የካቶሊክ ጳጳስ ቀይ ጫማ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? እና ሌሎች የማይደፈሩ ጥያቄዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ህልፈትን ተከትሎ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዲስ መሪ ለመምረጥ ካርዲናሎች በምሥጢር ተሰብስበዋል።
አዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከየትኛው የዓለም ክፍል እንደሚመረጡ ሁሉም ሰው በትኩረት እየተጠባበቀ ነው። አዲስ የሚመረጡት ጳጳስ ከቀደሙት የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች በተለየ ፖፕ ፍራንሲስ ያሳዩትን የአቃፊነት እንዲሁም ቀላል የአኗኗር ዘይቤን ይቀጥሉ ይሆን የሚል ጥቄያም እየተነሳ ነው።
ጳጳሱ በዓለም ዙሪያ ያሉ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ የካቶሊክ ዕምነት ተከታዮች መንፈሳዊ አባት ሲሆኑ፣ ካቶሊኮች ጳጳሱን ከቀደምት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ወራሽ አድርገው ይመለከቷቸዋል።
በክርስትና እምነት ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እና ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ከኢየሱስ 12 ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ እንደሆነ ይታመናል።
ይህ ትስስርም ጳጳሱን በቀጥታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማገናኘት የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መሪነት ዋነኛ ምንጭ ያደርጋቸዋል።
ጳጰሱ በመደበኛነት ገናን እና ትንሳኤን ጨምሮ በቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በሚካሄዱ የቤተ ክርስቲያኗ ሁሉንም ዋነኛ የበዓል ሥነ ሥርዓቶችን ይመራሉ።
ጰጳሱ ቤታቸውን የሚከታተሉ፣ ምግብ የሚያበስሉ እና የጽዳት ሥራን የሚያከናውኑ ትንሽ ቁጥር ያላቸው መነኮሳት እንዲሁም አልባሳቶቻቸውን የሚቆጣጠሩ አልባሽ አላቸው።
በተጨማሪም ንግግራቸውን የሚያዘጋጁ የንግግር ፀሐፊዎች ቡድን አላቸው።
የጳጳሱ አንደኛው ተግባር ቢያንስ በየአምስት ዓመቱ አንደ ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎችን ማግኘት ነው። በዚህም መሠረት በዓመት አንድ ሺህዎችን የሚያገኙ ሲሆን ይህም በሳምንት ውስጥ 20 ገደማ የሚሆኑ ቢሾፖችን ያነጋግራሉ እንደ ማለት ነው።
በዚህ ዘመን ደግሞ ጳጳሱ በውጭ አገራት የሚያደርጓቸው ጉብኝቶች ከኃላፊነቶቻቸው መካከል አንዱ ነው።
ጳጳሳት ያገባሉ?
በጥንት ዘመን ያገቡ ጰጳሳት እንደነበሩ ይነገራል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው ጳጳስ እንደሆነ የሚታመነው ቅዱስ ጴጥሮስም ሚስት ነበረው። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ያገባ ሰው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ሆኖ የመመረጥ ዕድል አይኖረውም።
በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የቀደምት ጳጳሳት ታሪክ ዋነኛ የምርምር ክርክር ርዕስ ነው። ምን ያህሉ ጳጳሳት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁሉ ጳጳስ ከመሆናቸው በፊት ያገቡ እንደነበሩ ግልጽ አይደለም።
በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሕግ ማንኛውም የተጠመቀ ወንድ ለጵጵስና ሥልጣን ሊቀርብ ይችላል፤ ነገር ግን በ1379 ከተሰየሙት ከአቡነ ኡርባን ስድስተኛ ጀምሮ ጳጳስ ለመሆን በካርዲናልነት ደረጃ ማለፍ አለባቸው።
አሁን ጳጳሱን ለመምረጥ የተሰበሰቡት ካርዲናሎች በሙሉ ያላገቡ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ የካቶሊክ ቀሳውስት ቅስናን ሲቀበሉ ያላገቡ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Vatican Media
ጳጳሱ ደሞዝ ይከፈላቸዋል?
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ከቤተ ክርስቲያኗ የሚያገኙትን ደሞዝ በሙሉ ለበጎ አድራጎት ሲሰጡ እንደነበር ይነገራል።
በአውሮፓውያኑ 2021 የቫቲካን ቃል አቀባይ የጳጳሱን ደሞዝ በተመለከተ ሲነገር የነበረውን ግምት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ "ጳጳሱ በፍጹም ደሞዝ ተቀብለው አያውቁም'' በማለት አረጋግጠዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ ከኃላፊነታቸው አንጻር የሚኖሩ አንዳንድ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ሲሉ ለጳጳስ ተብሎ ከተዘጋጀው ቅንጡ መኖሪያ ቤት ይልቅ በእንግዳ ማረፊያ ውስጥ መኖርን መርጠዋል።
ከእሳቸው በፊት የነበሩት እና ባልተለመደ ሁኔታ በአውሮፓውያኑ 2013 በጤና ችግር ምክንያት መንበራቸውን የለቀቁት ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ ጡረታ ይቀበሉ እንደነበር የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አንድ ጳጳስ ለምን ያህል ጊዜ ያገለግላሉ?
