የሱዳን ጦር ካርቱምን ከተቆጣጠረ በኋላ ንጹኃን ዜጎች መገደላቸውን ተመድ ገለጸ

ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ቱርክ የሱዳን ጦር ከሕግ ውጭ ግድያ መፈጸሙን የሚጠቁሙ "አሳማኝ ሪፖርቶች" መኖራቸውን ተናገሩ።

በዚህም በጣም ማዘናቸውን ገልጸው፣ ንጹኃን ዜጎች ላይ ግድያው የተፈጸመው የሱዳን ጦር ባለፈው ሳምንት መዲናዋን ከተቆጣጠረ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል።

"በርካታ ንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች እንደነበሩ የሚጠቁሙ ጠንካራ ሪፖርቶች አሉ።

በካርቱም የተለያዩ አካባቢዎች ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር አብራችኋል በሚል ግድያዎቹ ተፈጽመዋል" ብለዋል ኮሚሽነሩ።

በካርቱም ውስጥና ከካርቱም ውጭም በታጣቂዎች ንጹኃን ሲገደሉ ያሳያሉ የተባሉ ብዙ ቪድዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወሩ ነበር።

ቢቢሲ ቪድዮዎቹን በገለልተኛ ወገን ማጣራት ባይችልም የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ቪድዮዎቹ ተዓማኒነት አላቸው ብሏል።

የሱዳን ጦር ስለቀረበበት ክስ ምላሽ እስከሚሰጥ ቢቢሲ እየጠበቀ ነው።

"የታጠቁ ወንዶች ንጹኃንን በጭካኔ በአደባባይ ሲገድሉ የሚያሳዩ ብዙ አሰቃቂ ቪድዮዎች አሉ" ብለዋል ኮሚሽነሩ።

አንዳንዶቹ ቪድዮዎች ላይ ጥቃት አድራሾቹ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ደጋፊዎችን እየቀጡ እንደሆነ ይናገራሉ።

ላለፉት ሁለት ዓመታት የሱዳን ጦርና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጦርነት ውስጥ ናቸው።

የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በዓለም የከፋውን ሰብአዊ ቀውስ መፍጠሩ ተገልጿል።

"የሱዳን ጦር ኮማንደሮች ይሄንን የዘፈቀደ ግድያ በአፋጣኝ እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ። በግላቸው ጥቃት የሚሰነዝሩም ይሁን ወታደራዊ ትዕዛዝ የተሰጣቸው በዓለም አቀፍ ሕግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው" ሲሉ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

የሱዳን ጦርና አጋሮቹ በአርኤስኤፍ ሥር የነበሩትን ሳኔር፣ ገዚራ እና የሰሜን ኮርዶፋን የተወሰኑ አካባቢዎችን መልሰው ከተቆጣጠሩ በኋላ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ተከስሰዋል።

ከሁለት ወር በፊት ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ኮሚቴ አዋቅረው በገዚራ መዲና ዋድ መዳኒ የተፈጸሙ ጥቃቶች እንዲመረመሩ ቢያደርጉም ግኝቱ ለሕዝብ እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

በዋድ መዳኒ ደርሷል የተባለውን ሰብአዊ መብት ጥሰት ተከትሎ አሜሪካ በአል-ቡርሃን ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎ መሪ ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎም በጦር ወንጀሎችና በጭካኔ ድርጊት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

የአርኤስኤፍ ኃይል ሰዎችን በማሰር፣ በማሰቃየት፣ የሱዳንን ጦር ደግፋችኋል በሚል በመረሸን እና በምዕራብ ዳርፉር ጎሳ ተኮር ግድያ በመፈጸም ተከሷል።

ጦሩ ከዚህ ቀደም ግድያ የተፈጸመውና የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰው "በተወሰኑ ወታደሮች" ነው ሲል አውግዞ ነበር።

መዲናዋ ካርቱም ለሁለት ዓመት ገደማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሥር የቆየች ሲሆን በቅርቡ በሱዳን ጦር ይዞታ ሥር ገብታለች።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ውጊያውን ለመቀጠል የዛተ ሲሆን፣ ጦርነቱ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በአዳዲስ ግንባሮች ሊቀጥል እንደሚችል ተሰግቷል።