ከድሮን እስከ ኒውክሌር ከታጠቁት ከሕንድ እና ከፓኪስታን በወታደራዊ ኃይል ማን የበለጠ ነው?

የጦር ማሰሪያ እና ወታደሮች

ባለፈው ረቡዕ ሕንድ በፓኪስታን እና ፓኪስታን በምትቆጣጠረው የካሽሚር ግዛት ላይ ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ ፓኪስታን 25 የሕንድ ድሮኖችን መትታ መጣሏል አስታውቃለች።

ሕንድም በበኩሏ ከፓኪስታን የተወነጨፉ "ድሮኖችን እና ሚሳዔሎችን" መምታቷን ገልጻለች።

ሁለቱ አገራት ያላቸው ወታደራዊ አቋም ምን ይመስላል። ቀጥሎ የሕንድ እና የፓኪስታን ወታደራዊ አቋም በንጽጽር ቀርቧል።

ድሮኖች

ድሮን

የፎቶው ባለመብት, General Atomics Aeronautical Systems

ሁለቱም አገራት ያሏቸውን የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ቁጥርን ለማሳደግ ከውጭ አገራት በመግዛት እና እራሳቸው ሲያመርቱ ቆይተዋል። ነገር ግን ከቁጥር አንጻር ሕንድ በርካታ ድሮኖች ታጥቃለች።

በዓለማችን ከፍተኛ ሕዝብ ያላት ሕንድ በሚቀጥሉት ከሁለት እስከ አራት ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ አምስት ሺህ ያህል ድሮኖች ይኗሯታል ሲሉ የመከላከያ ትንታኙ ራሁል ቤዲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ሕንድ 31 የጦር መሳሪያ የሚታጠቁ ስካይጋርዲያን እና ሲጋርዲያን የተባሉ ከፍ ብለው መብረር የሚችሉ እና አየር ላይ ለረጅም ሰዓታት መቆየት የሚችሉ ድሮኖችን ከአሜሪካ ለመግዛት ስምምነት ተፈራርማለች።

ምንም እንኳን ፓኪስታን ከሕንድ ያነሰ ቁጥር ያላቸው ድሮኖች ቢኖሯትም፤ ወታደራዊ ድሮኖቿ ለቅኝት፣ ለስለላ እና ለተመረጡ ጥቃቶች የመዋል የተለያየ አቅም አላቸው።

የፓኪስታን ድሮኖች በተለይ ከውጊያ አቅም ጠንካራ መሆናቸው ይነገራል። ለምሳሌም ፓኪስታን ስሪት የሆነው 'ቡራቅ' የሚባለው የውጊያ ድሮን ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ በፀረ ሽብር ዘመቻዎች ላይ ጥቅም ላይ ውሏል። በተጨማሪም ዘመናዊ ድሮኖችን ከቱርክ እና ከቻይና አስገብታለች።

የመከላከያ በጀት እና የሠራዊት ብዛት

ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሁለቱ አገራት በአውሮፓውያኑ 1999 ካደረጉት የመጨረሻው ጦርነት ወዲህ አሁን በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ወደ ሙሉ ጦርነት ተመልሰው ይገባሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ከ1.4 ሚሊዮን በላይ መደበኛ ሠራዊት ያላት ሕንድ በግሎባል ፋየር ፓወር ደረጃ መሠረት ከዓለም ኃያል የሆነ ወታደራዊ አቅም ካላቸው አገራት በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ፓኪስታን ደግሞ 654,000 መደበኛ ሠራዊት በመያዝ በወታደራዊ አቅም ከዓለም በ12ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በ2024 ሕንድ ለመከላከያ ኃይሏ ከ86 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ከፓኪስታን ዘጠኝ ዕጥፍ የሚበልጥ ገንዘብ ማውጣቷን የስቶክሆልም ኢንተርናሽናል ፒስ ኢኒስቲቲዩት መረጃ ያመለክታል።

