በቀጠለው ግጭት ውስጥ ፓኪስታን 25 የሕንድ ድሮኖችን መትታ መጣሏን ገለፀች

የፓኪስታን ወታደር በመነጽር ሲመለከት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሐሙስ ዕለት ፓኪስታን 25 የሕንድ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን ስታስታውቅ፣ ሕንድ በበኩሏ ፓኪስታን ወታደራዊ ዒላማዎችን በድሮን እና በሚሳዔል "ማጥቃት እንዳትችል" ማድረጓን ገለፀች።

ሕንድ "የሽብርተኞች መሠረተ ልማቶች" ናቸው ያለቻቸውን ዒላማዎች ረቡዕ ዕለት በአየር ከደበደበች ወዲህ በሁለቱ ኒውክሌር የታጠቁ ጎረቤት አገራት መካከል የሚካሄደው ግጭት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ሕንድ በፓኪስታን የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ጥቃት የፈጸመችው በሕንድ ካሺሚር ግዛት ውስጥ በፓኪስታን መንግሥት ይደገፋሉ ያለቻቸው ታጣቂዎች 26 ሂንዱ የአገር ጎብኝዎችን ከገደሉ በኋላ ነው።

ምንም እንኳ ኢዝላማባድ የቀረበባትን ውንጀላ ውድቅ ያደረገች ቢሆንም፤ ሕንድ ለፈጸመችው ጥቃት ምላሽ እንደምትሰጥ ስትዝት ቆይታለች።

ረቡዕ ዕለት ፓኪስታን አምስት የሕንድ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን ብትገልጽም በቤይጂንግ የሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ ግን "ሐሰተኛ መረጃ" ሲል አጣጥሎታል።

ፓኪስታን በሁለት ትልልቅ ከተሞቿ ካራቺ እና ላሆር እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ ስፍራዎች ከሕንድ የተነሱ 25 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን ገልፃለች።

የፓኪስታን መከላከያ ቃል አቀባይ አሕመድ ሻሪፍ ቻውድሃሪ የአውሮፕላኖቹ ስብርባሪዎች እየተሰበሰቡ ነው ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም የፓኪስታን መከላከያ ዋና መቀመጫ በሚገኝበት ራዋልፒንዲ አንድ ድሮን ተመትቶ መውደቁን ተናግረዋል።

በላሆር አቅራቢያ አንድ ድሮን ወታደራዊ ዒላማ ላይ ጥቃት አድርሶ አራት የፓኪስታን መከላከያ አባላት ላይ ጉዳት ማድረሱን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

"ወደ ፓኪስታን የአየር ክልል የሕንድ ድሮኖች መላካቸውን አላቋረጡም. . . ለዚህ ያለምንም ምክንያት ለሚፈጽሙት ትንኮሳ ውድ ዋጋ ይከፍላሉ" ብለዋል።

የሕንድ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ፓኪስታን ረቡዕ ምሽት እና ሐሙስ ማለዳ በሰሜናዊ እና ምዕራብ ሕንድ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ መሞከሯን እና ሁሉም በሕንድ የአየር መቃወሚያ ሥርዓት "ከጥቅም ውጪ" መደረጋቸውን ተናግረዋል።

በምላሹም የሕንድ አየር ኃይል በተለያዩ ስፍራ የሚገኙ የአየር መከላከያ ራዳሮችን እና መቃወሚያዎችን ማውደሙን ተናግረዋል።

"የሕንድ ምላሽ ፓኪስታን በምትፈጽመው ልክ ተመጣጣኝ ነው" ሲሉ አክለዋል።

መግለጫው አክሎም ፓኪስታን ወደ ሕንድ የምታስወነጭፋቸውን ሚሳዔሎች መጨመሯን ገልጾ፣ በሕንድ ካሺምር ግዛት አምስት ሕጻናትን እና ሦስት ሴቶችን ጨምሮ 16 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

ሕንድ እና ፓኪስታን እአአ በ1947 ከብሪታኒያ ነጻነታቸውን ካገኙ ጊዜ ጀምሮ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ውጥረት የሞላበት ነው።

ሁለቱ አገራት በሦስት የተለያየ ጊዜያት የተዋጉ ሲሆን፣ ሁለቱ በካሽሚር ግዛት ይገባኛል የተነሳ የተካሄዱ ነበሩ።

ሁለቱም አገራት በ1990ዎቹ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መታጣቃቸው ይፋ ሆኗል።

ፓኪስታን ረቡዕ ዕለት ሕንድ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 31 ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ 50 ደግሞ መቁሰላቸውን ገልፃለች።

ሕንድ በበኩሏ 13 ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ 59 ቆስለውብኛል ብላለች።

ሐሙስ ዕለት የሕንድ መንግሥት ለአገሪቱ ፖለቲከኞች በፓኪስታን ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቀቃት ከ100 በላይ አሸባሪዎች ተገድለዋል ሲል መናገሩን የመንግሥት ምንጮች አመልክተዋል።

የፓኪስታን አቪየሽን ባለሥልጣን ከላሆር፣ ከካራቺ እንዲሁም ከአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ከተሞች የሚነሱ በረራዎችን "ለጊዜው" አግዷል።

እገዳው ለምን እንደተደረገ ዝርዝር ማብራሪያ አልተሰጠም።

ምንም እንኳ የፓኪስታን መንግሥት ሕንድ ለፈጸመችው ጥቃት ምላሹን ለመስጠት ቢዝትም የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ካሃዋጃ ሙሐመድ አሲፍ ግን አገራቸው ግጭቱን ለማብረድ ዝግጁ መሆኗን ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።