ሕንድ እና ፓኪስታን በተደጋጋሚ በካሽሚር ላይ የሚጋጩት ለምንድን ነው?

ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሁለቱ ኒውክሌር ታጣቂ ጎረቤት አገራት ሕንድ እና ፓኪስታን ከብሪታኒያ ነጻ ከወጡ በኋላ ወደ 80 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በጠላትነት በዓይነ ቁራኛ ሲጠባበቁ ቆይተዋል።

አገራቱ ፍጥጫ ውስጥ የገቡት ሁለቱም የራሳቸው እንደሆነች በሚገልጿት ካሽሚር ምክንያት ሲሆን፣ ምንም እንኳን ግዛቲቱን ሕንድ እና ፓኪስታን ለሁለት ቢካፈሏትም ሰላም አላገኙም።

ባለፉት ስምንት አስርት ዓመታት ውስጥ አገራቱ በካሽሚር ሰበብነት ሁለት ከባድ ጦርነቶችን እና ግጭቶችን አድርገዋል።

ሕንድ እና ፓኪስታን ለምንድን ነው በግዛት ይገባኛል ምክንያት ተፋጥጠው የሚገኙት? ይህ ሁኔታስ እንዴት ጀመረ?

የሁለቱ አገራት ግጭት መቼ የጀመረ ነው?

ካሽሚር የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚኖሩባት የሂማሊያ ተራራ አካባቢ ስትሆን፤ ባሏት ውብ ሐይቆች፣ አረንጓዴ መስኮች እና ጫፋቸው በበረዶ በተሸፈኑ ተራሮቿ ትታወቃለች።

በአውሮፓውያኑ 1947 ሕንድ እና ፓኪስታን ከብሪታኒያ ነጻነታቸውን ከማግኘታቸው በፊት ጭምር የካሽሚር አካባቢ በጣሙን አወዛጋቢ ነበረ።

የሕንድ እና የፓኪስታንን መለያየት በደነገገው የሕንድ ነጻነት አዋጅ መሠረት ብዙኃኑ ነዋሪዎቿ ሙስሊሞች የሆኑባት ካሽሚር ከሁለቱ አገራት ወደ አንዳቸው የመቀላለቀል መብት ተሰጥቷት ነበር።

የአካባቢው አስተዳዳሪ የነበረው ሃሪ ሲንግ በመጀመሪያ ላይ ካሽሚር እራሷን የቻለች ነጻ አገር እንድትሆን ፍልጎት የነበረው ቢሆንም፤ ከፓኪስታን ጎሳዎች የሚፈጸምባቸውን ወረራ ለመከላከል ለምትሰጣቸው ድጋፍ የካሽሚር መሪ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 1947 ሕንድ ጋር ለመቀላለቀል ወሰኑ።

ከዚያም በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ተቀስቅሶ ሕንድ የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ እንዲገባ ጠየቀች። የመንግሥታቱ ድርጅትም ካሽሚር ከሕንድ ወይም ከፓኪስታን ጋር መቀላቀል ትፈልግ እንደሆነ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ሃሳብ አቀረበ።

ነገር ግን ሕዝብ ውሳኔው ከመካሄዱ በፊት ሁለቱ አገራት ካሽሚርን ከሠራዊቶቻቸው እንቅስቃሴ ነጻ ለማድረግ ከስምምነት መድረስ ሳይችሉ ቀሩ።

በሐምሌ 1949 ሕንድ እና ፓኪስታን በተባበሩት መንግሥታት በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ መሠረት የተኩስ አቁም የሚያደርጉበትን ስምምነት በመፈረማቸው ካሽሚር ለሁለት ተከፈለች።

በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል በካሽሚር ምክንያት ሁለተኛው ዙር ጦርነት በአውሮፓውያኑ 1965 ተካሄደ። ከዚያም በ1999 ሕንድ ለአጭር ጊዜ የቆየ ነገር ግን መራራ ግጭት በፓኪስታን ከሚደገፉ የካሽሚር ኃይሎች ጋር አደረገች።

በዚያ ወቅት ሕንድ እና ፓኪስታን ኒውክሌር የታጠቁ አገራት መሆናቸው ይፋ ሆኖ ነበር። በአሁኑ ጊዜም አገራቱ የካሽሚር ግዛትን ሙሉ ለሙሉ የራሳቸው እንደሆነ ቢገልጹም የሚቆጣጠሩት ግን ከፊሉን የግዛቲቱን ክፍል ነው።

የካሽሚር የተራሮች ባቡር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካሽሚር ባሏት አረንጓዴ መስኮች እና ታራሮች ምክንያት አንዳንዶች የሕንድ ስዊትዘርላንድ ይሏታል

የሕንድ ካሽሚር ለምን አለመረጋጋት ይበረታል?

