድሙ ጆአኪን በአሁኑ ወቅት በሲናሎአ ግዛት በወር ከ1ሺህ300 እስከ 2ሺህ200 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕጽ የሚያመርት 11 የሜታምፌታሚን ፋብሪካዎችን ያስተዳድራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ጉዝማን-ሎፔዝ ለፖሊስ መረጃ የሚያቀብሉ ሰዎችን ስለመግደሉ፣ በዕጽ ዝውውር እና በልደት በዓሉ ላይ ለመዝፈን ፍቃደኛ የልሆነ ሙዚቀኛ ስለመግደሉ መረጃዎች ያመላክታሉ ብላለች።












