ሕንድ እና ፓኪስታን ለቀናት የቆየውን ግጭት ለማብቃት ተኩስ ለማቆም ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአራት ቀናት ከቆየ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት በኋላ ሕንድ እና ፓኪስታን በከባድ መሳሪያ እና በድሮኖች ሲፈጽሙ የቆዩትን ጥቃት ለማቆም የሚያስችል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።
በአሜሪካ ሸምጋይነት በሁለቱ ኒውክሌር ታጣቂ አገራት መካከል ተኩስ ለማቆም ስምምነት መደረሱን ትሩዝ በተባለው የሶሻል ሚዲያ ላይ ፍንጭ የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራም ናቸው።
ቀደም ብሎ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተው ውጥረቱን እንዲያረግቡ ጥሪ እቅርበው ነበር።
የፓኪስታኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር አገራቸው የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቷን አረጋግጠዋል። ሚኒስተሩ ለአገራቸው የመገናኛ ብዙኃን በዲፕሎማቲክ ጥረቱ ውስጥ ቱርክ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊን ጨምሮ "በርካታ አገራት" መሳተፋቸው ተናግረዋል።
የሕንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪክራም ሚስሪም በበኩላቸው "በምድር፣ በአየር እና በባሕር" አገራቸው የምትወስደው እርምጃን ለማቆም መስማማቷን አረጋግጠዋል። ጨምረውም ተኩስ አቁሙ በሰዓታት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።
የሁለቱ አገራት መሪዎችን ጨምሮ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ባለሥልጣናት ውይይት እንደሚያደርጉ፤ በተለይ ደግሞ ሰኞ ዕለት ሁለቱ አገራት ይፋዊ ንግግር እንደሚጀምሩ ታውቋል።
ስምምነቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የሕንድ የመከላከያ ባለሥልጣናት ኒው ዴልሂ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ስምምነቱን እንደተቀበሉ ነገር ግን አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ ሁሉ አገራቸውን ለመከላከል ዝግጁ ሆነው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።
ከረቡዕ ጀምሮ በተቀሰቀሰው የሁለቱ አገራት ድንበር ዘለል ግጭት የፓኪስታን የአየር ክልል ዝግ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ግን የአየር ክልሏ ለሁሉም አውሮፕላኖች ክፍት መሆኑን አስታውቃለች።
ለዘመናት በፍጥጫ፣ አልፎ አልፎም ጦርነት ውስጥ የቆዩት ሁለቱ ተጎራባች አገራት ዓለምን ያሳሰበውን ግጭት የጀመሩት ባለፈው ረቡዕ ሕንድ "የሽብር ቡድኖች" ይዞታ ናቸው ባለቻቸው በፓኪስታን እና በፓኪስታን ቁጥጥር ስር በምትገኘው ካሽሚር ውስጥ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው።
ሕንድ ይህንን ጥቃት እንድትፈጽም ምክንያት የሆናት ከሁለት ሳምንት በፊት በቁጥጥሯ ስር ባለው ካሽሚር ውስጥ ታጣቂዎች ከ20 የሚበልጡ ሕንዳውያን ቱሪስቶችን መግደላቸውን ለመበቀል ነው።
ሕንድ ጥቃቱን የፈጸሙት በፓኪስታን የሚደገፉ ታጣቂዎች ነው በሚል ብትከስም ፓኪስታን ግን ስለክስተቱ የምታውቀው ነገር እንደሌለ ስታስተባብል ቆይታለች።
ባለፉት አራት ቀናት ሁለቱ አገራት ከድንበር ባሻገር ዘልቀው ጥቃት በሚያደርሱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በከባድ መሳሪያዎች ወታደራዊ ዒላማ ናቸው ያሏቸው ቦታዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
ሁለቱም መንግሥታት አንዳቸው ሌላኛውን ግጭቱን በማባባስ ሲከስሱ የቆዩ ሲሆን፣ የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የኒውክሌር ጦር ማሳሪያን በተመለከተ እና በሌሎች ቁልፍ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጠውን ቡድን ዛሬ ጠዋት ለስብሰባ ጠርተው ነበር።
ባለፉት ቀናት በሕንድ እና በፓኪስታን ውስጥ በሚገኙ ቦታዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሁለቱም አገራት ወደ ከስድሳ በላይ ሰላማዊ ሰዎች በግዛቶቻቸው ውስጥ መገደላቸውን ገልጸዋል።












