የጄኔራል አል ቡርሐን መቀመጫ በሆነችው ፖርት ሱዳን ለሦስት ተከታታይ ቀናት የድሮን ጥቃት ተፈጸመ

ፖርት ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሱዳን ወታደራዊ ኃይል የሚመራው መንግሥት መቀመጫ በሆነችው የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳን ለሦስተኛ ተከታታይ ቀን የድሮን ጥቃት ተፈጸመባት።

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አይሎ አብዛኛውን ካርቱም ሲቆጣጠር በጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው የአገሪቱ ጦር ኃይል መቀመጫውን ወደ ፖርት ሱዳን አዙሮ ቆይቷል።

ከሳምንታት በፊት የአገሪቱ ጦር በፈጥኖ ደራሽ ኃይል ላይ የበላይነትን በማግኘት በርካታ የካርሩም ክፍሎችን መቆጣጠር ከቻለ በኋላ ነው ተከታታይ የድሮን ጥቃቶች በፖርት ሱዳን ላይ የተፈጸመው።

ፖርት ሱዳን የወታደራዊ ኃይሉ መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር በጦርነቱ ሳቢያ በከባድ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ለሚገኘው የሱዳን ሕዝብ የሚደርስ እርዳታ የሚተላለፍባት የወደብ ከተማ ናት።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት በከተማዋ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ የሱዳን ጦር ኃይል ተቀናቃኙን የፈጥኖ ደራሽ ጦር የከሰሰ ሲሆን፣ ቡድኑ ግን እስካሁን ጥቃቱን ስለመፈጸሙ ኃላፊነቱን አልወሰደም።

በፖርት ሱዳን የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት በተመለከተ ዋናውን የመርከቦች መግቢያ ወደብ እና ከአየር ማረፊያውን ጨምሮ በከተማዋ ካሉ ከበርካታ ቦታዎች ከፍተኛ ጥቁር ጭስ ሲወጣ መመልከታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

በከተማዋ በተደጋጋሚ በተፈጸሙት የድሮን ጥቃቶች ምክንያት ጉዞዎች መደናቀፋቸውም ተንገሯል።

የድሮን ጥቃቶቹ ከወደቡ እና ከአየር ማረፊያው በተጨማሪ የኃይል ማመንጫ እና ሆቴልን ዒላማ አድርገዋል።

ፖርት ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቀደም ሲል በድሮን የሚፈጸሙ ጥቃቶች በዋናነት ዒላማ የሚያደርጉት የነዳጅ ማከማቻን እና ወታደራዊ ጦር ሠፈሮችን ነበር። አሁን ግን የተለያዩ ተቋማት በድሮን ጥቃት እየተመቱ ይገኛሉ።

ጥቃቱ መፈጸም እስከ ጀመረበት ከሦስት ቀናት በፊት ድረስ በፖርት ሱዳን ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃይ ሱዳናውያን ነበሩ። ከሁለት ዓመት በላይ የዘለቀው እስር በርስ ጦርነት እና አሁን እየተባባሰ የመጣው ጥቃት ሕይወታቸውን የበለጠ ያመሳቅለዋል።

ሁለት ዓመት ባለፈው የጦር ሠራዊቱ እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሞቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ደግሞ ከመኖሪያው ተፈናቅሏል።

በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ላይ ወተዳራዊ ድሎችን እያገኘ የመጣው የሱዳን ጦር ሠራዊት ባለፈው ወር አብዛኛውን የዋና ከተማዋ ካርቱም ክፍሎች በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱን የገለጸ ቢሆንም ጦርነቱ ቀጥሏል።

በጄነራል አል ቡርሐን የሚመራው የአገሪቱ ጦር ኃይል በካርቱም የሚገኘውን ቤተ መንግሥት መቆጣጠሩን ተከትሎ መንግሥት መመሥረቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታት ቤተ መንግሥቱ በጄኔራል ዳጋሎ በሚመሩት ፈጽኖ ደራሽ ኃይሎች ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት ደርሶበታል።

ከካርቱም የተገፉት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በበኩላቸው ጄነራል አል ቡርሐን የሱዳን መንግሥትን ማቋቋማቸውን ተከትሎ ጄኔራል ዳጋሎም በበኩላቸው ሌላ ትይዩ መንግሥት መመሥረታቸውን አስታውቀዋል።

ይህም ሱዳንን ዳግም ለሌላ ዙር ክፍፍል ሊዳርጋት ይችላል ተብሎ እንዲሰጋ አድርጓል።

ከሁለት ዓመታት በላይ በቆየው ጦርነት በተለያዩ የአገሪቱ ከፍሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ጭፍጨፋዎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።

በተጨማሪም በጦርነቱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ ባለመቻሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ለችግር እና ለረሃብ መጋላጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።