ዩክሬን ፕሬዝዳንት ፑቲንን በድሮን ጥቃት ለመግደል ሞክራለች ስትል ሩሲያ ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ ቤተ መንግሥት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ልትገድላቸው ሞክራለች ስትል ሩሲያ ከሰሰች።
ማክሰኞ ምሽት የፕሬዝዳንት ፑቲን ቤተመንግሥትን ኢላማ ያደረጉ ሁለት ድሮኖችን ጥያለሁ ያለችው ሩሲያ፣ ዩክሬን ፑቲንን ለመግደል እየሞከረች ነው ስትል ከሳለች።
የክሬምሊን ቤተመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉት ለጥቃት የተሰማሩት ድሮኖችን የፕሬዝዳንቱ ጥበቃ ኃይል በኤሌክትሮኒክ ራዳር ከጥቅም ውጪ አድርገዋቸዋል።
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ ለአገሪቱ መንግሥት የዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ ፑቲን በወቅቱ ክሬምሊን ውስጥ አልነበሩም፤ እንዲሁም በቤተመንግሥቱ ሕንጻዎች ላይ ምንም አይነት የደረሰ ጉዳት የለም ብለዋል።
ሩሲያ ስለ ጥቃቱ ክስ ካሰማች በኋላ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የቀረባበቸውን ክስ ሐሰት ሲሉ አጣጥለውታል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሩሲያ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ እና እውነተኛነታቸው ያልተረጋገጡ ቪዲዮዎች ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ላይ ከማዕከላዊ የሞስኮ ክፍል የሚነሳ ጭስ አሳይተዋል።
ከክሬምሊን በተሰጠ መግለጫ ላይ “ባለፈው ምሽት የዩክሬን መንግሥት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ክሬምሊን ውስጥ በሚገኘው የሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሯል።”
ጨምሮም “ፕሬዝዳንቱን ለመግደል የታቀደ የሽብር ተግባር በመሆኑ፣ ሩሲያ አስፈላጊ በሆነ በየትኛው ቦታ እና ጊዜ የአጸፋ እርምጃ የመውሰድ መብት አላት” ብሏል።
ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል የተባሉት ድሮኖች ስብርባሪ በክሬምሊን ቤተመንግሥት ግቢ ውስጥ የወደቁ ሲሆን፣ ምንም ጉዳት እንዳላደረሱ ተገልጿል።
መግለጫው በፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን እና ያሏቸው መረሃ ግብሮች በሙሉ በተያዘላቸው ቅደም ተከተል መሠረት በተለመደው ሁኔታ ይካሄዳሉ ብሏል።
ይህ ጥቃት የተፈጸመው የውጭ አገራት እንግዶች የሚታደሙበት እና ከቀናት በኋላ ከሚከበረው ከሩሲያ የድል ቀን በዓል ቀደም ብሎ መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ጠቅሷል።
በሩሲያ በኩል የተሰነዘረባት ጥቃት ተፈጽሞብኛል የሚለው ክስ ዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማካሄድ እንደ ሰበብ የቀረበ ነው ሲሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።
ፊንላንድን በመጎብኘት ላይ የነበሩት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ አገራቸው የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ለመግደል ጥቃት ፈጽማለች መባሉን ውድቅ አድርገውታል።
“ፑቲንንም ወይም ሞስኮን አናጠቃም። የምንዋጋው በራሳችን ግዛት ውስጥ ነው። እኛ እየተከላከልን ያለነው የራሳችንን መንደሮች እና ከተሞች ነው” በማለት ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት አስተባብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ የሆኑት ማይኼሎቭ ፖዶሊያክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ክሱ ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ “ለመጠነ ሰፊ የሽብር ጥቃት እየተዘጋጀች” ሊሆን እንደሚችል አመልካች ነው ሲሉ ከሰዋል።