የምድር ኃይልን በተመለከተ ሕንድ ከ4,200 ታንኮች በላይ እና 150 ሺህ ወታደራዊ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ባለቤት ስትሆን፤ ፓኪስታን ደግሞ ከ2,600 ታንኮች እና ከ18 ሺህ ያነሰ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች አሏት።

የሕንድ አየር ኃይል 513 ተዋጊ ጄቶች እና 130 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን ጨምሮ በአጠቃላይ 2,229 አውሮፕላኖች አሉት። በግሎባል ፋየር ፓወር መረጃ መሠረት ፓኪስታን በአጠቃላይ 830 ያህል አውሮፕላኖች አሏት።

በባሕር ኃይል በኩል ሕንድ ከፓኪስታን በዕጥፍ የሚበልጡ የተለያዩ ዓይነት 293 የባሕር ኃይል መርከቦች አሉት።

ሚሳዔሎች እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች

የኒውክሌር አረር ጭምር መሸከም የሚችል የሕንድ ሚሳዔል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኒውክሌር አረር ጭምር መሸከም የሚችል የሕንድ ሚሳዔል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፓኪስታን የሚሳዔል ፕሮግራም ረጅም ርቀት የሚጓዙ ተወንጫፊ እና በጦር ግንባሮች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ስልታዊ ተወንጫፊ እንዲሁም የአጭር እና የመካከለኛ ርቀት ሚሳዔሎችን የሚያካትት ነው።

የሕንድ ሚሳዔሎች ፍግሞ የተለያዩ ዓይነቶችን የሚያካትቱ ሲሆን፣ እነዚህም ከ250 አስከ 600 ኪሎ ሜትሮች ርቀት የሚጓዙ፣ ከ1,200 አስከ 8,000 ኪሎ ሜትሮች የሚወነጨፉ እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት ያላቸው ተምዘግዛጊ ሚሳዔሎች አሏት።

የሕንድ የተለያየ ርቀት የሚጓዙ ሚሳዔሎችን መታጠቋ በግዛት ይገባኛል ከምትወዛገባት ጎረቤት ቻይና አንጻር ሊገጥማት የሚችል ስጋትን ከግምት ያስገባ ነው።

ምንም እንኳን ሕንድ በሚሳዔል ትጥቋ ከፓኪስታን የበለጠች ብትሆንም፤ በወሳኙ የኒውክሌር ጦር ማሳሪያ በኩል ግን ሁለቱም አገራት ተመሳሳይ አቅም ያላቸው አውዳሚ ጦር መሳሪያዎችን ታጥቀዋል።

በትቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ተቋም መረጃ መሠረት ሕንድ 172 የኒውክሌር አረሮች ያላት ሲሆን፣ ፓኪስታን ደግሞ 170 አረሮችን ታጥቃለች።

ነገር ግን እነዚህ አገራት ከታጠቋቸው የኒውክሌር አረሮች መካከል ምን ያህሉ ጥቅም ላይ በሚውሉበት ደረጃ ዝግጁ ስለመሆናቸው በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም።

ፓኪስታን የኒውክሌር ጦር ማሰሪያዎችን የምትገነባው ከተቀናቃኟ ሕንድ ጋር በመፊካከር ሲሆን፣ ሕንድ ደግሞ ዋነኛ ትኩረቷ ቻይናን በማድረግ ነው የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎችን የምትገነባው።

በተጨማሪም የሕንድ እና የቻይና ተጎራባች የሆነችው ቻይናም በበኩሏ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዋን አቅም በ22 በመቶ በማሳደግ የነበሯትን 410 የኒውክሌር አረሮች ቁጥር ወደ 500 አሳድጋለች።

አሁን የተቀሰቀሰው የሕንድ እና የፓኪስታን ግጭት የቀረውን ዓለም በተለይ ያሳሰበው ሁለቱም አገራት የኒውክሌር ታጣቂ በመሆናቸው ነው። የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትርም የአገሪቱን ከፍተኛ ወታደራዊ ውሳኔ የሚያሳልፈውን ቡድን ለስብሰባ መጥራታቸው ግጭቱነ እየተባባሰ መሆኑን አምልከቷል።