በካሽሚር ውስጥ ግዛቲቱ ከየትኛው አገር ጋር መሆን እንዳለባት በተመለከተ ያለው አስተያየት የተከፋፈለ እና የተካረረ ነው። በርካቶች በሕንድ ስር ከመተዳደር ይቅል ነጻ አገር መሆንን አሊያም ከፖኪስታን ጋር መዋሃድን ይመርጣሉ።

ለዚህም ሃይማኖት አንድ ምክንያት ሲሆን፣ በሕንድ ይዞታ ስር ያለው ጃሙ እና ካሽሚር ውስጥ ከሚገኘው ሕዝብ ከ60 በመቶው በላይ ሙስሊም ሲሆን፣ ይህም ሙስሊም ብዙኃን የሆነበት ብቸኛው የሕንድ ክፍል ያደርገዋል።

ከ1989 ጀምሮ የሕንድን አስተዳደር በመቃወም በአካባቢው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ የትጥቅ አመጽ ተካሂዷል።

ሕንድ በካሽሚር የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎችን በመርዳት ፓኪስታንን ብትከስም ጎረቤት ፓኪስታን ግን ይህንን ታስተባብላለች።

በ2019 የሕንድ መንግሥት በሚያስተዳድረው የካሽሚር ክልል ውስጥ ከባድ ደኅንነት የማስከበር እርምጃ ወስዶ ግዛቱ የነበረውን ከፊል የራስ ገዝነት ሥልጣን እንዲገፈፍ አደረገ።

ይህ ሕንድ ለካሽሚር ሰጥታው የነበረው ልዩ መብት ከተነሳ በኋላ ለበርካታ ዓመታት በአካባቢው የሚካሄድ የትጥቅ እንቅስቃሴ ጋብ ብሎ፤ ለጉብኝት የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ቆይቷል።

ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በካሽሚር ግጭት ውስጥ ሃይማኖት ጉልህ ሚና አለው

ከቀደሙት የታጣቂዎች ጥቃቶች በኋላ ምን ተከሰተ?

በአውሮፓውያኑ 2016 ኡሪ በተባለው የካሽሚር አካባቢ 19 የሕንድ ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ ሕንድ ሁለቱን አገራት በግዛቲቱ ውስጥ የሚለየውን ድንበር ተከትሎ የታጣቂዎች ይዞታዎች ናቸው በተባሉ ዒላማዎች ላይ "ለይቶ የመምታት" ጥቃት ማካሄድ ጀመረች።

በ2019 ደግሞ የፑልዋማው የቦምብ ጥቃት በሚባለው ጥቃት ከ40 በላይ የሕንድ ሚሊሻ አባላት መገደላቸው ተከትሎ ከ1971 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕንድ ወደ ፓኪስታን ግዛት ዘልቃ በመግባት ጥቃት ፈጸመች።

ይህም ፓኪስታን የአጸፋ እርምጃ እንድትወስድ እና የጦር አውሮፕላኖቻቸው የአየር ላይ ውጊያ እስከማድረግ አድርሷቸው ነበር።

ለዓመታት በሁለቱ አገራት መካከል አንጻራዊ ሰላም ከሰፈነ በኋላ በዚህ ዓመት ሚያዝያ ወር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ታጣቂዎች ሕንድ በምታስተዳድረው ካሽሚር ውስጥ በአንዲት የመዝናኛ ከተማ በፈጸሙት ጥቃት 26 ቱሪስቶች ተገደሉ።

ይህም በሃያ ዓመታት ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ እጅግ አደገኛው ጥቃት ተብሏል።

ለዚህም አጸፋ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሕንድ በፓኪስታን ውስጥ እና በፓኪስታን በሚተዳደረው ካሽሚር ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን በሚሳኤል መታች። በዚህም ሳቢያ በአገራቱ መካከል ያለው ፍጥጫ ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮ ፍጥጫው እንዲረግብ ጥሪ እየቀረበ ነው።

በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ካሽሚር በዓለም ላይ ካሉ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።

የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ እነ የሕንዱ አቻቸው ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ እነ የሕንዱ አቻቸው ናሬንድራ ሞዲ

የሰላም ተስፋ አለ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በ2003 ሕንድ እና ፓኪስታን ተኩስ አቁም ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2014 የአሁኑ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ሥልጣን የመጡት በፓኪስታን ላይ ጠንከር ያለ አቋም እንደሚይዙ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ የሰላም ንግግር ለመጀመር ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።

በዚያ ወቅት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ናዋዝ ሸሪፍ ዴልሂ ውስጥ በተካሄደው ሞዲ ሥልጣን ለመረከብ በፈጸሙት የቃለ መሐላ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ነበር።

ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ሕንድ በሰሜናዊ ግዛቷ ፑንጃብ ውስጥ በሚገኘው የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ ለተፈጸመባት ጥቃት ከፓኪስታን የሚነሱ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጋለች።

በዚህም የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ውስጥ በአውሮፓውያኑ 2017 ይካሄደው በነበረው ቀጣናዊ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የነበራቸውን ዕቅድ ሰርዘዋል።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ በጎረቤታሞቹ ሕንድ እና ፓኪስታን መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነት የሚያስተካክል ምንም ዓይነት እርምጃ ከሁለቱም ወገን አልተወሰደም።

አሁን ደግሞ ሕንድ በምትቆጣጠረው ካሽሚር ውስጥ ከሁለት ሳምንት በፊት በቱሪስቶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ማክሰኞ ሌሊት በፓኪስታን ውስጥ እና በምትቆጣጠረው ካሽሚር ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን ፈጽማለች።

የፓኪስታን ጦር ሠራዊት በጥቃቱ ወቅት አምስት የሕንድ የጦር አውሮፕላኖችን እና አንድ ድሮን መትቶ መጣሉን ቢገልጽም፣ ከሕንድ በኩል ግን የተባለ ነገር የለም።

ፓኪስታን በጥቃቱ ቢያንስ 26 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 46 ደግሞ ቆስለዋል ስትል፤ ሕንድ ደግሞ በምትቆጣጠረው ካሽሚር ላይ ፓኪስታን በፈጸመችው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸውን እና 43 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቃለች።