ሊቢያ የሕዝብ አወቃቀሯን "በአፍሪካውያን" ለመቀየር እየሞከሩ ነው ያለቻቸውን የረድዔት ድርጅቶች አባረረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሊቢያ ያሉ የረድዔት ድርጅቶች አፍሪካውያን ስደተኞች እንዲቆዩ በማበረታት የአገሪቱን ስነ ህዝብ አወቃቀር ለመቀየር እያሴሩ ነው ሲሉ ባለስልጣናቱ ከሰሱ።
እነዚህ የአገሪቱን የስነ ህዝብ አወቃቀር (ዲሞግራፊ) ለመቀየር አሲረዋል የተባሉ ድርጅቶችም ቢሯቸው እንዲዘጋ በያዝነው ሳምንት ሐሙስ ትዕዛዝ ተላልፏል።
ባለስልጣናቱ፤ድንበር የለሽ የሐኪሞች ማህበር፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) እና የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤትን ጨምሮ አስር ድርጅቶችን ለይተዋል።
"የአፍሪካ ተወላጅ የሆኑ ስደተኞችን በአገራችን የማስፈር እቅድ የጥላቻ ተግባርን የሚወክል ነው። አላማውም የአገሪቱን የስነ ህዝብ አወቃቀር ለመቀየር እና የሊቢያን ማህበረሰብ አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ሲሉ የሃገር ውስጥ ደህንነት ባለስልጣን ቃል አቀባይ ሳሌም ጌይት ሐሙስ ዕለት ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የቱኒዝያው መሪ በዋነኝነት አረብ እና ሙስሊም የሆነችውን የሰሜን አፍሪካዋን አገራቸውን የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ለመለወጥ ሴራ ተጎንጉኗል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል። ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካውያን ወደ ቱኒዝያ የሚሰደዱት የዚህ ሴራ አካል ነው ማለታቸውን ተከትሎ በጥቁር ጠልነት እና በዘረኝነት ተወግዘው ነበር።
ሁለቱም አገራት በሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ ላይ የሚገኙ ሲሆን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለሚገቡ አፍሪካውያን ስደተኞች ቁልፍ መሸጋገሪያዎች ናቸው።
የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ በአውሮፓውያኑ 2011 መውደቅ ተከትሎ አገሪቱ ስርዓተ አልበኝነት ሰፍኖባታል። አገሪቱ ለሁለት ተከፍላ በተቀናቃኝ አስተዳደሮች እየተመራች ትገኛለች።
የታጠቁ ሚሊሻዎች በርካታ የአገሪቱን ክፍሎች የሚመሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እንዲሁም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መናኸሪያ አድርጓታል።
የስደተኞች መቆያ ማዕከላት በሚሊሻዎች ይመራሉ። እነዚህ ሚሊሻዎች ስደተኞችን በማስራብ እንዲሁም እሰከ ሞት በሚያደርሱ ክፉኛ በመደብደብ ይወነጀላሉ።
የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎችም በአደጋ ውስጥ ሆነው በጀልባዎች እየተጓዙ ያሉ ስደተኞችን ከመታደግ ይልቅ በቪዲዮዎች ይቀርጿቸዋል። የሊቢያ ባለስልጣናት በነዚህ ክሶች ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።
የረድዔት ድርጅቶቹን የማባረር ትዕዛዝ ከሰሞኑ የተላለፈው መቀመጫውን በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ ያደርገው እና አለም አቀፍ እውቅና በተሰጠው መንግሥት ነው።
"ሊቢያውያን አፍሪካውያን አይደሉም?"
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ማህበር (ኤምኤስኤፍ) ከመጋቢት ጀምሮ የሊቢያ ባለስልጣናት የትንኮሳ ዘመቻ ካደረሱባቸው በኋላ ከሳምንት በፊት ስራውን ማቆሙን ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) በበኩሉ የሚረዳቸው ስደተኞች በችግር ላይ ያሉ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል። በትሪፖሊ መንግሥት ፈቃድ እንደሚሰራም ገልጿል።
"ከሊቢያ ባለስልጣናት ጋር በመገናኘት ሁኔታውን በግልጽ ለመረዳት እየሞከርን ነው። ዩኤንኤችሲአር በሊቢያ ከ30 ዓመታት በላይ ሲሰራ ቆይቷል። በነዚህም አመታት ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰብዓዊ እርዳታዎችን መለገስ ጨምሮ ተጋላጭ የሊቢያ ማህበረሰቦችንም እየደገፈ ይገኛል" ሲሉ ቃል አቀባዪ ዊልያም ስፒንድለር ይናገራሉ።
የሊቢያ ባለስልጣናት አስሩ የረድዔት ድርጅቶች ላይ ከሰነዘሩት ውንጀላ አንዱ "ለህገ ወጥ ስደተኞች ምግብ፣ አልባሳት እና መድኃኒት በመስጠት ይደግፋሉ" የሚል ነው።
ይህም እንደ ባለስልጣኑ "ስደተኞቹ ሊቢያን እንደ መሸጋገሪያ ሳይሆን የመጨረሻ መዳረሻቸው አገር እንዲቆጥሯት አበረታቷቸዋል" የሚል ነው።
ነገር ግን ባለስልጣኑ እንደሚሉት ሳይሆን በርካታ ስደተኞች በሊቢያ መቆየት እንደማይፈልጉ ይናገራሉ።
ለዓመታት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከሰሃራ በታች የሚመጡ አፍሪካውያን ስደተኞች በሊቢያ መገደል፣ ባርነት ወይም በተደጋጋሚ መደፈርን ጨምሮ የከፋ የመብት ረገጣ እና ጥሰቶች ይፈጸሙባቸዋል።
"አጸያፊ ጥቁር እያለ ይጠራኝ ነበር። ደፈረኝ እናም ሴቶች የተፈጠሩት ለዚህ ነው አለኝ" ስትል ቤቱን እንድታጸዳ የቀጠራት ግለሰብ ያደረሰባትን አንዲት በሊቢያ የነበረች ሱዳናዊት ስደተኛ ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።
"ህጻናቱ ራሱ ለኛ ክፉ ናቸው። እንደ አውሬ እና ጠንቋይ አድርገው ይቆጥሩናል። ጥቁር እና አፍሪካዊ ብለው ይሰድቡናል። እነሱ ራሳቸው አፍሪካውያን አይደሉምን? " ይህቺ ስደተኛ ትጠይቃለች።












