በሊቢያ የ28 ስደተኞች የጅምላ መቃብር መገኘቱን ባለስልጣናቱ አስታወቁ

የሊቢያዋ ከተማ ኩፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በደቡብ ምስራቅ ሊቢያ በረሃ ቢያንስ የ28 ስደተኞች አስከሬን የያዘ የጅምላ መቃብር መገኘቱን የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

መቃብሩ የተገኘበት ስፍራ ኩፍራ በተሰኘች ከተማ አቅራቢያ ነው።

ከቀናት በፊት 19 አስከሬኖችን የያዘ ሌላ የጅምላ መቃብር በዚህችው ከተማ በሚገኝ እርሻ ላይ ተገኝቷል።

ባለስልጣናቱ የህገወጥ ሰዎች ዝውውር ይፈጸምበታል የተባለ ስፍራን ከተቆጣጠሩ በኋላ የጅምላ መቃብሩ ሊገኝ እንደቻለ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት በፌስቡኩ አስፍሯል።

በዚያችው ስፍራ ላይ በእስር ላይ የሚገኙ እና ስቃይ የደረሰባቸው 76 ስደተኞችን ባለስልጣናቱ መታደጋቸው ተገልጿል።

አንድ ሊቢያዊ እና ሁለት የውጭ ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጽህፈት ቤቱ አክሏል።

"ይህ ወሮበላ ቡድን በህገወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን ሆን ብለው ነጻነታቸውን በመንፈግ፣ ስቃይ እና ጭካኔ ፈጽመውባቸዋል፤ እንዲሁም ለውርደት እና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ዳርገዋቸዋል። " ብሏል መግለጫው።

በበይነ መረብ ላይ የተጋሩ ምስሎች ፖሊስ እና በጎ ፈቃደኞች በአሸዋማ ስፍራው ላይ ቁፋሮ ሲያካሂዱ እንዲሁም አስከሬኖችን በጥቁር ፕላስቲክ ላይ ተዘርግተው አሳይተዋል።

ከሊቢያ መዲና ትሪፖሊ በ1 ሺህ 700 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኩፍራ እየተካሄደ ያለው ቁፋሮ እና ፍለጋ ቀጥሏል።

በጅምላ መቃብሩ የተገኙት አስከሬኖች ለምርመራ መወሰዳቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል። በተጨማሪም ባለስልጣናቱ የተረፉ ስደተኞችን ምስክርነት እየሰሙ ይገኛሉ።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ቢያንስ የ65 ስደተኞች አስከሬኖችን የያዘ የጅምላ መቃበር መገኘቱን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ማስታወቁ ይታወሳል።

ተቋሙ ይህንን ክስተት "በጣም አስደንጋጭ" ሲል በወቅቱ ገልጾት ነበር።

ስደተኞቹ የሞቱበትን ሁኔታ እና የየት አገር ዜጎች ስለመሆናቸው አስካሁን የታወቀ ነገር እንደሌለ ድርጅቱ ገልጾ፣ ነገር ግን በሊቢያ በረሃ በኩል ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር በድብቅ ሲወሰዱ ሳይሞቱ እንደማይቀሩ ይታመናል።

ሊቢያ በአደገኛው የሜዲትራኒያን ባሕር በኩል በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚፈልጉ ስደተኞች ከሚጠቀሙባቸው መስመሮች መካከል ዋነኛዋ ናት።

በተለይም የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊ በአውሮፓውያኑ 2011 ከስልጣን መገርሰስ ተከትሎ በርካቶች ለሞት የሚዳረጉበትን አደገኛውን በረሃ በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመሸገጋገር በሚደረገው ትግል ዋነኛ ማዕከል ሆናለች።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2024 ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሜዲትራንያን ባህርን ሲያቋርጡ የጠፉ ወይም የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሺህ 200 መብለጡን አስታውቋል።