እንደ ፖፕ ፍራንሲስ ሁሉ አብዛኞቹ ጳጳሳት እስከ ህልፈተ ሕይወታቸው ዕለት ድረስ በመንበራቸው ላይ ይቆያሉ።
በ1415 ጵጵስናቸውን ከለቀቁት ጆርጅ 12ኛ በኋላ መንበራቸውን በፍላጎታቸው በመልቀቅ ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ ከክፍለ ዘመናት በኋላ የመጀመሪያው ናቸው።
ነገር ግን የታሪክ አጥኚዎች ስንት ጳጳሳት ከመንበራቸው በፍላጎታቸው ለቀቁ በሚለው ላይ ስምምነት የላቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Mimmo Chianura-Pool
ጳጳስ መሆን የሚችለው ማነው?
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የዕምነት ሥርዓትን በሚመራው ሕግ መሠረት የሚከተሉት ሰዎች የቤተ ክርስቲያኗ ጳጳስ ሆነው ሊመረጡ እንደሚችሉ ካቶሊክ ኦንላይን ዘግቧል፡
"ማንኛውም የተጠመቀ እና ማመዛዘን የሚችል ካቶሊክ፣
"ምንም እንኳን ካርዲናል ያልሆነ የእምነቱ አባል ጵጵስናን ከተቀበለ ከ500 ዓመታት በላይ ቢሆንም፣ ቀደምት ታሪካዊ ልምዶች ግን ሌሎች ቀሳውስት ወይም ተራ ሰው ሊመረጥ ይችላል፣
"የተመረጠው ዕጩ የቅስና ማዕረግ ከሌለው፣ ጵጵስናውን ከመረከቡ በፊት የቅስና ማዕረግ ወዲያውኑ እንዲያገኝ ይደረጋል።"
በርካቶች እንደሚሉት የጵጵስናውን መንበር ለመረከብ መልካም ባሕሪይ በይፋ ያልተነገረ ወሳኝ መመዘኛ ነው።
በጳጳስ ምርጫ ውስጥ ድምጽ መስጠት የሚችሉት 'ካርዲናል' የሚል ማዕረግ ያላቸው ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በታች የሆነ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው። በአዲስ ጳጳስ ምርጫ ላይ መሳተፍ የአንድ አባት ሥራ እና መንፈሳዊ ኃላፊነት ነው።
የጳጳስ ምርጫ የሚካሄድበት ጉባኤ (ኮንክሌቭ) ለክፍለ ዘመናት ምሥጢራዊነቱ እና ከሌሎች ተጽእኖ ተጠብቆ እንዲካሄድ በተቀመጠለት ጥብቅ መመሪያ በመከተል የሚካሄድ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጳጳሱ ለምንድን ነው ቀይ ጫማ የሚያደርጉት?
በካቶሊክ ዕምነት ቀይ ቀለም ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ፍቅርን እና መስዋዕትነትን ይወክላል። ይህም በአዲስ ኪዳን ላይ እንደተጠቀሰው የኢየሱስ ክርስቶስን ስቃይ፣ መያዝ፣ ለፍርድ መቅረብን እና መሰቀልን ያመለክታል።
ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ እና ከእሳቸው በፊት የነበሩ በርካታ ጳጳሳት ቀይ ጫማ የማድረግን ባህል ሲከተሉ ቆይተዋል።
ነገር ግን ታዛቢዎች እንደሚሉት ፖፕ ፍራንሲስ ትኩረት ላለመሳብ እና ከቅንጦትን ለመራቅ ሲሉ ጥቁር ጫማ ነበር የሚጫሙት።
ፖፕ ጆን ፖል ዳግማዊም አንዳንድ ጊዜ የተለየ ቀለም ያለው ጫማ ያደርጉ እንደነበረ ይነገራል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለምን ጳጳስ አስፈለጋት?
ይህንን ለመመለስ ከክርስትና ቅዱስ መጽሐፍ አንድ ጥቅስ እንውሰድ።
ኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ የሆነውን የስምዖንን ስም ወደ ጴጥሮስ ቀየረው፤ ይህም 'አለት' ማለት ነው። ማቲዮስ 16፡18 ላይ "እኔም እልሃለው አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚችም አለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔንም እሰራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም" ይሏል።
ቀደም ሲል እንደገለጽነው ካቶሊኮች የቤተ ክርስቲያኗ ጳጳስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ የሆነው የቅዱስ ጴጥሮስ ወራሾች ናቸው ብለው ያምናሉ።
ስለዚህም ጳጳሱ እንደ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወሳኝ መሠረቶች መካከል አንዱ እና ህያው መሪ ተደርገው ይታያሉ።
ጳጳሱ ካቶሊኮች በምን ላይ ማተኮር እንዳለባቸው እና ትንሽም ይሁን ትልቅ በሕይወታቸው ውስጥ የሚገጥሟቸውን ፈታናዎችን በተመለከተ ምክር ይሰጣሉ። በተጨማሪም አዳዲስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ማኅበረሰባቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸው ድጋፍ ይሰጣሉ።
ምዕመናንም ከዓለም ዙሪያ ወደ ቫቲካን በመጓዝ ጳጳሱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚያካሂዱት የጸሎት እና የቡራኬ ሥነ ሥርኣት ላይ ይታደማሉ።
በተጨማሪም ጳጳሱ በሌሎች አገራት ውስጥ የሚያደርጉት ጉብኝት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብን ይጋብዛል፤ ይህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያም ምን ያህል ተሰሚ እንደሆነች ማሳያ ነው።












